በደም የተከተበ ምስክርነት
የቀደሙት አባቶችና እናቶች ክርስቲያን በመሆናቸው ብቻ ያለፉበት የመከራ እቶን፣ ለዛሬዋ ቤተ ክርስቲያን የጸና መሠረትና የሕይወት ዘር የሆነ ታላቅ ታሪክ ነው። በጥንቷ ሮም ስደት በበረታበት ዘመን፣ ክርስትናን መምረጥ ማለት ሞትን እንደ ጓደኛ መቅጠር ማለት ነበር። እነዚያ ቅዱሳን ግን ከምድራዊው ሰላም ይልቅ ሰማያዊውን አክሊል በመናፈቅ፣ በደማቸው የታተመ የጽናት ምስክርነትን ጥለውልን አልፈዋል።
በመጀመሪያዎቹ ሦስት መቶ ዓመታት፣ ክርስቲያኖች በሮማውያን ነገሥታት ዘንድ እንደ መንግሥት ጠላት ይታዩ ነበር። ምክንያቱም 'ጌታችን ቄሣር ነው' ብለው ለመናገር ባለመፍቀዳቸውና ለሮም አማልክት ባለመስገዳቸው ነው። በዚህም ምክንያት በታሪክ መጻሕፍት ውስጥ የሚዘገንኑና ልብን የሚሰብሩ መከራዎች በእነርሱ ላይ ደርሰዋል፤ ለአራዊት ተጥለዋል፣ በእሳት ተቃጥለዋል፣ እንዲሁም በሰይፍ ተሰይፈዋል። በተለይም በኔሮን፣ በዲዮቅልጥያኖስና በዶሜጥያኖስ ዘመን ደማቸው እንደ ውኃ ፈስሷል። ይኽ ሁሉ መከራ ግን አስቀድሞ በጌታ የተነገረ ነበር፣ “በዓለም ሳላችሁ መከራ አለባችሁ፤ ነገር ግን አይዞአችሁ፤ እኔ ዓለምን አሸንፌዋለሁ” (ዮሐ. 16፥33)። የሚያስደንቀው እውነታ መከራው በበዛ ቁጥር የክርስቲያኖች ቁጥር ይበልጥ መጨመሩ ነው። ታላቁ የቤተ ክርስቲያን አባት ተርቱሊያን እንደተናገረው፣ “የሰማዕታት ደም ለቤተ ክርስቲያን ዘር ነው”፤ አንዱ ሲሞት አሥሩ ይተኩ ነበር። ምንአልባት ይኽ ጠፍቶ ይሆን የምንበዛበት ፍጥነት 'እንደእንትን' ቀስ ያለው።
እነዚህ ቅዱሳን መከራውን የተቀበሉት በለቅሶ ሳይሆን በዝማሬና በደስታ ነበር። እንደ ቅዱስ ፖሊካርፕ ያሉ አባቶች በእሳት ሊቃጠሉ ሲሉ፣ “ለሰማንያ ስድስት ዓመታት አገለገልኩት፤ እርሱም ክፉ አላደረገብኝም፤ ታዲያ እንዴት አምላኬንና አዳኜን እክዳለሁ?” በማለት ለሞት ሳይንበረከኩ ለክርስቶስ ያላቸውን ፍቅር አሳይተዋል። ሴቶችና ሕፃናት እንኳ ሳይቀሩ “ክርስቶስን ክዱ” ሲባሉ፣ በመስቀል ላይ የፈሰሰውን ፍቅር እያሰቡ አንገታቸውን ለሰይፍ ይሰጡ ነበር። ይህ ጽናት የመጣው ከራሳቸው ኃይል ሳይሆን፣ “የክርስቶስ ሥቃይ በእኛ ላይ እንደ በዛ፥ እንዲሁ መጽናናታችን ደግሞ በክርስቶስ በኩል ይበዛልናልና” (2ቆሮ. 1፥5) እንደሚለው ቃሉ፣በመከራው መካከል አብሯቸው ከቆመውና ሸክማቸውን ካቀለላቸው ከመንፈስ ቅዱስ ረዳትነት ነው።
በዚያ የስደት ዘመን፣ ክርስቲያኖች መኖሪያቸው በምድር ላይ አልነበረም። ስደት ሲበረታባቸው “ካታኮምብ” (Catacombs) ወደተባሉ ከመሬት በታች ያሉ ጠባብ ዋሻዎችና የመቃብር ስፍራዎች ተሰደዋል። በዚያ ጨለማ ውስጥ ሆነው ያመልኩ፣ ይጸልዩና ይማሩ ነበር። “ዓለም አልተገባቸውምና በምድረ በዳና በተራራ፥ በዋሻና በምድር ጕድጓድ ተቅበዘበዙ (ተንከራተቱ)” (ዕብ. 11፥38) ተብሎ እንደተጻፈው፣ በዚያ የጭንቅ ወቅት ነበር እንደ 'ዓሣ' (Ichthys) ያሉ ሚስጥራዊ ምልክቶችን በመጠቀም አንዱ ሌላውን የሚያውቀው (በዚኽ ምልክት ዙሪያ ሰፋ ባለ መልኩ እመለስበታለሁ)። ዛሬ የምንጠቀምባቸው ታላላቅ የነገረ መለኮት ትምህርቶችና የጸሎት ሥርዓቶች የተወለዱት በእንደዚህ ዓይነት መከራና ስደት ውስጥ ሆነው አባቶች በጠበቁት እምነት ነው።
ዛሬ እኛ ያለ ምንም ስጋት በነፃነት ስናመልክ፣ የእነዚያን ቅዱሳን መስዋዕትነት ማሰብ ይኖርብናል። የቀደሙት አባቶች መከራውን የታገሱት ለጊዜያዊ ጥቅም ሳይሆን ለዘላለማዊ ክብር ነው። የእነርሱ ጽናት ዛሬም ለእኛ ታላቅ ትምህርት ነው፤ ዓለም ብትጠላንም፣ መከራ ቢበዛብንም፣ በክርስቶስ ያለን ተስፋ ግን የማይናወጥ መሆኑን ያሳዩናል። እምነት ዋጋ እንደሚያስከፍል፣ ያ ዋጋም ወደማይጠፋ የሕይወት አክሊል (ያዕ. 1፥12፤ ራዕ. 2፥10) እንደሚያደርስ የእነርሱ ሕይወት ሕያው ምስክር ነው።
“በፈተና የሚጸና ሰው የተባረከ ነው፤ ከተፈተነ በኋላ ለሚወዱት ተስፋ ስለ እርሱ የሰጣቸውን የሕይወትን አክሊል ይቀበላልና።” (ያዕ. 1፥12)
“ልትቀበለው ያለህን መከራ አትፍራ . . . እስከሞት ድረስ የታመንህ ሁን የሕይወትንም አክሊል እሰጥሃለሁ።” (ራዕ. 2፥10)
ዛሬ ላይ ክርስትናን የሃብት ማካበቻ ሲደረግ ማየቱ እጅግ ያማል፤ አባቶቻችን በደማቸው የገነቧት ቤተ ክርስቲያን ዛሬ ላይ የንግድ መድረክ ስትሆን ማየት የሕሊና ቁስል ነው፤ አባቶቻችን ስለ እውነት አንገታቸውን ለሰይፍ በሰጡበት በዚያ ቅዱስ ስፍራ፣ ዛሬ ስለ ምድራዊ ብልጽግና ብቻ የሚጮኹ ድምፆች መብዛታቸው ልብ ይሰብራል። የቀደሙት ቅዱሳን "መስቀሌን ተሸክሜ እከተልሃለሁ" ብለው የክርስቶስን መከራ ሲካፈሉ፣ ዛሬ ግን መስቀሉን ጥለው "እንዴት ባለጸጋ እሆናለሁ?" በሚል ስስት ተጠምደዋል። መስቀሉን ተሸክሞ መከተል ቀርቶ፣ መስቀሉን ለምድራዊ ጥቅም መሸከሚያ ማድረግ የተለመደ ሆኗል። ቅዱስ ጳውሎስ “ብዙዎች ለክርስቶስ መስቀል ጠላቶቹ ሆነው ይመላለሳሉ . . . ሆዳቸው አምላካቸው ነው፥ ክብራቸው በነውራቸው ነው፥ አሳባቸውም ምድራዊ ነው” (ፊል. 3፥18-19) በማለት የተነገረው ቃል ዛሬ በዓይናችን ፊት ሲፈጸም ይታያል። የቀደሙት ቅዱሳን “ስለ ክርስቶስ ሁሉን አጣሁ” ሲሉ፣ ዛሬ ላይ ግን “በክርስቶስ ስም ሁሉን አከማቸሁ” የሚሉ ድምፆች እንዴት እንበዙ። ጳውሎስ አሁንም “አእምሮአቸውም በጠፋባቸው እውነትንም በተቀሙ፥ እግዚአብሔርን መምሰል ማትረፊያ የሚሆን በመሰላቸው” (1ጢሞ. 6፥5) ሲል የገለጻቸው ሰዎች ዓይነት ዛሬ ላይ በዝተዋል። ዛሬ ላይ ሰማዕትነት በምቾት፣ ጽናትም በጥቅም ተተክቷል። ጥንት ክርስቲያኖች ወደ አናብስት ጉድጓድ ሲወረወሩ ስለ እምነታቸው ይዘምሩ ነበር፤ ዛሬ ላይ ግን ጥቅማችን በትንሹ ሲነካ እምነታችንን ለመሸጥ አንሰቀስቅም። “ገንዘብን መውደድ የክፉት ሁሉ ሥር ነውና” (1ጢሞ. 6፥10) የሚለው ቃል ዛሬ ላይ በብዙዎች ሕይወት ውስጥ በተግባር እየታየ ነው። ዛሬ ላይ ወንጌል ሰውን ወደ ሰማይ የሚያስገባ የሕይወት መንገድ መሆኑ ቀርቶ፣ ምድር ላይ እንዴት ባለጸጋ መሆን እንደሚቻል የሚመከርበት 'የስኬት ጥበብ' ተደርጎ ተወስዷል። አባቶች በጨለማ ዋሻ ውስጥ ሆነው የሰማይን ብርሃን ያዩ ነበር፤ ዛሬ ላይ ግን በኤሌክትሪክ መብራት በደመቁ አዳራሾች ውስጥ ሆነን የውስጥ ጨለማችንን ማሸነፍ አቅቶናል። በካታኮምብ (ዋሻ) ውስጥ ሆነው በጨለማ የሚያበሩት ቅዱሳን፣ ለነፍሳቸው እንጂ ለሥጋቸው አልተጨነቁም ነበር። ዛሬ ግን በዘመናዊ ሕንጻዎችና በድምቀት ውስጥ ሆነን፣ የውስጥ ማንነታችን ግን በመንፈሳዊ ድርቅ ተመቷል። ጌታችን “ሰው ዓለሙን ሁሉ ቢያተርፍ ነፍሱንም ቢያጐድል ምን ይጠቅመዋል?” (ማቴ. 16፥26) ያለውን መሠረታዊ ጥያቄ ዘንግተን በምድራዊው ሩጫ ተጠምደናል። 'ሰው' ብቻ ሆነናል። ዛሬ ላይ ለሰማያዊው አክሊል ከመጨነቅ ይልቅ ለምድራዊው ዝና የምንሮጥበት ፍጥነት ያስፈራል። “ዓለምን ወይም በዓለም ያሉትን አትውደዱ” (1ዮሐ. 2፥15) የሚለው መለኮታዊ ትእዛዝ በስልጣንና በንብረት ፍቅር ተውጧል። ወንጌል በነጻ የተሰጠ የሕይወት ስጦታ ሆኖ ሳለ፣ ዛሬ ግን እንደ ሸቀጥ ለሽያጭና ለትርፍ መገኛ ሲውል ማየት እጅግ ያሳዝናል። የጥንቶቹ አባቶች የክርስቶስን ፍቅር በደማቸው ሲመሰክሩ፣ ዛሬ ግን ብዙዎች ክርስትናን "መሰላል" በማድረግ ለዝናና ለሥልጣን መውጫ ሲጠቀሙበት ይታያል። ዛሬ ግን በከንቱ ጩኸትና በተስፋ ቃል ሽያጭ የሰውን ልብ የሚያደነዝዙ በዝተዋል። “ሰዎች ራሳቸውን የሚወዱ ይሆናሉና፥ ገንዘብን የሚወዱ፥ ትምክህተኞች፥ ትዕቢተኞች፥ ተሳዳቢዎች፥ ለወላጆቻቸው የማይታዘዙ፥ የማያመሰግኑ፥ ቅድስና የሌላቸው፥ ፍቅር የሌላቸው፥ ዕርቅን የማይሰሙ፥ ሐሜተኞች፥ ራሳቸውን የማይገዙ፥ ጨካኞች፥ መልካም የሆነውን የማይወዱ፥ ከዳተኞች፥ ችኩሎች፥ በትዕቢት የተነፉ፥ ከእግዚአብሔር ይልቅ ተድላን የሚወዱ ይሆናሉ፤” (2ጢሞ. 3፥2-4) ተብሎ የተጻፈው የስህተት ዘመን ላይ መሆናችን እርግጥ ነው።
ስለዚህ ዛሬ ላይ ቆመን ወደኋላ መመልከት ያስፈልገናል። የአባቶቻችንን የጽናት መንገድ ትተን በስስት መንገድ ላይ የምንጓዝ ከሆነ፣ ስማችን ክርስቲያን ቢባልም መንፈሳችን ግን ከጥንቶቹ አማኞች፣ ቅዱሳንና ሰማዕታት ጋር ዝምድና አይኖረውም። እግዚአብሔር ያን የጽናት መንፈስ ለእኛም ይስጠን። በመከራ ውስጥ የሚገኝ ደስታን፣ በሞት ፊት የማይደነግጥ እምነትን ተምረን ለክብሩ እንድንቆም ጸጋው ይርዳን።
የጌታ ሰላም ለሁላችሁ ይሁን!
No comments:
Post a Comment