በታሪክ ውስጥ የሰው ልጅን አኗኗር በእጅጉ ከቀየሩ ግኝቶች መካከል ሰው ሰራሽ አስተውሎት (Artificial Intelligence) ግንባር ቀደሙን ስፍራ እየያዘ ይገኛል። እንደ አማኝ ይህንን ቴክኖሎጂ ስንመለከት በሁለት ጽንፎች መካከል ልንወድቅ እንችላለን፤ አንደኛው በፍርሃት ርቆ መቆም ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ ያለ ምንም ጥንቃቄ ራስን አሳልፎ መስጠት ነው። ነገር ግን መጽሐፍ ቅዱሳዊው እይታ "ሁሉን መርምሩ፤ መልካሙንም ያዙ" (1 ተሰ. 5:21) በሚለው መርህ እንድንመራ ያሳስበናል። AI መረጃን የማቀነባበር እንጂ እስትንፋሰ መለኮት ያለበት "ነፍስ" ያለው ፍጥረት እንዳልሆነ መረዳት የመጀመሪያው እርምጃ ነው። እግዚአብሔር ለሰው ልጅ ዓለምን እንዲገዛና እንዲያለማ የሰጠው ጥበብ ውጤት ቢሆንም፣ ይህ መሣሪያ ፈጣሪውን የሚተካ ሳይሆን ለፈጣሪ ክብር የሚውል ሊሆን ይገባል። ሆኖም ይህ ቴክኖሎጂ በውስጡ የያዘው "ሁሉን አዋቂነት" የሚመስል ባህሪ አማኙን ከእውነተኛው የጥበብ ምንጭ እንዳያርቀው ከፍተኛ ጥንቃቄ ያስፈልጋል።
የAI አጠቃቀማችን ከክርስቲያናዊ ስነ-ምግባር አንጻር ሲመዘን ትልቁ ፈተና "ታማኝነት" ላይ ያርፋል። ዛሬ AI ድርሰቶችን ሊጽፍ፣ ስብከቶችን ሊያዘጋጅ ወይም ጥልቅ የሆኑ የሥነ መለኮት ትንታኔዎችን ሊሰጥ ይችላል። እዚኽ ጋር ግን አንድ ሞጋች ጥያቄ መነሳት አለበት፦ "ይህ ውጤት ከልቤ የፈለቀ ነው ወይስ የማሽን ውጤት?" መንፈሳዊ ሕይወት በዋነኝነት ከእግዚአብሔር ጋር የሚደረግ የግል ትጋትና ግንኙነት ውጤት ነው። አንድ አማኝ የAI ውጤቶችን እንደ ግል መንፈሳዊ ልምምዱ አድርጎ ማቅረብ ሲጀምር፣ ውስጣዊ ማንነቱና ውጫዊ ገጽታው መለያየት ይጀምራል። እግዚአብሔር የሚፈልገው የእኛን ድካም፣ ጥረትና ከልብ የሚመነጭ ምስጋና እንጂ በማሽን የተቀነባበረ ፍጹም የሚመስል ግን "ባዶ" የሆነ ጽሑፍ አይደለም። ቴክኖሎጂው ጥልቅ የሆኑ አሳቦችን ሊያቀነባብር ቢችልም፣ የመንፈስ ቅዱስን ቅባትና የልብ መለወጥን ሊተካ አይችልም። ስለዚህ ቴክኖሎጂውን እንደ ረዳት እንጂ እንደ ምንጭ አለመመልከት ለቅንነትና ለታማኝነት ሕይወታችን ወሳኝ ነው።
በመቀጠልም፣ AI በሰው ልጅ "ብቸኝነት" እና "ማኅበራዊ ትስስር" ላይ የሚያመጣው ተጽዕኖ በከፍተኛ ሁኔታ ሊሞገት የሚገባው ጉዳይ ነው። የሰው ልጅ "ብቻውን ይሆን ዘንድ መልካም አይደለም" ተብሎ እንደመፈጠሩ፣ ህብረትና ግንኙነት የሰውነቱ መገለጫዎች ናቸው። ይሁን እንጂ የAI አጠቃቀማችን ከሰዎች ጋር ካለን ቀጥተኛ ግንኙነት ይልቅ ከማሽኖች ጋር የምናደርገውን መስተጋብር እያበረታታው ነው። በዲጂታል ዓለም ውስጥ የሚሰጡ "ሰው ሰራሽ" ማጽናኛዎችና ምክሮች እውነተኛውን የወንድማማችነት መጽናናትና የቤተክርስቲያንን ኅብረት ሊተኩ አይገባም። ቤተክርስቲያን የክርስቶስ አካል እንጂ የዲጂታል መረጃዎች ስብስብ አይደለችም። AI አንዳች ስሜት ሳይኖረው "እግዚአብሔር ይወድሃል" ሊል ይችላል፤ አማኝ ግን ይህንን የሚለው ከክርስቶስ ፍቅር ተካፋይ በመሆንና ከሚሰማው ርኅራኄ በመነሳት ነው። ቴክኖሎጂው መረጃን ሊያቀርብ ይችላል እንጂ ፍቅርን፣ እምነትንና ተስፋን ሊያስተላልፍ አይችልም። በመሆኑም አጠቃቀማችን ሰዎችን ወደ ማሽን ሳይሆን ወደ ሕያው እግዚአብሔርና ወደ እውነተኛው የወንድማማችነት ሕብረት የሚመራ ሊሆን ይገባል።
ሌላው እጅግ አሳሳቢው ነጥብ የAI "ሥልጣን" (Authority) ጉዳይ ነው። ብዙ ጊዜ ቴክኖሎጂው የሚሰጠንን መልስ እንደ መጨረሻ እውነት የመቀበል ዝንባሌ ይታይብናል። ነገር ግን AI መረጃዎችን የሚያቀነባብረው በውስጡ ከተጫኑለትና በዓለም ላይ ካሉ መረጃዎች በመሆኑ፣ የዓለማዊውን አስተሳሰብ (Worldview) እና አድሎአዊነትን ሊያንጸባርቅ ይችላል። መጽሐፍ ቅዱስ "የእውነትን ቃል በትክክል" (2 ጢሞ. 2:15 አ.መ.ት.) ማስረዳትን እንደሚጠይቀን፣ ከAI የምናገኛቸውን መልሶች በቃለ እግዚአብሔር መፈተን ይኖርብናል። AI መንፈሳዊ ጥያቄዎቻችንን ሲመልስ የመስቀሉን ሞኝነት፣ የጸጋን ጥልቀትና የመንፈስ ቅዱስን ምሥጢራዊ አሠራር ላያካትት ይችላል። ይልቁንም እምነት ወደ ስነ-ልቦናዊ ቀመር ወይም ወደ ሰብአዊ ጥበብ ብቻ ሊያወርደው ይችላል። ስለዚህ የእኛ መንፈሳዊ ብስለት የሚለካው ቴክኖሎጂውን በመቃወም ሳይሆን፣ በቴክኖሎጂው መካከል የእግዚአብሔርን ድምፅ ለይቶ በማወቅና ሰብአዊ ክብራችንን ጠብቀን በመመላለስ ነው።
በመጨረሻም፣ የAI አጠቃቀማችን ለስንፍና በር እንዳይከፍት መጠንቀቅ አለብን። መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት፣ መጸለይና መንፈሳዊ ነገሮችን ማሰላሰል ድካምንና ትጋትን የሚጠይቁ የዲሲፕሊን ሥራዎች ናቸው። AI እነዚህን ሂደቶች "አሳጥሮ" ሲያቀርብልን፣ እኛ ሳንለወጥ እውቀት ብቻ እንድንሰበስብ ሊያደርገን ይችላል። እውነተኛ መንፈሳዊ እድገት የሚመጣው ግን በመረጃ ብዛት ሳይሆን በቃሉ ውስጥ በምናሳልፈው ሰዓትና በመንፈስ ቅዱስ መታደስ ነው። AIን ስንጠቀም ሁልጊዜም "ይህ መሣሪያ ለእግዚአብሔር ክብር፣ ለቤተክርስቲያን እድገትና ለሰዎች በረከት እየዋለ ነው? ወይስ እኔን ከመንፈሳዊ ጥጋትና ከእውነተኛ ትጋት እያራቀኝ ነው?" ብለን ራሳችንን መጠየቅ የዘመኑ የጥበብ መጀመሪያ ነው። ቴክኖሎጂው አገልጋያችን እንጂ አምላካችን እንዳይሆን፣ በአልጎሪዝም በተሞላው ዓለም ውስጥ በእግዚአብሔር አምሳያ መፈጠራችንንና የክርስቶስ ምስክሮች መሆናችንን አንዘንጋ።
🤔ለማሰላሰል የሚረዱ ነጥቦች🤔
1. AIን ስጠቀም (ለምሳሌ ለስብከተ፣ ለጽሑፍ ወይም ለጥናት) የራሴን ድካምና ትጋት እየተካሁበት ነው ወይስ እያገዝኩበት? AIን ተጠቅሜ የምሰራቸው እነዚህና የመሳሰሉት ሥራዎች በእግዚአብሔር ፊት "የእኔ" ተብለው ሊቀርቡ የሚችሉ ናቸው? ወይስ መንፈሳዊ አቋራጭ እየፈለግኩ ነው?
2.የAI መልሶች መጽሐፍ ቅዱሳዊ እውነትን እየደገፉ ነው ወይስ በዘመኑ አስተሳሰብ የተበረዙ ናቸው? መለየት የምችልበት መንፈሳዊ ንቃት አለኝ? በቴክኖሎጂ አማካኝነት የማገኛቸውን መረጃዎች በመጽሐፍ ቅዱስ እውነት የመመዘን ልምድ አለኝ?
3.ቴክኖሎጂው ከሰዎች ጋር ባለኝ የቀጥታ ግንኙነትና በቤተክርስቲያን ተሳትፎዬ ላይ ቦታ እየቀማኝ ይሆን?
👉 ስለዚህ ዘመኑን የሚዋጅ ጥበብ ይኑረን፤ ቴክኖሎጂው የምርምራችን ረዳት እንጂ የልባችን ጌታ፣ የጥናታችን መሣሪያ እንጂ የመንፈሳዊ ማንነታችን ምንጭ እንዳይሆን በንቃት እንመላለስ።
የጌታ የኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ ከመንፈሳችሁ ጋር ይሁን!
No comments:
Post a Comment