የጸጋ ስጦታዎች ክርክርና የእግዚአብሔር ሉዓላዊ ነፃነት፡ ጥያቄው ራሱ ስህተት ሲሆን!
በቤተክርስቲያን ታሪክ ውስጥ ለዘመናት የቆየውና ምዕመኑን ለሁለት የከፈለው፣ በዘመናችንም ያሉ የክርስቲያን ነገረ-መለኮት ክርክሮች በአብዛኛው የሚያጠነጥኑት “የጸጋ ስጦታዎች በዚህ ዘመን አሉ ወይስ የሉም?” በሚሉ ሁለት የቆሙ ጽንፎች ላይ ነው።
📍 በአንድ በኩል ስጦታዎች ከሐዋርያት ሞትና ከመጽሐፍ ቅዱስ ተጽፎ መጠናቀቅ (Canonization) ጋር አብረው አክትመዋል የሚሉ “ሴሴሺየኒስቶች” (Cessationists) ሲሰለፉ፤
📍 በሌላ በኩል ደግሞ ስጦታዎች በሐዋርያት ዘመን እንደነበሩት ሁሉ ዛሬም በግድ መታየት አለባቸው የሚሉ “ኮንቲኒውየሺኒስቶች” (Continuationists) ይገኛሉ።
ሆኖም በጥልቀት ለተመለከተው ሰው፣ ይኽ “አሉ ወይስ የሉም?” የሚለው መሠረታዊ ጥያቄ ራሱ የግንዛቤ ስህተት ያለበትና መለኮታዊውን ባሕርይ የማይመጥን ድፍረት ነው። ጥያቄው እግዚአብሔርን በሰው ልጅ የታሪክ ንባብና በነገረ-መለኮት ቀመሮች ውስጥ ለመቆለፍ የሚሞክር በመሆኑ፣ ሰጪውን ትቶ ስለ ስጦታው የሚያሟግት ከንቱ ልፋት ሆኖ ይገኛል። እግዚአብሔር ለማንም ሕግና ሥርዓት የማይገዛ፣ በምክሩ የማይመረመርና በሥራው የማይወሰን ፍጹም ሉዓላዊ አምላክ መሆኑን መዘንጋት ትልቅ ውድቀት ነው።
እኛ ይኽንን ሚዛናዊ ዕይታ " ሶቨረይንታዝም" (Sovereigntism) ወይም "ሉዓላዊያን" ለማለት ወደድን። ስም መስጠቱ መጥፎ አይደለም ብዬ ነው። ይኽ አቋም ትኩረቱ በስጦታዎቹ መኖር ወይም አለመኖር ላይ ሳይሆን፣ ስጦታዎቹን የመግለጥ ፍጹም መብቱ የባለቤቱ የእግዚአብሔር ሉዓላዊ ነፃነት መሆኑን ያውጃል። እግዚአብሔርን “ይኽን ያደርጋል” ወይም “ይኽን አያደርግም” ብሎ በሰው ቀመር ውስጥ መዝጋት የመለኮትን እጅ እንደ መገደብ ይቆጠራል። ሐዋርያው ጳውሎስ በ1ኛ ቆሮንቶስ 12፥11 ላይ “ይኽን ሁሉ ግን ያ አንዱ መንፈስ እንደሚፈቅድ ለእያንዳንዱ ለብቻው እያካፈለ ያደርጋል” በማለት የነገሩ ባለቤት መንፈስ ቅዱስ መሆኑን ያረጋግጣል። ይኽ “እንደሚፈቅድ” የሚለው ሐረግ ለማን፣ መቼ፣ የትና በምን ዓይነት መጠን መስጠት እንዳለበት ውሳኔው የመለኮት እንጂ የሰው ልጅ ንድፈ-ሐሳብ አለመሆኑን ያሳያል። ስለዚህ እግዚአብሔር በአንድ ዘመን ቤተክርስቲያንን ለማነጽ ተአምራትን ሊያበዛ ይችላል፤ በሌላ ዘመን ደግሞ በጥበብና በቃል ስጦታዎች ሊያጸናት ይችላል። ይኽ የእርሱ የጥበብ ባለቤትነት እንጂ የሥራው መቋረጥ ወይም የመለወጡ ማረጋገጫ ተደርጎ ሊወሰድ አይገባውም። “ነፋስ ወደሚወደው ይነፍሳል” (ዮሐንስ 3:8)፤ ነፋስን ማንም ሰው “በዚህ በኩል እለፍ” ወይም “እዚህ ጋር ቁም” ሊለው እንደማይችል ሁሉ፣ መንፈስ ቅዱስም በቤተክርስቲያን ታሪክ ውስጥ የጸጋ ስጦታዎቹን የሚገልጥበት መንገድ ለማንም የሰው ልጅ ፍልስፍና አይገዛም።
🚩 “ስጦታዎች አቁመዋል” የሚለው ወገን፣ ሳያውቀው እግዚአብሔርን በታሪክ መዝገብ ቤት ውስጥ ያስራል። እግዚአብሔር ትላንት የሠራውን ዛሬም የመሥራት አቅም እያለው፣ “አይችልም” ወይም “አያደርግም” ብሎ መደምደም የመንፈስ ቅዱስን ሕያውነት መካድ ነው። ይኽ አቋም የመጽሐፍ ቅዱስን ሙሉ ሥልጣን ለማስከበር ቢሞክርም፣ ሳያውቀው የመንፈስ ቅዱስን ሕያውና በተለያየ አሠራር መገለጡን ወደ ቀዝቃዛ የታሪክ መዝገብነት ይለውጠዋል። እግዚአብሔር በፈለገው ሰዓትና ቦታ የፈለገውን ስጦታ የመግለጥ መብቱ የተጠበቀ በመሆኑ፣ “አቁሟል” የሚለው ድምዳሜ የእግዚአብሔርን ሉዓላዊነት የሚጋፋ ነው።
🚩 በአንጻሩ ደግሞ፣ “የጸጋ ስጦታዎች ሁልጊዜና በሁሉም ቦታ ሊኖሩ ይገባል” የሚለው ወገን፣ እግዚአብሔርን በሰው ፍላጎትና ስሜት ውስጥ የመዘወር አደጋ አለበት። ስጦታዎችን እንደ ግዴታ ወይም እንደ ቀመር ማየት፣ እግዚአብሔርን እንደ ሰራተኛ የመቁጠር ያህል ነው፤ ይኽም ለእግዚአብሔር የሚገባውን ሉዓላዊ ክብር ይነጥቃል። ስለዚህ “ስጦታዎች በየቀኑ ካልታዩ እግዚአብሔር የለም ወይም አልሰራም” የሚለው አመለካከት፣ እግዚአብሔርን በሰው ልጅ ቁጥጥር ስር ለማዋል መሞከር ነው።
የ“ሉዓላዊያን” እይታ ይኽ ጥያቄ፣ “የጸጋ ስጦታዎች በዚህ ዘመን አሉ ወይስ የሉም?”፣ ራሱ መሠረታዊ የሆነ የግንዛቤ ስህተት ያለበት መሆኑን የሚያረጋግጥባቸው ሦስት ሰፋ ያሉ መለኮታዊ ምክንያቶች አሉ፦
1. የመለኮትን ነፃነት መጋፋቱ
የመጀመሪያውና ዋናው ምክንያት ጥያቄው እግዚአብሔርን “አዎ” ወይም “አይደለም” በሚል የሰው ልጅ ጠባብ ቀመር ውስጥ ለማስገደድ መሞከሩ ነው። እግዚአብሔር በባሕርዩ ፍጹም ነፃ አምላክ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ስለ መለኮታዊ ነፃነት ሲናገር “አምላካችንስ በላይ በሰማይ ነው፤ በሰማይም በምድርም የፈቀደውን ሁሉ አደረገ” (መዝ. 115፥3) ይላል። “አሉ” ወይም “የሉም” ብሎ መከራከር ግን እግዚአብሔርን በአንድ ወገን “ይኽን እንድታደርግ ተፈርዶብሃል” በሌላ ወገን ደግሞ “ይኽን እንዳታደርግ ታግደሃል” የማለት ያህል ድፍረት ነው። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ መንፈስ ቅዱስ አሠራር ሲያስተምር ነፋስን እንደ ምሳሌ በመጥቀስ “ነፋስ ወደሚወደው ይነፍሳል... ከመንፈስ የተወለደ ሁሉ እንዲሁ ነው” (ዮሐ. 3፥8) ብሏል። ነፋስን ማንም ሰው “ዛሬ በዚህ በኩል ብቻ ንፈስ” ብሎ ድንበር ሊያበጅለት እንደማይችል ሁሉ፣ መንፈስ ቅዱስም በፈለገው ዘመንና በፈለገው ቦታ ስጦታውን የመግለጥ መለኮታዊ ነፃነት አለው። ጥያቄው ይኽንን ነፃነት ነጥቆ እግዚአብሔርን በሰው ልጅ የንድፈ-ሐሳብ እስር ቤት ውስጥ ስለሚቆልፈው መሠረታዊ ስህተት አለበት። እግዚአብሔርን "አለብህ" ወይም "አትችልም" በሚሉ ሰዋዊ አጥር ውስጥ ማገድ የአምላክን ልዑልነት አለመረዳት ነው።
2. ከሰጪው ይልቅ በስጦታው ላይ ማተኮሩ
ሁለተኛው ስህተት ጥያቄው ትኩረቱን ከሰጪው (The Giver) ነቅሎ ወደ ስጦታው (The Gift) ማዞሩ ነው። “የጸጋ ስጦታዎች አሉ ወይ?” ብሎ መጠየቅ፣ ትኩረቱን ወደ ተአምራቱ፣ ወደ ልሳኑ ወይም ወደ ትንቢቱ ያደርጋል። ይኽ ደግሞ አማኙን በስጦታዎች ፍለጋ ውስጥ እንዲባዝን ወይም ስጦታዎች ሲታጡ ደግሞ በእግዚአብሔር ሕያውነት ላይ ጥርጣሬ እንዲገባው ያደርጋል። ነገር ግን መጽሐፍ ቅዱስ “ይህን ሁሉ ግን ያ አንዱ መንፈስ እንደ ወደደ ለእያንዳንዱ ለራሱ እያካፈለ ያደርጋል” (1ቆሮ. 12፥11) ይላል። እዚህ ጋር ትኩረቱ “ማን አደረገው?” በሚለው ላይ እንጂ “ምን ተደረገ?” በሚለው ላይ አይደለም። “ሉዓላዊያን” እንደመሆናችን፣ እግዚአብሔር ዛሬ ተአምር ባያደርግ እንኳ እርሱ ዛሬም ተአምር አድራጊ አምላክ መሆኑን እናምናለን። ጥያቄው “ምን ተደረገ?” በሚለው ክስተት ላይ ሲያተኩር፣ እግዚአብሔርን በሥራው ብቻ የምንመዝነው ይመስላል፤ ይኽ ደግሞ እርሱን እንደ ባሪያ ወይም እንደ ሰራተኛ የመቁጠር ያህል ስህተት ነው። ትኩረታችን ሊሆን የሚገባው ስጦታውን በሚሰጠው ሉዓላዊ አምላክ ላይ ብቻ ነው። እርሱ በዝምታውም ውስጥ አምላክ ነው፤ በተአምራቱም ውስጥ አምላክ ነው።
3. የእግዚአብሔርን ጥበብ መገደቡ
ሦስተኛውና የመጨረሻው ነጥብ ጥያቄው የእግዚአብሔርን ጥበብና አርቆ አሳቢነት ችላ ማለቱ ነው። እግዚአብሔር ለቤተክርስቲያን የሚያስፈልጋትን መቼና እንዴት መስጠት እንዳለበት የሚያውቀው እርሱ ብቻ ነው። በኤፌሶን 4፥7 ላይ “ነገር ግን እንደ ክርስቶስ ስጦታ መጠን ለእያንዳንዳችን ጸጋ ተሰጠን” ይላል። ይኽ “እንደ ክርስቶስ ስጦታ መጠን” የሚለው ሐረግ ሰጪው ያለውን የጥበብ ልክ ያሳያል። ቤተክርስቲያን በተለያዩ ዘመናት ውስጥ ስታልፍ፣ በየዘመኑ የሚያስፈልጋት የስጦታ ዓይነት ሊለያይ ይችላል። እግዚአብሔር በአንድ ዘመን ተአምራትን በማብዛት ወንጌልን ሊያስፋፋ ይችላል፤ በሌላ ዘመን ደግሞ በቃሉ እውነትና በጽናት ስጦታ አማኞችን ሊያጸና ይችላል። ይኽንንም የሚያደርገው በምክሩ ባለጠግነት ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ በሮሜ 11፥33 ላይ “የእግዚአብሔር ባለ ጠግነትና ጥበብ እውቀቱም እንዴት ጥልቅ ነው፤ ፍርዱ እንዴት የማይመረመር ነው፥ ለመንገዱም ፍለጋ የለውም” እንዳለ፣ እኛ በጠባብ አእምሮአችን “ዛሬ ስጦታ ሊኖር ይገባል ወይም የለበትም” ብለን የእግዚአብሔርን ጥበብ ልንገደብ አንችልም። እግዚአብሔር ለቤተክርስቲያኑ የሚበጀውን የሚያውቅ ሉዓላዊ አባት ስለሆነ፣ ጥያቄውን ለእርሱ ጥበብ ትተን በታዛዥነት መኖር ይገባናል።
በአጠቃላይ፣ “ሉዓላዊያን” (Sovereigntists) ስንል፣ እግዚአብሔርን ከሰው ቀመር ነፃ የሚያወጣ፣ ትኩረቱን በሰጪው ላይ የሚያደርግ እና መለኮታዊ ጥበቡን የሚያከብር አቋም መያዛችንን ነው። እግዚአብሔር ዛሬም ድውያንን የመፈወስ፣ ትንቢትን የማናገር፣ ተአምራት የማድረግ ሙሉ አቅም አለው፤ ነገር ግን ይኽንን የሚያደርገው እኛ “አሉ” ስለአልን ወይም በሰው ቀመር ስለወሰንን፤ የማያደርገው ደግሞ እኛ "የሉም" ስላልን ሳይሆን፣ እርሱ በራሱ ጥበብና ለቤተክርስቲያን መታነጽ አስፈላጊ ሆኖ ሲያገኘው ብቻ የሚያደርገው ነው። እውነተኛው መንፈሳዊ ጥያቄ “አሉ ወይስ የሉም?” የሚለው ድርቅ ያለ ክርክር ሳይሆን፣ “እግዚአብሔር ዛሬ ለቤተክርስቲያኑ የሚበጀውን በሉዓላዊነቱ ምን ሊሰጥ ይወዳል?” የሚለው መሆን አለበት። ይኽ አቋም አማኙን ከሁለት አደገኛ ጽንፎች ይታደጋል፤ እግዚአብሔርን “አይሰራም” ብሎ ከመገደብ (Skepticism) እና እግዚአብሔርን “አሁኑኑ ተአምር አድርግ” ብሎ ከመፈታተን (Presumption) ይጠብቃል። በዚህም “እግዚአብሔርን ማወቅ” (Theology) ማለት እርሱን መቆጣጠር ሳይሆን ለእርሱ ሉዓላዊነት እጅ መስጠት መሆኑን ግንዛቤ ይፈጥራል። ስለዚህ “አሉ ወይስ የሉም?” ከሚል የክርክር መንፈስ ወጥቶ “ጌታ ሆይ፣ በሉዓላዊነትህና በጥበብህ ለዛሬዋ ቤተክርስቲያን የሚበጀውን ስጦታ እንደ ፈቃድህ ስጥ” ወደሚል ጸሎትና አምልኮ ሊለወጥ ይገባል። እግዚአብሔር እንደ ወደደ የሚሠራ አምላክ መሆኑን አምኖ መቀበል፣ የነገረ-መለኮት ክርክርን አቁሞ ወደ እውነተኛው አምልኮና ለፈቃዱ ወደ መገዛት የሚያመራ ብቸኛው መጽሐፍ ቅዱሳዊ መንገድ ነው። እግዚአብሔርን ማወቅ” (Theology) ማለት እርሱን መቆጣጠር ሳይሆን ለእርሱ ሉዓላዊነት እጅ መስጠት ነው!
እናንተስ? እግዚአብሔርን በሁለቱ ጽንፎች ከመገደብ ወጥታችሁ ለሉዓላዊነቱ እጅ ስትሰጡ ምን ዓይነት መንፈሳዊ እረፍት የምታገኙ ይመስላችኋል? አሳባችሁን አጋሩኝ።
የጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋና ሰላም ከሁላችሁ ጋር ይሁን!"
No comments:
Post a Comment