በዚኽ በሩጫና በውጥረት በናወዘ ዓለም ውስጥ ሁላችንም አንድ የጋራ ምስጢር አለን፤ እርሱም 'ጥማት' ነው። የተሻለ ሥራ ስናገኝ፣ የሚያምር ቤት ስንሠራ፣ ዝናና እውቅናን ስንጎናጸፍ 'ጥማታችን' የሚያበቃ ይመስለን ይሆናል። ነገር ግን ድል ባደረግን ቁጥር ውስጣችን "ገና ነው፣ አልሞላም" የሚል ባዶነት ይጮኻል። ይኽ ባዶነት የቁሳቁስ እጥረት ሳይሆን፣ የነፍስ ርሃብ ነው። የሰው ልጅ የተፈጠረው ከምድር ቢሆንም፣ በውስጡ ግን ሰማያዊ 'ጥማት' ተተክሏል። ይኽን ጥማት ደግሞ በምድራዊ መጠጥ ለማርካት መሞከር የባዶነት ትልቁ ምክንያት ነው።
በዮሐንስ ወንጌል ምዕራፍ 4 ላይ የምናገኛት ሳምራዊቷ ሴት፣ የዘመናችን ወጣትና ጎልማሳ ትክክለኛ ምሳሌ ናት። እርሷም እንደ እኛ ደስታን ፍለጋ ብዙ ደጅ ጠንታለች፤ ብዙ "የጉድጓድ ውኃዎችን" ቀድታለች። ነገር ግን ጌታ ኢየሱስ በጉድጓዱ አጠገብ አግኝቶ እንዲህ አላት፦ "ከዚህ ውኃ የሚጠጣ ሁሉ እንደገና ይጠማል፤ እኔ ከምሰጠው ውኃ የሚጠጣ ሁሉ ግን ለዘላለም አይጠማም" (ዮሐ. 4፥13-14)።
ዛሬም ዓለም የምታቀርብልን 'ውኃ' (ገንዘብ፣ ሥልጣን፣ ሱስ፣ ጊዜያዊ ደስታ) ለጥቂት ጊዜ ያደነዝዘን ይሆናል እንጂ ጥማታችንን አይቆርጥም። ዓለማዊ ስኬት ጨው እንደተቀላቀለበት ውኃ ነው፤ በጠጣነው ቁጥር ይበልጥ ያስጠማናል፣ አያረካንም።
ታላቁ የሥነ-መለኮት ሊቅ አውግስጢኖስ (Augustine of Hippo) Confessions በተሰኘው መጽሐፉ የመጀመሪያው ምዕራፍ የመጀመሪያው አንቀጽ ላይ፣ "አቤቱ ለራስህ ፈጠርኸን፣ ልባችንም በአንተ ውስጥ እስካላረፈ ድረስ ሰላም(ዕረፍትን) አያገኝም" በማለት ተናግሮ ነበር። በልባችን ውስጥ እግዚአብሔር ብቻ ሊሞላው የሚችል አንድ ክፍተት አለ። ይኽን ክፍተት በሰው፣ በንብረት ወይም በዝና ለመሙላት መሞከር ባዶ ቅርጫት ውስጥ ውኃ የመቅዳት ያህል ነው። ጎልማሳው በሥራው ስኬት ውስጥ፣ ወጣቱ በቴክኖሎጂና በዝነኝነት ውስጥ የሚፈልገው ያ ባዶነት፣ በእውነቱ ያለበት የፈጣሪ ናፍቆት ነው። ነፍሳችን የጠፋችበትን ቤት እየፈለገች ነው፤ ያ ቤት ደግሞ ክርስቶስ ነው።
መመለስ የሚጀምረው 'ጎድሎኛል' ብሎ ከማመን ነው። በገዛ ጥረታችን ሰላምን ለመፍጠር የምናደርገው ሩጫ ደክሞናል? ነፍሳችን በኃጢአትና በዓለም ጭንቀት ዝላለች? ጌታ ዛሬም በታላቅ ድምፅ "ማንም የተጠማ ቢኖር ወደ እኔ ይምጣና ይጠጣ" (ዮሐ. 7፥37) ይለናል። ኢየሱስን መከተል 'ኃይማኖታዊ' ግዴታ ሳይሆን፣ ከተጠማንበት በረሃ ወደ ሕይወት ወንዝ መሻገር ነው። እርሱ የሚሰጠን ሰላም ዓለም እንደሚሰጠው አይደለም፤ የማይለወጥ፣ የማይጠፋና የማይሰረቅ ሰላም ነው።
ወዳጄ ሆይ! የልብህን ባዶነት በጊዜያዊ ነገሮች ለመሸፈን አትታገል፤ ጥማትህ የእግዚአብሔር ጥሪ ነው። ይኽ ጥሪ ወደ ቀደመው ማንነትህ፣ ወደ ፈጣሪህ ፍቅርና ወደ እውነተኛው ዕረፍት እንድትመለስ የሚጋብዝህ የሰማይ ድምፅ ነው። ዛሬም ጌታ በልብህ ደጅ ቆሞ ያንኳኳል፤ የልብህን በር ከከፈትክለት እርሱ ይገባል፣ የጎደለውንም ማንነትህን ሞልቶ የተረፈ ሕይወት ይሰጥሃል። ባዶነትህን ወደ ሙላት፣ ጥማትህን ወደ ዕርካታ ለመለወጥ ኢየሱስ ዛሬም ታማኝ ነው። ወደ እርሱ ተመለስ፤ እውነተኛው ሕይወት እርሱ ነውና!
እግዚአብሔር በዓለም ሩጫ የዛሉ ነፍሶቻችንን ወደ ራሱ ይመልስ፤ የልባችንንም ጥማት በማይጠፋው ፍቅሩ ያርካው! ከንቱውን ትተን ዘላለማዊውን እንድንይዝ ጸጋው ይርዳን!
የጌታ ኢየሱስ ዕረፍት ይብዛላችሁ!
https://t.me/anidSew
No comments:
Post a Comment