Monday, January 5, 2026

በእርሱ ዘንድ የለውጥ ጥላ የለም . . . በሚለዋወጥ ዓለም ውስጥ የማይለወጠው ማንነት!

በዙሪያህ ያለውን ዓለም ተመልከት፤ ሁሉም ነገር በለውጥ ማዕበል ውስጥ ነው። የያዝከው ስልክ ያረጃል፣ ወቅቶች ይፈራረቃሉ፣ ስሜቶችህ እንደ አየር ሁኔታ ይዋዥቃሉ፣ እንዲያውም መስተዋት ውስጥ ስታይ የምታየው ፊትህ እንኳ ከዓመት ዓመት እየተለወጠ ነው። እኛ የፍጥረት ልጆች ሁልጊዜ "በመሆን" (Becoming) ሂደት ውስጥ ያለን ፍጥረታት ነን። ዛሬ ካለንበት ነገ የተሻለ ዕውቀት ልንጨብጥ፣ ወይም ደግሞ የነበረንን ጉልበትና ጤና ልናጣ እንችላለን። በእኛ ውስጥ ሁልጊዜም ገና ያልደረስንበት "ሊሆን የሚችል" (Potentiality) አቅም የታቀፈ ነው። ነገር ግን፣ በዚህ ሁሉ መለዋወጥ ውስጥ፣ በፍጹም የማይለወጥ፣ አንድም ስንዝር የማይናወጥ "ታላቅ ማንነት" አለ። በክርስቲያን ዕቅበተ-እምነት ስሙ መጀመሪያ ተጠቃሽ የሆነው ኖርማን ጋይስለር እንደሚያስረዳው፣ እግዚአብሔር "ፍጹም ሕያው" (Pure Actuality) ነው። ይህ ማለት 'እግዚአብሔር መሆን የሚገባው ሁሉ ቀድሞውኑ ነው' ማለት ነው! እርሱ ራሱን ለሙሴ ሲገልጥ "ያለና የሚኖር" (I AM WHO I AM) ብሎ መጥራቱ (ዘጸ. 3፥14)፣ እርሱ ምንጊዜም በሙላቱ የሚኖር፣ የማይጨምርና የማይቀንስ አምላክ መሆኑን ያረጋግጥልናል።


እግዚአብሔር "ፍጹም ሕያው" በመሆኑ በእርሱ ዘንድ "ገና ወደፊት የሚሆን" ወይም "ሊጨመር የሚችል" አዲስ ባሕርይ የለም። ለምን መሰለህ? ምክንያቱም እርሱ ቀድሞውኑ ፍጹም ሙላት ስለሆነ ነው! ለፀሐይ አዲስ ብርሃን መጨመር እንደማይቻል፣ ወይም ከባሕር ላይ ውኃ ማጉደል እንደማይቻል ሁሉ፣ በእግዚአብሔር ማንነት ላይ የሚጨመር አዲስ ጥበብም ሆነ የሚቀነስ ኃይል የለም። መዝሙረኛው የእግዚአብሔርን ዘላለማዊነትና ሙሉነት “ተራሮች ሳይወለዱ፥ ምድርም ዓለምም ሳይሠሩ፥ ከዘላለም እስከ ዘላለም ድረስ አንተ ነህ” (መዝ. 90፥2) በማለት ያወድሳል።

ይኽ እውነት ከእግዚአብሔር ጋር ያለንን ግንኙነት በምን ያህል ጥልቅ ሁኔታ እንደሚቀይረው እስኪ አስበው። እኛ ሰዎች ዛሬ የምንወደውን ሰው ነገ ልንጠላው እንችላለን፤ ዛሬ የገባነውን ቃል ነገ አቅም አጥተን ልናጥፈው እንችላለን። እግዚአብሔር ግን "ፍጹም ሕያው" በመሆኑ፣ ባሕርዩ ለሰከንድ እንኳ ዝንፍ አይልም። እግዚአብሔር ነገ ከዛሬ ይበልጥ ሊያፈቅርህ አይችልም፤ ምክንያቱም ፍቅሩ ቀድሞውኑ ፍጹም (Pure) ነው። እግዚአብሔር ነገ ከዛሬ ይበልጥ ሊያውቅ አይችልም፤ ምክንያቱም ዕውቀቱ የመጨረሻው ጫፍ ላይ ነው። ያዕቆብ ይኽንን ሲያጠናክር፣ “በጎ ስጦታ ሁሉ ፍጹምም በረከት ሁሉ ከላይ ናቸው፥ መለወጥም በእርሱ ዘንድ ከሌለ በመዞርም የተደረገ ጥላ በእርሱ ዘንድ ከሌለ ከብርሃናት አባት ይወርዳሉ” (ያዕ. 1፥17)። ይህ የእግዚአብሔር "ፍጹም መሆን" ወደ ሌላኛው ትልቅ ባሕርይው ማለትም ወደ "አለመለወጡ" (Immutability) ይመራናል። እርሱ በጊዜና በሁኔታዎች የማይታጠር፣ ሁልጊዜም በሙላቱ የሚኖር "ያለና የሚኖር" አምላክ ነው።

በዚህ በሚለዋወጥና በሚያናውጥ ዓለም ውስጥ፣ እንዲህ ዓይነት አምላክ መኖሩ ለክርስቲያን ትልቁ እፎይታ ነው። ኑሮህ ቢመሰቃቀል፣ ጤናህ ቢታወክ ወይም ዓለም ብትናወጥ፣ አንተ የተደገፍከው ግን ፈጽሞ አይናወጥም። እግዚአብሔር "ፍጹም ሕያው" ከሆነ፣ የሰጠን ተስፋና ለእኛ ያለው ፍቅርም እንደ ባሕርዩ የማይለወጥና ጽኑ ነው። "እኔ እግዚአብሔር አልለወጥም፤" (ሚል. 3፥6) የሚለው ቃል ከስሜታዊ መጽናኛነት ባለፈ፣ በእግዚአብሔር "ፍጹም መሆን" ላይ የተመሠረተ ጽኑ መለኮታዊ እውነት ነው። እርሱ ትናንትና ዛሬ እስከ ለዘላለምም ያው ነው (ዕብ. 13፥8)። ታዲያ ይህ የማይለወጥ አምላክ፣ በአንተ ሕይወት ውስጥ ስላለው ዕቅድና ዓላማ ምን ይል ይሆን?

የጌታ ሰላም ይብዛላችሁ!

No comments:

Post a Comment