Friday, January 16, 2026

አምስቱ "ብቻዎች"

በታሪክ ማኅደር ውስጥ የቤተ ክርስቲያን ጉዞ በሰው ሰራሽ ወጎችና በሃይማኖታዊ ሥርዓቶች ጭጋግ ተከልሎ በነበረበት ወቅት፣ በ16ኛው ክፍለ ዘመን የተነሳው የተሐድሶ ንቅናቄ አምስት ደማቅ የብርሃን ጨረሮችን ፈነጠቀ። እነዚህ ጨረሮች "አምስቱ ሶላዎች" (The Five Solas) በመባል የሚታወቁ ሲሆን፣ "ሶላ" (Sola) የሚለው የላቲን ቃል "ብቻ" የሚል ትርጉም አለው። እነዚህ መርሖች የክርስትና እምነትን ወደ ጥንታዊውና ወደ ንጹሁ ምንጩ የመለሱ፣ የወንጌልን እውነተኛ ገጽታ የገለጡና የአማኙን ሕይወት ከሰው ሥልጣን ሥር አውጥተው በእግዚአብሔር ሉዓላዊነት ሥር ያሳረፉ የነፃነት አዋጆች ናቸው።


አምስቱ ሶላዎች በአንድነት ሲቆሙ የመዳንን መንገድ እንዲህ ሲሉ ይተርካሉ፣

1. በመጽሐፍ ቅዱስ ብቻ (Sola Scriptura) - የእውነት ሁሉ መለኪያና የመጨረሻው ሥልጣን የእግዚአብሔር ቃል ብቻ ነው።

2. በጸጋ ብቻ (Sola Gratia) - መዳናችን በገዛ ጥራታችን ወይም በሥራችን ሳይሆን፣ በእግዚአብሔር ነፃ ስጦታና ቸርነት ብቻ ነው።

3. በእምነት ብቻ (Sola Fide) - በእግዚአብሔር ፊት ጻድቅ ሆነን የምንቆመው በክርስቶስ በማመን ብቻ እንጂ በሕግ ሥራ አይደለም።

4. በክርስቶስ ብቻ (Sola Christus) - በእግዚአብሔርና በሰው መካከል ያለው ብቸኛው መካከለኛና አዳኝ ኢየሱስ ክርስቶስ ብቻ ነው።

5. ለእግዚአብሔር ክብር ብቻ (Sola Deo Gloria) - ከፍጥረት ጀምሮ እስከ መዳን ድረስ ያለው ክንውን ሁሉ የሚከናወነው ለእግዚአብሔር ታላቅ ክብር ብቻ ነው።

እነዚኽ አምስት መሠረቶች ዝም ብለው የሥነ-መለኮት ንድፈ ሐሳቦች አይደሉም፤ ይልቁንም አማኙ በጸጋ ተመርጦ፣ በእምነት ጸድቆ፣ በክርስቶስ ታርቆ፣ በቃሉ ተመርቶ፣ ለእግዚአብሔር ክብር እንዲኖር የሚያደርጉ የሕይወት መንገዶች ናቸው። ዛሬም ድረስ ቤተ ክርስቲያን ከእውነት ጎዳና እንዳትወጣ የሚጠብቋት፣ መንፈሳዊ ማንነቷን የሚመዝኑ የወርቅ ሚዛኖች ሆነው ያገለግላሉ።

1. "መጽሐፍ ቅዱስ ብቻ"

የቤተ ክርስቲያን ታሪክ አቅጣጫውን በቀየረበት በ16ኛው ክፍለ ዘመን የተሐድሶ ንቅናቄ ወቅት፣ "መጽሐፍ ቅዱስ ብቻ" (Sola Scriptura) የሚለው መርሕ እንደ አንድ ተራ የሃይማኖት መፈክር ሳይሆን፣ እንደ መንፈሳዊና ዕውቀታዊ አብዮት ነበር ብቅ ያለው። ይህ መርሕ ቤተ ክርስቲያን ለዘመናት ተብትበው የያዟትን ሰዋዊ ወጎችና የሊቃውንት ትርጓሜዎች ከፈጣሪ ቃል ጋር እኩል የማሰለፍ አባዜን በመገዳደር፣ መጽሐፍ ቅዱስ ብቻውን ለማንኛውም ክርስቲያናዊ እምነትና ተግባር የመጨረሻውና የማይሻረው የበላይ ሥልጣን መሆኑን ያውጃል። ይህ አስተምህሮ መጽሐፍ ቅዱስ ከሌሎች መጻሕፍት የተለየ "መነሻ" እንዳለው ይሞግታል፤ ይኸውም ቃሉ የሰዎች የሥነ-ጽሑፍ ውጤት ሳይሆን፣ በመለኮታዊ እስትንፋስ (Theopneustos) የተቃኘና የእግዚአብሔርን የማንነት መገለጫ የያዘ በመሆኑ ነው። ቅዱስ ጳውሎስ "የእግዚአብሔር ሰው ፍጹምና ለበጎ ሥራ ሁሉ የተዘጋጀ ይሆን ዘንድ፥ የእግዚአብሔር መንፈስ ያለበት መጽሐፍ ሁሉ ለትምህርትና ለተግሣጽ ልብንም ለማቅናት በጽድቅም ላለው ምክር ደግሞ ይጠቅማል" (2ኛ ጢሞቴዎስ 3:16-17) በማለት እንደተናገረው፣ መጽሐፍ ቅዱስ በራሱ በቂ፣ በራሱ ግልጽና በራሱ ተርጓሚ በመሆን የሰው ልጅን ሕሊና ለፈጣሪ ፈቃድ ብቻ የሚያስገዛ ብቸኛው መስታወት ሆኖ ይቆማል።

የ"መጽሐፍ ቅዱስ ብቻ"  ኃያልነት የሚመነጨው መጽሐፍ ቅዱስን እንደ አንድ የምክር መጽሐፍ ሳይሆን፣ እንደ ፍጹም መለኮታዊ ቀኖና ከመመልከት ነው። ምሁራዊ በሆነው የሥነ-መለኮት እይታ፣ ይህ መርሕ ቤተ ክርስቲያን የመጽሐፍ ቅዱስ "ፈጣሪ" ሳትሆን "ተቀባይና ጠባቂ" መሆኗን ያስምርበታል። ቤተ ክርስቲያን የመጽሐፍ ቅዱስን ሥልጣን አታጸድቅም፤ ይልቁንም የመጽሐፍ ቅዱስ ሥልጣን ቤተ ክርስቲያንን ያጸድቃታል። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዘመኑ የነበሩትን የሃይማኖት መሪዎች "ስለ ወጋችሁ የእግዚአብሔርን ቃል ሻራችሁ" (ማቴዎስ 15:6) በማለት የገሰጻቸው፣ የሰው ሥርዓት ከእግዚአብሔር ቃል በላይ ሊሆን እንደማይችል ለማስገንዘብ ነው።

ይኽ መሠረታዊ ልዩነት በመካከለኛው ዘመን የነበረውን "ቤተ ክርስቲያን ከመጽሐፍ ቅዱስ በላይ ናት" የሚለውን አስተሳሰብ ገልብጦታል። ቃሉ በራሱ የተሟላ መሆኑን (Sufficiency of Scripture) ስንረዳ፣ ለማዳን ለሚበቃ እውቀትም ሆነ ለቅድስና ሕይወት ከቃሉ ውጪ ሌላ "ልዩ መገለጥ" ወይም የሰዎች ፍልስፍና እንደማያስፈልግ እንረዳለን። ነቢዩ ዳዊት "ሕግህ ለእግሬ መብራት፥ ለመንገዴም ብርሃን ነው" (መዝሙር 119:105) እንዳለ፣ ቃሉ አማኙን ለመምራት ብቁ ነው። ይህ ጽንሰ-ሐሳብ የአማኙን ሕሊና ከሰዋዊ አምባገነንነት ነፃ በማውጣት፣ እያንዳንዱ ግለሰብ በእግዚአብሔር ቃል ፊት በቀጥታ እንዲቆም የሚያደርግ መንፈሳዊ ሉዓላዊነትን ያጎናጽፋል።

በተጨማሪም፣ ይኽ መርሕ የመጽሐፍ ቅዱስን ግልጽነት (Perspicuity) አጥብቆ ይሟገታል። መጽሐፍ ቅዱስ ለተመረጡ ጥቂት ሊቃውንት ብቻ የተሰጠ ምስጢራዊ ኮድ ሳይሆን፣ በመንፈስ ቅዱስ እርዳታ ለሚመጣ ማንኛውም ትጉህ አንባቢ የመዳንን መንገድ በግልጽ የሚያሳይ ብርሃን ነው። በቤርያ የነበሩት አማኞች "ነገሩ እንደዚሁ ይሆንን? ብለው ዕለት ዕለት መጻሕፍትን እየመረመሩ ቃሉን በሙሉ ፈቃድ ተቀበሉ" (የሐዋርያት ሥራ 17:11) ተብሎ እንደተጻፈ፣ እውነትን የመመርመር ሥልጣን የእያንዳንዱ አማኝ ድርሻ ነው። ጥልቅ ጥናትና ታሪካዊ ዳራ አያስፈልግም ማለት አይደለም፤ ይልቁንም የመጽሐፍ ቅዱስ ዋናው መልእክት፣ ማለትም የክርስቶስ የማዳን ሥራ፣ በጣም ግልጽ ከመሆኑ የተነሳ ትርጓሜው በቤተ ክርስቲያን ባለሥልጣናት ቁጥጥር ስር መውደቅ የለበትም ማለት ነው። "መጽሐፍ ቅዱስ ራሱን ይተረጉማል" (Scriptura sacra sui ipsius interpres) የሚለው መርሕ፣ አንዱ ግልጽ ያልሆነ ክፍል በሌላው ግልጽ በሆነ ክፍል መቃኘት እንዳለበት ያስተምረናል። ይህም ሥነ-መለኮት በግላዊ ስሜት ወይም በወቅታዊ የፖለቲካ ፍላጎት እንዳይበረዝ የሚከላከል ሳይንሳዊና መንፈሳዊ አጥር ነው።

"መጽሐፍ ቅዱስ ብቻ" ዛሬም ድረስ ለዘመናዊው ዓለም የሚሰጠው ትርጉም እጅግ ከፍተኛ ነው። ፍጹም የሆነ የእውነት መለኪያ በጠፋበትና "የእኔ እውነት" እና "የአንተ እውነት" በሚሉ አንጻራዊ አመለካከቶች ዓለም በታወረችበት በዚህ ዘመን፣ ይህ መርሕ የማይናወጥ ቋጥኝ ሆኖ ያገለግላል። መጽሐፍ ቅዱስ ከባህል፣ ከልማድና ከሰው ሰራሽ ሕጎች በላይ ሆኖ ሲቀመጥ፣ ማኅበረሰቡን ከሥነ-ምግባር ውድቀትና ከመንፈሳዊ ድንቁርና ይታደጋል። "መጽሐፍ ቅዱስ ብቻ" ማለት መጻሕፍትን መጥላት ሳይሆን፣ ሁሉንም መጻሕፍትና ትምህርቶች በ"መጽሐፉ" ሚዛን መመዘን ማለት ነው። ይህ ኃያል መርሕ የአማኙን ልብ ወደ ክርስቶስ፣ አእምሮውን ወደ እውነት፣ ሕይወቱን ደግሞ ወደ እግዚአብሔር ክብር የሚመራ ዘላቂ የመንፈሳዊ ተሐድሶ ሞተር ነው።

2. "ክርስቶስ ብቻ"

"ክርስቶስ ብቻ" የሚለው መርሕ 'ተመልሶ' ብቅ ያለበት ታሪካዊ ዐውድ፣ በሰውና በእግዚአብሔር መካከል በርካታ 'መካከለኛ ድልድዮች' ተገንብተው በነበረበት ወቅት ነው። በመካከለኛው ዘመን የነበረው ሥነ-መለኮት አማኙ ወደ እግዚአብሔር ለመቅረብ በቅዱሳን አማላጅነት፣ በድንግል ማርያም ልመናና በቤተ ክርስቲያን ቀኖናዊ ሥርዓቶች ውስጥ ማለፍ እንዳለበት ያስተምር ነበር። ይኽ ደግሞ ክርስቶስ በመስቀል ላይ የከፈለውን ፍጹም መሥዋዕትነት "ያልተሟላ" ወይም "ረዳት የሚሻ" አስመስሎት ቆይቷል። "ክርስቶስ ብቻ" ግን ይኽንን የተሳሳተ ግንዛቤ በመስበር፣ በኃጢአት ምክንያት የተቋረጠውን የሰውና የእግዚአብሔር ግንኙነት ለመጠገን ክርስቶስ ብቸኛውና በቂው መንገድ መሆኑን አወጀ። ሐዋርያው ጳውሎስ "በእግዚአብሔርና በሰውም መካከል ያለው መካከለኛው ደግሞ አንድ አለ" (1ኛ ጢሞ. 2፥5) ሲል፣ ይኽ "አንድ" የሚለው ቃል ሌላ ሁለተኛ ወይም ተባባሪ መካከለኛን ፈጽሞ የሚያስወግድ ነው። ክርስቶስ ሙሉ ሰውና ሙሉ አምላክ በመሆኑ፣ ሰውን ወክሎ የእግዚአብሔርን ፍትሕ ለማርካት፣ እግዚአብሔርን ወክሎ ደግሞ የሰውን ልጅ ለመታደግ ብቁ የሆነው እርሱ ብቻ ነው።

የ"ክርስቶስ ብቻ" መርሕ ጥልቀት ይበልጥ የሚታየው ክርስቶስ የያዛቸውን ሦስት ታላላቅ ማዕረጎች ስንመረምር ነው። በመጀመሪያ፣ ክርስቶስ እንደ "ነቢይ" የእግዚአብሔር የመጨረሻ ቃል ነው። ዕብራውያን 1፥1-2 እንደሚለው፣ እግዚአብሔር ቀድሞ በነቢያት ቢናገርም፣ "በልጁ በዚህ ዘመን መጨረሻ ለእኛ ተናገረን"። ይኽ ማለት ከክርስቶስ ውጭ የሚመጣ ማንኛውም 'አዲስ መገለጥ' ወይም የሰዎች ፍልስፍና ከእውነት መንገድ የሚያወጣ መሆኑን ያሳያል። በሁለተኛ ደረጃ፣ ክርስቶስ እንደ "ካህን" ራሱን መሥዋዕት አድርጎ ያቀረበና ዛሬም የሚማልድ ነው። በመካከለኛው ዘመን የነበረው 'የክህነት ሥርዓት' ካህናትን እንደ "ጸጋ ማከፋፈያ" ይመለከት ነበር፤ "ክርስቶስ ብቻ" ግን አማኙ በቀጥታ ወደ ጸጋው ዙፋን መቅረብ እንደሚችልና የክርስቶስ መሥዋዕትነት ድጋሚ የማይቀርብ (Non-repeatable) ፍጹም ሥራ መሆኑን ያረጋግጣል። በሦስተኛ ደረጃ፣ ክርስቶስ እንደ "ንጉሥ" የቤተ ክርስቲያን ብቸኛ ራስ ነው። ማንኛውም ምድራዊ መሪ ወይም ድርጅት በክርስቶስ መንጋ ላይ ፍጹም ሉዓላዊ ሥልጣን ሊኖረው አይችልም። ቤተ ክርስቲያን የምትመራው በሰው ሕግ ሳይሆን በክርስቶስ መንፈሳዊ አገዛዝ ብቻ ነው።

የ"ክርስቶስ ብቻ" መርሕ አንዱ ትልቁ ፋይዳ ለአማኙ የሚሰጠው የደኅንነት እርግጠኝነት ነው። መዳን 99% በክርስቶስ፣ 1% ደግሞ በሰው ጥረት ወይም በ'ቅዱሳን' እርዳታ የሚሆን ቢሆን ኖሮ፣ የሰው ልጅ ያቺን 1% ማሟላቱን በምንም መንገድ ሊያረጋግጥ አይችልም ነበር። ይኽ ደግሞ አማኙን በጭንቀትና በፍርሃት ውስጥ ይተወዋል። ነገር ግን ጌታ በመስቀል ላይ "ተፈጸመ" (ዮሐንስ 19:30) ሲል፣ የሰው ልጅ መዳን የሚያስፈልገውን ዋጋ በሙሉ ከፍሎ ማጠናቀቁን ማወጁ ነው። በዚኽ መርሕ መሠረት፣ 'ጽድቅ' ከሰው ወደ እግዚአብሔር የሚወጣ ሳይሆን፣ ከክርስቶስ ወደ አማኙ የሚሰጥ (Imputed Righteousness) ስጦታ ነው። አማኙ በራሱ ቅድስና ሳይሆን በክርስቶስ ፍጹም ጽድቅ ተሸፍኖ በእግዚአብሔር ፊት ይቆማል። ይኽ ትምህርት የሰውን ትምክህት ሙሉ በሙሉ የሚያጠፋና ክብርን ሁሉ ለክርስቶስ ብቻ የሚሰጥ ነው። መዳን የጋራ ሥራ ሳይሆን፣ የክርስቶስ ብቻ ብቸኛ ድል ነው፤ እኛም የዚኽ ድል ተካፋዮች የምንሆነው በእርሱ ላይ በሚኖረን እምነት ብቻ ነው።

በዛሬው ዓለም "ክርስቶስ ብቻ" የሚለው መርሕ ከሁለት አቅጣጫዎች ጥቃት እየደረሰበት ይገኛል። በአንድ በኩል፣ "ሁሉም ኃይማኖቶች ወደ አንድ አምላክ ይወስዳሉ" የሚለው የኃይማኖት ብዝኃነት (Pluralism) ክርስቶስን ከብቸኛ መንገድነት አውርዶ እንደ አንዱ "ጥሩ መምህር" ብቻ ለማየት ይሞክራል። በሌላ በኩል ደግሞ፣ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ሰዋዊ መሪዎችን፣ "ነቢያትንና ሐዋርያትን" የሚባሉትን እንደ ልዩ የጸጋ በርና እንደ አማላጅ የመመልከት አዝማሚያ እንደገና እያገረሸ ይገኛል። በዚህ ዐውድ "ክርስቶስ ብቻ" እንደገና ሊሰበክ የሚገባው ወሳኝ እውነት ነው። አማኙን ከሰው አምልኮና ከኃይማኖታዊ ባርነት ነፃ የሚያወጣው ይኽ መርሕ ነው። ክርስቶስ በቂ ከሆነ፣ ሌላ መካከለኛ አያስፈልግም፤ ክርስቶስ ካዳነን፣ መዳናችን የተሟላ ነው፤ ክርስቶስ የሚማልድልን ከሆነ፣ ጸሎታችን ይሰማል። ይኽ መርሕ የክርስትናን እምነት ከማንኛውም ሃይማኖታዊ ድብልቅልቅነት (Syncretism) የሚጠብቅና የአምልኮአችንን ማዕከል በክርስቶስ ላይ ብቻ የሚተክል የሕይወት መልሕቅ ነው።

3. "በጸጋ ብቻ"

"በጸጋ ብቻ" የሚለው መርሕ ትርጉም የሚኖረው፣ በመጀመሪያ የሰው ልጅ ያለበትን አስከፊ የኃጢአት ደረጃ ስንረዳ ነው። የተሐድሶው ሥነ-መለኮት እንደሚያስተምረው፣ የሰው ልጅ በውድቀት ምክንያት "በበጎ ሥራው እግዚአብሔርን ደስ ማሰኘት" የሚችልበትን አቅም ብቻ ሳይሆን፣ ወደ እግዚአብሔር የመምጣት "ፍላጎቱን" ጭምር አጥቷል። ሰው በኃጢአቱ ምክንያት በመንፈስ "ሙት" እንደመሆኑ (ኤፌ. 2፥1)፣ ሙት ደግሞ ራሱን በራሱ ማንሳት እንደማይችል ሁሉ፣ የሰው ልጅም ያለ እግዚአብሔር ቀዳሚ ረድኤት ወደ ሕይወት ሊመጣ አይችልም። በመሆኑም ጸጋ ማለት ለደካማ ሰው የሚሰጥ "ተጨማሪ ኃይል" ሳይሆን፣ ለሞተ ሰው የሚሰጥ "ሕይወት" ነው። ይኽ መርሕ መዳንን ከሰው ልጅ 'ብቃት' አውጥቶ በእግዚአብሔር "ቸርነት" ላይ ብቻ ይተክለዋል። ጸጋ እግዚአብሔር ለእኛ ያለው ሞገስ ብቻ ሳይሆን፣ በውስጣችን የሚሠራና ፈቃዳችንን ወደ በጎ የሚለውጥ መለኮታዊ ኃይልም ጭምር ነው።

በተሐድሶው ወቅት የነበረው ትልቁ ክርክር "ሰው ለመዳኑ ምን ያህል ድርሻ አለው?" በሚለው ነጥብ ላይ ነበር። በመካከለኛው ዘመን የነበረው አስተሳሰብ "እግዚአብሔር ጸጋውን ይሰጣል፣ ሰው ደግሞ በነፃ ፈቃዱ ይተባበራል" (Synergism) የሚል ነበር። ነገር ግን "በጸጋ ብቻ" ይኽንን ሐሳብ በመቃወም መዳን "Monergistic" ወይም የእግዚአብሔር ብቸኛ ሥራ መሆኑን ያውጃል። እግዚአብሔር የሰውን ልጅ ለማዳን ሲነሳ፣ በሰው ውስጥ ያየው አንዳች "መልካም ነገር" ኖሮ ሳይሆን፣ በገዛ ሉዓላዊ ፈቃዱና በምሕረቱ ባለጠግነት ምክንያት ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ በሮሜ 9፥16 ላይ “እንግዲህ ምሕረት ለወደደ ወይም ለሮጠ አይደለም፥ ከሚምር ከእግዚአብሔር ነው እንጂ” ሲል፣ የመዳን መነሻውም ሆነ መድረሻው የእግዚአብሔር ጸጋ መሆኑን ማረጋገጡ ነው። ይኽ መርሕ እግዚአብሔርን "ረዳት አዳኝ" ከመሆን አውጥቶ "ብቸኛ አዳኝ" እና "የሕይወት ምንጭ" ወደ መሆን ዙፋኑ ይመልሰዋል።

"በጸጋ ብቻ" የሚለው ትምህርት የሰውን ልጅ ትዕቢት ሙሉ በሙሉ የሚያፈርሰ ሥነ-መለኮታዊ መሣሪያ ነው። መዳን በከፊልም ቢሆን በሰው ሥራ፣ በጾም፣ በጸሎት ወይም በሃይማኖታዊ ትጋት ላይ የተመሠረተ ቢሆን ኖሮ፣ ሰው በእግዚአብሔር ፊት "ይገባኛል" የማለትና የመመካት ዕድል ይኖረው ነበር። ነገር ግን መዳን 100% የእግዚአብሔር ስጦታ መሆኑን ስንረዳ፣ ብቸኛው ምላሻችን ትሕትናና ምስጋና ብቻ ይሆናል። ይኽ ጸጋ አማኙን ከኃጢአት በደል ነፃ የሚያወጣ ብቻ ሳይሆን፣ ለቅድስና ሕይወትም የሚያበቃ ነው። ቲቶ 2፥11-12 እንደሚለው "ሰዎችን ሁሉ የሚያድን የእግዚአብሔር ጸጋ ተገልጦአልና፤ ይህም ጸጋ፥ ኃጢአተኝነትንና ዓለማዊ ምኞትን ክደን . . . ራሳችንን በመግዛትና በጽድቅ እግዚአብሔርንም በመምሰል በአሁኑ ዘመን እንድንኖር ያስተምረናል"። ስለዚህ ጸጋ ለኃጢአት ፈቃድ የሚሰጥ "የላላ አኗኗር" ሳይሆን፣ ለእግዚአብሔር ክብር እንድንኖር አቅም የሚሰጠን "መለኮታዊ ሞተር" ነው።

"በጸጋ ብቻ" የሚለው መርሕ ለአማኙ የሚሰጠው ትልቁ በረከት "መንፈሳዊ ዕረፍት" ነው። ይኽ ዕረፍት የሚመነጨው መዳናችን በራሳችን ብቃት፣ ጥረት ወይም በማንነታችን ላይ የተመሠረተ አለመሆኑን ከመረዳት ነው። መዳን በከፊልም ቢሆን በእኛ የሥነ-ምግባር ጥንካሬ ወይም ስህተት ባለመሥራት ላይ የተንተራሰ ቢሆን ኖሮ፣ ዛሬ በሠራነው ድካም ምክንያት ነገ ደኅንነታችንን ልናጣ እንችላለን በሚል የማያቋርጥ የሕሊና ጭንቀትና ፍርሃት እንዋጥ ነበር። ነገር ግን መዳን የጀመረው በእግዚአብሔር የማይለወጥ ጸጋና ሉዓላዊ በጎነት በመሆኑ፣ አማኙ ትኩረቱን ከራሱ ድካም አውጥቶ በእግዚአብሔር ፍጹም አዳኝነት ላይ እንዲያሳርፍ ያደርገዋል።

ይኽ መርሕ እግዚአብሔር የወደደንና የፈለገን ገና በኃጢአታችን ሳለን (ሮሜ 5፥8) መሆኑን በማረጋገጥ፣ የእግዚአብሔር ጸጋ ከሰው ልጅ ውድቀትና ድካም ይልቅ እጅግ ኃያል መሆኑን ያስገነዝባል። በዚህም ምክንያት አማኙ በደካማነቱና በውድቀቱ ጊዜ እንኳ ተስፋ ቆርጦ ከመኮነን ይልቅ፣ ወደ ሚምረውና ወደሚረዳው አምላክ በንስሐ የመመለስ ድፍረት ያገኛል። ምክንያቱም የደኅንነቱ መሠረት በእርሱ የሚዋዥቅ ጥንካሬ ላይ ሳይሆን፣ በማይለወጠውና ሁልጊዜ ታማኝ በሆነው በእግዚአብሔር ማንነት ላይ የተመሠረተ ስለሆነ ነው። "በጸጋ ብቻ" መኖር ማለት በራስ አቅምና ብቃት ላይ ተስፋ መቁረጥ፣ ነገር ግን በእግዚአብሔር ወሰን በሌለው ምሕረት ላይ ሙሉ በሙሉ መታመንና መደገፍ ማለት ነው።

4. "በእምነት ብቻ"

የ"በእምነት ብቻ" መርሕ ፋይዳው ጎልቶ የሚታየው፣ በእግዚአብሔር ፍጹም ቅድስና እና በሰው ልጅ የኃጢአት ጥልቀት መካከል ያለውን ገደል ስንረዳ ነው። እግዚአብሔር ፍጹም ጻድቅ በመሆኑ ኃጢአትን ዝም ብሎ ማለፍ አይችልም፤ የሰው ልጅ ደግሞ በውድቀት ምክንያት የቱንም ያህል በጎ ሥራ ቢሠራ የእግዚአብሔርን የጽድቅ መመዘኛ ሊያሟላ አይችልም። በመካከለኛው ዘመን የነበረው ሥነ-መለኮት ይህንን ክፍተት ለመሙላት "ሰው የተወሰነውን ያህል ይጣር፣ እግዚአብሔር ደግሞ የቀረውን ይሞላል" የሚል "ሲነርጂያዊ" (Synergistic) አስተሳሰብ ነበረው። ነገር ግን "በእምነት ብቻ" ይህንን ተስፋ ቢስ ድካም በመስበር፣ ጽድቅ ከሰው ጥረት የሚመነጭ ሳይሆን ከእግዚአብሔር የሚሰጥ መሆኑን አወጀ። ሐዋርያው ጳውሎስ በሮሜ 4፥5 ላይ “ነገር ግን ለማይሠራ፥ ኃጢአተኛውንም በሚያጸድቅ ለሚያምን ሰው እምነቱ ጽድቅ ሆኖ ይቆጠርለታል” ሲል፣ ጽድቅ የሥራ ውጤት ሳይሆን የእምነት ውጤት መሆኑን ያረጋግጣል። ይኽ መርሕ አማኙ በእግዚአብሔር ፊት ተቀባይነት ለማግኘት በራሱ ማንነት ላይ ሳይሆን በክርስቶስ ማንነት ላይ ብቻ እንዲደገፍ በማድረግ፣ ሕሊናውን ከሥራ ቀንበር ነፃ ያወጣል።

በ"በእምነት ብቻ" አስተምህሮ ውስጥ ማዕከላዊው ሐሳብ "መቆጠር" የሚለው ጽንሰ-ሐሳብ ነው። ይኽ ሐሳብ መጽደቅ ማለት አንድ ሰው በባሕርይው "ጻድቅ ሆነ" ማለት ሳይሆን፣ በእግዚአብሔር የፍርድ አደባባይ "ጻድቅ ተብሎ ታወጀ" ማለት መሆኑን ያስረዳል። በእምነት አማካኝነት በኃጢአተኛው ሰውና በክርስቶስ መካከል "ታላቅ ልውውጥ" ይደረጋል፤ የእኛ ኃጢአትና በደል በክርስቶስ ላይ ተቆጥሮ እርሱ በመስቀል ላይ ስለ እኛ ተቀጣ፣ የክርስቶስ ፍጹም ጽድቅና ታዛዥነት ደግሞ በእኛ ላይ ተቆጥሮ እኛ በእግዚአብሔር ፊት እንደ ጻድቅ እንታያለን። ይኽ ጽድቅ "Extra Nos" (ከእኛ ውጭ ያለ) የተባለበት ምክንያት፣ ምንጩ በእኛ ውስጥ ያለ ቅድስና ሳይሆን በክርስቶስ የተፈጸመ ሥራ ስለሆነ ነው። ስለዚህ አማኙ በእግዚአብሔር ፊት የሚቆመው በገዛ ጽድቁ ግራ ተጋብቶ ሳይሆን፣ በክርስቶስ ጽድቅ ተሸፍኖና በድፍረት ነው። ይኽ መርሕ እግዚአብሔር ኃጢአተኛውን ሳይቀጣ እንዴት ጻድቅ ሊያደርገው እንደሚችል የሚያሳይ የመለኮታዊ ጥበብ መግለጫ ነው።

ብዙዎች "በእምነት ብቻ" የሚለውን መርሕ ሲሰሙ፣ እምነት ራሱ እንደ አንድ "በጎ ሥራ" ወይም አምላክን ለማግባቢያ የሚቀርብ "ብቃት" አድርገው ይሳሳታሉ። ነገር ግን እምነት መዳንን የሚያስገኝ "መሠረት" ሳይሆን መዳንን የሚቀበል "መሣሪያ" (Instrumental Cause) ነው። እምነት በራሱ ዋጋ ኖሮት ሳይሆን፣ ዋጋ ያለውን የክርስቶስን ሥራ አጥብቆ ስለሚይዝ ብቻ ያጸድቃል። ልክ አንድ የተራበ ሰው ምግብ የሚቀበልበት እጅ ምግቡን እንደማይተካ ሁሉ፣ እምነትም ጸጋውን ይቀበላል እንጂ ጸጋውን አይፈጥረውም። እምነት "ባዶ እጅ" ነው፤ ባዶነቱ ደግሞ የእግዚአብሔርን ሙላት ለመቀበል ምቹ ያደርገዋል። ይኽ እይታ አማኙ "እምነቴ ጠንካራ ነው ወይስ ደካማ?" ብሎ በራሱ ላይ ከማተኮር ይልቅ "የማምንበት ክርስቶስ ታማኝ ነውን?" ብሎ ወደ አዳኙ እንዲመለከት ያደርገዋል። እምነት ትኩረቱን ወደ ራሱ ሳይሆን ወደ ክርስቶስ የሚያደርግ መለኮታዊ ስጦታ በመሆኑ፣ ክብርን ሁሉ ወደ ሰጪው ይመልሳል።

"በእምነት ብቻ" የሚለው መርሕ ሥራን ወይም ቅድስናን ከክርስቲያን ሕይወት የሚያገለል ተደርጎ ሊወሰድ አይገባም፤ ይልቁንም የሥራን "ቦታ" በትክክል የሚያስቀምጥ መነጽር ነው። "በእምነት ብቻ" መጽደቅ ማለት ሥራ አያስፈልግም ማለት ሳይሆን፣ ሥራ ለመጽደቅ "ቅድመ ሁኔታ" (Cause) መሆኑ ቀርቶ የመጽደቅ "ውጤት" (Evidence) መሆኑን ማሳየት ነው። እውነተኛ እምነት በተፈጥሮው ፍሬያማ ነው። አንድ ዛፍ ሕያው መሆኑ የሚታወቀው ፍሬ በማፍራቱ እንደሆነ ሁሉ፣ አንድ አማኝ በእውነት ማመኑ የሚታወቀው በሕይወቱ በሚታይ የመቀደስና የበጎ ሥራ ፍሬ ነው። ማርቲን ሉተር እንደገለጸው "እኛ የምንጸድቀው በእምነት ብቻ ነው፣ ነገር ግን የሚያጸድቀው እምነት ግን ብቻውን (ከሥራ ተለይቶ) አይኖርም"። ይኽ ማለት ሥራ መዳንን ሊገዛ ወይም ሊጨምር አይችልም፤ ነገር ግን መዳን በሰው ውስጥ መኖሩን የሚያረጋግጥ ምስክር ነው። አማኙ መልካም ሥራን የሚሠራው እግዚአብሔርን ፈርቶ ወይም ደኅንነቱን ላለማጣት ተጨንቆ ሳይሆን፣ ለተሰጠው ነፃ ጽድቅ ባለው ፍቅርና ምስጋና ተገፋፍቶ ነው። ይህም ክርስቲያናዊ ምግባርን ከባርነት ግዴታነት አውጥቶ ወደ ነፃነት አገልግሎት ይለውጠዋል።

"በእምነት ብቻ" የሚለው መርሕ የክርስትና እምነት የቆመበት ወይም የሚወድቅበት አንቀጽ ነው። ይኽ መርሕ በጠፋበት ዘመን ሁሉ ቤተ ክርስቲያን ወደ ሕግተኝነትና ወደ ሰዋዊ ጥረት ባርነት ትመለሳለች። "በእምነት ብቻ" ለአማኙ የሚሰጠው የሕሊና ዕረፍት ወደር የለውም፤ ምክንያቱም መጽደቃችን በማይለወጠው የክርስቶስ ሥራ ላይ እንጂ በእኛ በሚዋዥቅ ማንነት ላይ የተመሠረተ አለመሆኑን ስለሚያረጋግጥ ነው። ይኽ መርሕ ዛሬም ድረስ እራሳቸውን በራሳቸው ለማጽደቅ ለሚደክሙ፣ በኃጢአት በደል ለተጨነቁና በኃይማኖታዊ ሥርዓቶች ለታከቱ ነፍሳት ሁሉ ብቸኛው የምስራች ነው። በአንድ በኩል መዳንን በሥራ ለማግኘት ከሚደረግ "ሕግተኝነት" (Legalism)፣ በሌላ በኩል ደግሞ እምነት አለኝ እያሉ በኃጢአት ከመመላለስም (Antinomianism) ይታደጋል። ክብርን ሁሉ ለእግዚአብሔር የሚሰጥ፣ ሰውን በትሕትና የሚያኖርና ለፍቅር አገልግሎት ኃይል የሚሆን ዘላለማዊ እውነት ነው።

5. "ለእግዚአብሔር ክብር ብቻ"

"ለእግዚአብሔር ክብር ብቻ" የሚለው መርሕ ከሌሎቹ አራት መርሖች የሚለየው፣ እርሱ የመዳን "መንገድ" ሳይሆን የመዳን "መጨረሻ" በመሆኑ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ብቻውን ባለሥልጣን የሆነው፣ ጸጋ ብቻውን ያዳነው፣ እምነት ብቻውን ያጸደቀውና ክርስቶስ ብቻውን መካከለኛ የሆነው ለምንድን ነው? ለሚለው ጥያቄ ምላሹ "ለእግዚአብሔር ክብር ብቻ" የሚል ነው። ይኽ መርሕ እግዚአብሔር ሰውን ያዳነው ሰውን ስላስፈለገው ወይም በሰው ውስጥ አንዳች የሚጎድለው ነገር ኖሮ ሳይሆን፣ የገዛ ራሱን ታላቅነት፣ ምሕረትና ጽድቅ ለፍጥረት ሁሉ ለመግለጥ መሆኑን ያስረግጣል። በሥነ-መለኮታዊ እይታ፣ መዳን "ሰው-ተኮር" (Anthropocentric) ሳይሆን "አምላክ-ተኮር" (Theocentric) ነው። ይኽም ማለት የሰው ልጅ መዳን ትልቁ ዓላማ የሰው ልጅ ደስተኛ መሆን ሳይሆን፣ የእግዚአብሔር ክብር መገለጥ ነው። ይኽ እውነት አማኙን ከራስ ወዳድነት መንፈሳዊነት አውጥቶ፣ አምልኮውንና ሕይወቱን በፈጣሪው ዙፋን ፊት እንዲያበረክት ያደርገዋል።

በተሐድሶው ዘመን የነበረው አንዱ ትልቅ መንፈሳዊ አብዮት፣ በ"መንፈሳዊ አገልግሎት" እና በ"ተራ ሕይወት" መካከል የነበረውን የሥልጣን ተዋረድ መስበሩ ነው። "ለእግዚአብሔር ክብር ብቻ" እንደሚያስተምረው፣ አንድ እናት ልጇን ስትንከባከብ፣ አንድ አናጺ ቤትን ሲሠራ ወይም አንድ ገበሬ መሬቱን ሲያርስ፣ ያንን ሥራ በእምነትና ለእግዚአብሔር ክብር ካደረገው፣ ልክ እንደ ቤተክርስቲያን ውስጥ እንደሚያገለግለው ያህል የተቀደሰ ተግባር ነው። ይኽ አስተሳሰብ "የአማኞች ሁሉ ክህነት" (Priesthood of All Believers) ከሚለው መርሕ ጋር የተያያዘ ነው። ማንኛውም የሰው ልጅ እንቅስቃሴ እግዚአብሔርን የማመስገኛ መድረክ ሊሆን ይችላል። ይኽ መርሕ በታሪክ ውስጥ ለሥራ ባህል ዕድገት፣ ለሳይንስና ለጥበብ መበልጸግ ትልቅ አስተዋጽኦ አድርጓል። ምክንያቱም አማኞች የሚሠሩት ሥራ ሁሉ በሰዎች ዘንድ ለመታየት ሳይሆን፣ በሰማይ ላለው አምላክ የሚቀርብ መሥዋዕት መሆኑን ስለተረዱ፣ በሥራቸው ሁሉ ጥራትንና ታማኝነትን እንዲፈልጉ አድርጓቸዋል።

በመካከለኛው ዘመን የነበረው ሥነ-መለኮት፣ ክብርን በእግዚአብሔርና በሰው መካከል የማከፋፈል አዝማሚያ ነበረው። "ሰው ጥቂት ይሠራል፣ እግዚአብሔር ደግሞ ቀሪውን ይሞላል" በሚል አስተሳሰብ፣ ምስጋናውም ለሰውና ለእግዚአብሔር እንዲከፈል ይደረግ ነበር። "ለእግዚአብሔር ክብር ብቻ" ግን ይኽንን በጽኑ ይቃወማል። መዳን "ብቻ"  በሚሉ መርሖች ላይ መቆሙ፣ ክብር ሁሉ ለእግዚአብሔር "ብቻ" እንዲሆን ያደርገዋል። ሐዋርያው ጳውሎስ በሮሜ 11፥36 ላይ "ሁሉ ከእርሱና በእርሱ ለእርሱም ነውና" ሲል፣ ሰው የራሱ የሆነ አንዳች ሊመካበት የሚችል ነገር እንደሌለው ያሳያል። እምነታችን ራሱ የእግዚአብሔር ስጦታ ከሆነ፣ የምንመካው በሰጪው እንጂ በተቀባዩ አይደለም። ይኽ መርሕ ቤተ ክርስቲያንን ከሰው አምልኮ፣ ከመሪዎች ግነትና ከኃይማኖታዊ ድርጅቶች ትምክህት ይጠብቃታል። ማንም ሰው ወይም ድርጅት የእግዚአብሔርን ክብር ለራሱ ሊወስድ እንደማይችልና ሁሉም በቃሉ ፊት እኩል ተገዢዎች መሆናቸውን ያውጃል።

ጆን ካልቪን ዓለምን "የእግዚአብሔር ክብር መድረክ (ቴአትር)" ብሎ መጥራቱ፣ አማኙ ለዓለም ሊኖረው የሚገባውን አመለካከት ይለውጠዋል። እግዚአብሔርን ለማክበር የግድ ከዓለም መለየት ወይም ወደ 'ገዳም' መሄድ አያስፈልግም (ሁሉም የራሴ የሚለው 'ገዳም' ይኖረዋል ብዬ ነው፤ ደግሞ 'ዳ'ን ላላ አድርገችሁ አንብቧት)። ይልቁንም፣ በእግዚአብሔር በተፈጠረው ዓለም ውስጥ ተሳታፊ በመሆን፣ የተሰጠንን ተፈጥሮና ጸጋ በመጠቀም፣ እግዚአብሔርን ማክበር ይቻላል። ይኽ መርሕ አማኙ በሥነ-ምግባሩ፣ በንግግሩና በማኅበራዊ ግንኙነቱ የእግዚአብሔርን ማንነት እንዲያንጸባርቅ ያበረታታል። "ለእግዚአብሔር ክብር ብቻ" ማለት እግዚአብሔር በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ብቻ ሳይሆን፣ በትምህርት ቤት ውስጥ፣ በገበያ ውስጥ፣ በፖለቲካው አደባባይና በቤተሰብ ሕይወት ውስጥ ንጉሥ መሆኑን ማወጅ ነው። ይኽ ሉዓላዊ እይታ አማኙን ለዓለም ብርሃንና ጨው እንዲሆን የሚያስችለው ታላቅ ኃይል ነው።

"ለእግዚአብሔር ክብር ብቻ" የሚለው መርሕ፣ የአምስቱን ብቻዎች ሕንፃ የሚያቆም የማዕዘን ድንጋይና ጣሪያ ነው። መጽሐፍ ቅዱስን የምናጠናው፣ በጸጋ የምንድነው፣ በእምነት የምንጸድቀውና በክርስቶስ የምንታመነው መጨረሻው ለእግዚአብሔር ክብር እንዲሆን ነው። ይኽ መርሕ ለሰው ልጅ እውነተኛውን ነፃነት ይሰጠዋል፤ ምክንያቱም የሰው ልጅ ትልቁ ደስታና እርካታ የሚገኘው የፈጠረውን አምላክ ሲያከብርና በእርሱም ለዘላለም ደስ ሲሰኝ ብቻ በመሆኑ ነው። "ለእግዚአብሔር ክብር ብቻ" የአማኙ የሕይወት መዝሙር፣ የቤተ ክርስቲያን የሥራ መመሪያና የፍጥረት ሁሉ የህልውና ምስጢር ነው።

እናጠቃለው - አምስቱ "ብቻዎች" ብቻቸውን ይጮሃሉ!

አምስቱ "ሶላዎች" (The Five Solas) ለብቻቸው የቆሙ የተነጣጠሉ ንድፈ ሐሳቦች ሳይሆኑ፣ አንዱ ከሌላው ጋር የተሳሰረና የወንጌልን ሙሉነት የሚገልጡ የወርቅ ሰንሰለቶች ናቸው። እነዚህ መርሖች በጋራ ሲቆሙ የክርስትናን እምነት ሕይወትና ትንፋሽ ይወክላሉ። "መጽሐፍ ቅዱስ ብቻ" የእምነታችንን መሠረትና የመጨረሻውን ሥልጣን ሲያሳየን፣ "በጸጋ ብቻ" የመዳናችንን መነሻና ምንጭ ይነግረናል። ይኽ ጸጋ በሕይወታችን ተግባራዊ የሚሆነው "በእምነት ብቻ" ሲሆን፣ የእነዚህ ሁሉ ማዕከልና ብቸኛ አምላካዊ መካከለኛ ደግሞ "በክርስቶስ ብቻ" ነው። በመጨረሻም የዚህ ሁሉ መለኮታዊ ክንውን ግብና መድረሻ "ለእግዚአብሔር ክብር ብቻ" ነው።

ይኽ የአምስቱ ብቻዎች ስብስብ ዛሬም ድረስ ለቤተ ክርስቲያን ተገቢና አስፈላጊ የሆነበት ምክንያት፣ የሰውን ልጅ ልብ ከእውነት የሚያርቁ አዳዲስ ወጎችና ፍልስፍናዎች በየዘመኑ ስለሚነሱ ነው። "ብቻ" የሚለው ቃል ዛሬም ሊሰመርበት ይገባል፤ ምክንያቱም ወንጌልን የሚያጠፋው መካድ ብቻ ሳይሆን፣ ከእግዚአብሔር ቃል ጎን ሌላ ሥልጣን፣ ከክርስቶስ ጎን ሌላ አዳኝ፣ ከጸጋ ጎን ሌላ የሰው ሥራ፣ እንዲሁም ከእግዚአብሔር ክብር ጎን የሰው ዝናን መጨመር ጭምር ነው። እነዚህ መርሖች አማኙን ከመንፈሳዊ ድንቁርናና ከኃይማኖታዊ ባርነት ነፃ አውጥተው፣ በእግዚአብሔር ፊት በልበ ሙሉነት እንዲቆም ያደርጉታል።

እነዚህን መሠረቶች ማጥናት ታዲያ የታሪክ ድርሳናትን መግለጥ ብቻ ሳይሆን፣ ዛሬም ድረስ ለቤተ ክርስቲያን ንጽሕናና ለወንጌል እውነተኝነት መቆም ማለት ነው። ቤተ ክርስቲያን "ሁልጊዜ ተሐድሶ የሚያስፈልጋት" እንደመሆኗ፣ ሕይወታችንን፣ አምልኮአችንንና አገልግሎታችንን ሁልጊዜ በእነዚህ አምስት ሚዛኖች መመዘን ይኖርብናል። ቃሉን መሠረት፣ ጸጋውን ኃይል፣ እምነትን መንገድ፣ ክርስቶስን መሪ፣ ክብሩን ደግሞ ግባችን አድርገን ስንጓዝ፣ ለዘመናችን ትውልድ የማይናወጥ መንፈሳዊ ቋጥኝ ሆነን እንቆማለን።

እነዚህ አምስት "ብቻዎች" ዝም ያሉ ንድፈ ሐሳቦች ሳይሆኑ፣ ዛሬም ድረስ በቤተ ክርስቲያን አደባባይና በሰው ልጅ ሕሊና ውስጥ የሚጣሩ፣ የተሳሳተውን የሚያርሙና የጠፋውን ወደ መሠረቱ የሚጠሩ ሕያው ድምፆች ናቸው።

መጽሐፍ ቅዱስ ይጮሃል "እግዚአብሔር እንዲህ ይላል!" እያለ። ይኽ ድምፅ የሰውን ልጅ ሥልጣን፣ 'የሊቃውንትን ግምት' ና የቤተ ክርስቲያንን 'ልማድ' ከዙፋኑ አውርዶ፣ መለኮታዊውን እስትንፋስ በበላይነት ያነግሣል። ቃሉ ይጮሃል፤ ምክንያቱም ከእርሱ ውጭ ያለው መንገድ ሁሉ ጭጋግ፣ መመሪያውም ሁሉ 'ስህተት' ስለሆነ ነው። "ሰማይና ምድር ያልፋሉ፥ ቃሌ ግን አያልፍም" የሚለው የክርስቶስ ድምፅ፣ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ዛሬም ድረስ ብቸኛውና የመጨረሻው ዳኛ ሆኖ ይጣራል።

ጸጋም ይጮሃል፤ ጩኸቱም "ያለ እኔ አንዳች ልታደርጉ አትችሉም!" የሚል ነው። ይኽ ድምፅ የሰውን ልጅ ብቃት፣ ጥረትና ሃይማኖታዊ ተጋድሎ ከንቱ ያደርጋል። ሰው በራሱ ጥረት ወደ ሰማይ ለመውጣት ለሚገነባው የባቢሎን ግንብ፣ ጸጋው "መዳን ስጦታ ነው!" በማለት ምላሽ ይሰጣል። ይኽ ጩኸት ኃጢአተኛውን ከራሱ ድካም አውጥቶ በእግዚአብሔር ቸርነት ላይ እንዲያርፍ ያደርገዋል። ጸጋው ሲጮህ፣ የሰው ልጅ መመኪያ ድምፅ ሁሉ ጸጥ ይላል።

እምነትም ይጮሃል፤ "እመኑና ጽደቁ!" የሚል ጥሪን ያስተጋባል። ይኽ ጩኸት ሕግና ሥርዓትን በመፈጸም ጽድቅን ለመግዛት ለሚደክም ልብ "ተፈጸመ!" የሚል የዕረፍት ድምፅ ነው። እምነት የሚጮኸው ስለራሱ ብቃት ሳይሆን ስለሚይዘው ክርስቶስ ፍጹምነት ነው። በሥራ በሚመካው ዓለም ውስጥ፣ እምነት "በእግዚአብሔር ፊት የምትቆሙት በጸጋው ተቀብላችሁ እንጂ በሥራችሁ አይደለም" በማለት የሕሊናን ሰላም ያውጃል።

ክርስቶስ ይጮሃል፤ "መንገዱና እውነቱ ሕይወቱም እኔ ነኝ" ይላል። ይኽ ጩኸት በሰውና በእግዚአብሔር መካከል የቆሙትን የቅዱሳን፣ የሥርዓቶችና የሰዋዊ 'ክህነቶችን' ድልድይ ሁሉ ያፈርሳል። ክርስቶስ ብቸኛው መካከለኛ ሆኖ ሲጣራ፣ ሌላ አዳኝ፣ ሌላ አማላጅና ሌላ መሸሸጊያ እንደማያስፈልግ ግልጽ ይሆናል። በመስቀል ላይ የፈሰሰው ደም ድምፅ፣ ከማንኛውም ሰዋዊ ጽድቅ ይልቅ እጅግ አጥብቆ ይጮሃል።

የእግዚአብሔር ክብር ይጮሃል፤ ጩኸቱም "ምስጋና ሁሉ ለእኔ ይሁን!" የሚል ነው። ይኽ ድምፅ የሰውን ልጅ ራስን ወይም ከእግዚአብሔርጨውጪ ያለን ነገር የማምለክ እና ዝናን የመፈለግ አባዜን ይሰብራል። ፍጥረት ሁሉ፣ መዳንም ሆነ ቅድስና ለፈጣሪው ክብር እንዲሆን ይጣራል። ይኽ ጩኸት ሕይወታችንን ከመሬት አንስቶ ወደ ሰማያዊው ዙፋን ያደርሰዋል፤ ሰውን ከራሱ አውጥቶ ለእግዚአብሔር ታላቅነት እንዲገዛ ያደርገዋል።

እነዚህ አምስት ጩኸቶች ዛሬም አየሩን ሞልተውታል። 'ብቻዎቹ' ብቻቸውን ይጮሃሉ፤ እውነት ተባባሪ አያስፈልገውምና። ቃሉ ብርሃን ነው፣ ጸጋው መዳን ነው፣ እምነቱ መንገድ ነው፣ ክርስቶስ ሕይወት ነው፣ ክብሩ ደግሞ ግብ ነው። ይኽንን ጩኸት የሚሰማ ሕሊና ከዘላለም ሞት አምልጦ ወደ ዘላለም ሕይወት ይሻገራል።

የጌታ ኢየሱስ ጸጋና ሰላም ምህረትም ይብዛላችሁ!

እኛ አገራችን በሰማይ ነውና

 “እኛ አገራችን በሰማይ ነውና፥ ከዚያም ደግሞ የሚመጣ መድኃኒትን እርሱንም ጌታን ኢየሱስ ክርስቶስን እንጠባበቃለን፤”  (ፊል. 3፥20)


የሰው ልጅ በታሪኩ ሂደት ውስጥ ዘላቂ መኖሪያን ፍለጋ ብዙ ደክሟል፤ ብዙ ግዛቶችንም መስርቷል። ነገር ግን በጊዜ ማዕበል የማይናወጥ፣ በሞት ጽዋ የማይመረዝ እውነተኛ ማንነትና መጠለያ ማግኘት ከቶ አልተቻለውም። በዚኽ የምድራዊ ታሪክ ውዝግብና የባዕድነት ስሜት መሃል፣ ሐዋርያው ጳውሎስ የመንፈስ ቅዱስን ብዕር አንስቶ በፊልጵስዩስ 3፥20 ላይ ታላቅ ሰማያዊ መፈክር ያውጃል። “እኛ አገራችን በሰማይ ነውና፥ ከዚያም ደግሞ የሚመጣ መድኃኒትን እርሱንም ጌታን ኢየሱስ ክርስቶስን እንጠባበቃለን፤” በማለት የሚናገረው ቃል፣ የክርስቲያናዊ ማንነትን ጥልቅ መሠረትና የሕይወትን አቅጣጫ የሚወሰን፤ አሮጌውን ምድራዊ ማንነት አርቆ የሚጥልና አዲሱን ሰማያዊ ሕላዌ የሚቀዳጅ ሰማያዊ አዋጅ ነው።

“አገራችን” በግሪክ ቋንቋ “ፖሊቲውማ” (politeuma) በሚለው ቃል ሲገለጽ፣ ትርጉሙም ተራ “መኖሪያ” ማለት ብቻ ሳይሆን “ዜግነት”፣ “የመንግሥት አስተዳደር” ወይም “የሕዝብ ማኅበረሰብ” የሚሉትን ጽንሰ-ሐሳቦች ያጠቃልላል። በወቅቱ ፊልጵስዩስ የሮም ቅኝ ግዛት እንደመሆኗ መጠን፣ ነዋሪዎቿ ከሮም ከተማ ርቀው ቢኖሩም የሮም ዜጎች እንደሆኑና የሮምን ሕግ እንደሚያከብሩ ሁሉ፣ አማኝም በዚህ ምድር ላይ በእንግድነትና በመጻተኝነት እየኖረ ዋናውና እውነተኛው ዜግነቱ ግን ሰማያዊ መሆኑን በመንገር የክርስቲያን መሠረታዊ የሕይወት መመሪያ ከዚህ ዓለም ፖለቲካዊና ፍልስፍናዊ ሥርዓት የወጣ መሆኑን ሐዋርያው ያስገነዝባል። የእኛ “ፖሊቲውማ” ወይም የመንግሥት አስተዳደር በሰማይ ነው ሲል፣ በምድር ላይ ስንኖር የምንመራው በሰማያዊ ሥነ-ምግባር፣ በሰማያዊ ፍቅርና በሰማያዊ ጽድቅ መሆኑን ማሳሰቡ ነው። ይኽ ዜግነት በመሬት ዳርቻ ወይም በደም ሐረግ የሚወሰን ሳይሆን፣ በክርስቶስ ኢየሱስ ደም የተገዛና በትንሣኤው ኃይል የጸና ነው። ስለሆነም፣ አማኙ በዓለም ውስጥ ቢኖርም የዓለም አይደለም፤ ልቡ በሰማይ የታሰረ፣ ናፍቆቱ ከመለኮት ጋር የተሳሰረ፣ ሕይወቱም ከክርስቶስ ጋር በእግዚአብሔር ዘንድ የተሰወረ ነው። ይኽ ዜግነት በወረቀት ላይ የሚሰፍር ተራ መታወቂያ ሳይሆን፣ የአስተሳሰባችን፣ የሥነ-ምግባራችንና የናፍቆታችን ማዕከል ከዚህ ከሚጠፋው ዓለም ሥርዓት ወጥቶ በማይናወጠው የእግዚአብሔር መንግሥት ላይ እንዲመሠረት የሚያደርግ መንፈሳዊ ኃይል ነው። ይኽ ዜግነት በምድራዊ መዝገብ ላይ የሰፈረ ሳይሆን፣ በበጉ የሕይወት መጽሐፍ ላይ በደም የተጻፈ የማይሻር ሰነድ ነው።

ይኽ ሰማያዊ ዜግነት የሚጠይቀው የአኗኗር ዘይቤ፣ የናፍቆትና የትኩረት አቅጣጫን ማስተካከል ነው። በቆላስይስ 3፥1-2 ላይ እንደተጻፈው “ክርስቶስ ባለበት በላይ ያለውን እሹ፤ በላይ ያለውን አስቡ እንጂ በምድር ያለውን አይደለም” የሚለው መመሪያ፣ የዜግነታችን ተግባራዊ መግለጫ ነው። እውነተኛው ማንነቱ በሰማይ የሆነ ሰው፣ በዚህ ምድር ላይ ለሚታየውና ለሚጠፋው ነገር አይንበረከክም። ይልቁንም፣ አብርሃም “መሠረት ያላትንና እግዚአብሔር የሠራትን ከተማ” እንደጠበቀ (ዕብራውያን 11፥10)፣ እኛም ዛሬ በዚህች ዓለም ውስጥ እንደ እንግዳና እንደ መጻተኛ ስንመላለስ፣ ልባችን ግን የዘላለም ንጉሥ ባለበት ዙፋን ስር ያርፋል። ይኽ ግንዛቤ በውስጣችን ያለውን የፍርሃት ሰንሰለት ይሰብራል፤ ምክንያቱም የዚህ ዓለም ገዥዎች ሊወስዱት የማይችሉት፣ ሞትም ሊያጠፋው የማይችለው የማይደፈር ሰማያዊ መታወቂያ አለን። እኛ በዚህ ዓለም ላይ ስንኖር በ2ኛ ቆሮንቶስ 5፥20 ላይ እንደተጠቀሰው “የክርስቶስ እንደራሴዎች” እንጂ ተራ ተገዢዎች አይደለንም።

በዚህ ጥቅስ ውስጥ የሚገኘው ሁለተኛውና እጅግ አስደሳች የሆነው እውነት “መጠበቅ” የሚለው ቃል ነው። እዚህ ላይ ጥቅም ላይ የዋለው የግሪክ ቃል “አፔክዴኮማይ” (apekdechomai) የሚል ሲሆን፣ ይኽ ቃል በታላቅ ጉጉት፣ አንገትን አቅንቶ፣ ዓይንን ካሰቡት አካል ላይ ሳይነቅሉ የሚደረግ ጥበቃን ያመለክታል። እኛ የምንጠብቀው ጽንሰ-ሐሳብን ሳይሆን “መድኃኒትን” ነው፤ እርሱም ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። ይኽ ጥበቃ በውስጡ ታላቅ ኃይል አለው፤ ምክንያቱም የሚመጣው መድኃኒት ሞትን የረገጠ፣ ሰይጣንን ድል የነሳና የክብር ንጉሥ በመሆኑ ነው። አማኙ በዚህ ዓለም ላይ ለሚገጥመው ማናቸውም ዓይነት ግፍ፣ መከራና ውድቀት መልሱ ያለው በዚህ “ጥበቃ” ውስጥ ነው። ይኽ ተስፋ በታሪክ አጋጣሚዎች የሚናወጥ ሳይሆን፣ በዘላለም ቃል ላይ የተመሠረተ ጽኑ መልሕቅ ነው። በየቀኑ የምንተነፍሰው አየር ሰማያዊውን መዓዛ የሚሸት ሊሆን የሚገባው፣ የምንጠብቀው ጌታ በማንኛውም ቅጽበት ሊገለጥ እንደሚችል ስለምናምን ነው።

ይኽ የፊልጵስዩስ ቃል የሕይወታችን መሪ ቃል ሊሆን ይገባል! እኛ የዚህ ዓለም ተረፈ-ምርቶች ሳንሆን፣ የሰማያዊው አምላክ ወራሾችና ከክርስቶስ ጋር አብረን የምንነግሥ ቅዱሳን ነን። ምድር በትከሻችን ላይ ሸክም ብታበዛብንም፣ ሰማይ ግን የክብር ዘውድ አዘጋጅቶልናል። ምድር ለጊዜው እንግዳ ብታደርገንም፣ ሰማይ ግን እንደ ዋና ዜጋ በክብር ይጠብቀናል። ይኽ እውነት በውስጣችን የእሳት ነበልባል ሆኖ ሊነድድ ይገባል፤ ይኽም ነበልባል የምድራዊነትን ሰንሰለት የሚበጥስ፣ ከኃጢአት ግዞት ነፃ የሚያወጣና ለዘለዓለማዊው ክብር የሚያዘጋጅ መሆን አለበት። መድኃኒታችን ክርስቶስ ሲገለጥ፣ በውርደት ያለው ሥጋችን ተለውጦ የእርሱን የክብር ሥጋ እንዲመስል ያደርጋል (ፊል. 3፥21)።

ስለዚህ፣ ዛሬ በምድር ላይ ስንመላለስ እንደ ሰማይ ዜጎች በግርማ፣ በቅድስናና በማይናወጥ ተስፋ እንኑር። ዓለምን የምናሸንፈው በዜግነታችን ከፍታ እንጂ በምድራዊ ጥበባችን አይደለም፤ ምክንያቱም እውነተኛው ቤታችን፣ ዘላለማዊው ፋኖሳችንና የክብራችን ዘውድ ያለው እዚያ በማይለወጠው ሰማያዊ ግዛት ውስጥ ነውና! ፊታችንን ወደ ሰማይ አቅንተን፣ ልባችንን በቃሉ አጽንተን፣ የመድኃኒታችንን የክርስቶስን መገለጥ በናፍቆት እንጠባበቅ። የዚህ ዓለም ጥላ ሲያልፍ፣ እውነተኛው የክብር ፀሐይ ይወጣል፤ ያኔ ዜግነታችን በተሟላ ግርማ ይገለጣል፣ እኛም ከዘላለም ንጉሥ ጋር ለዘላለም በክብር እንነግሣለን! ማራናታ፣ ጌታ ኢየሱስ ሆይ ና!

“የተስፋ አምላክም በመንፈስ ቅዱስ ኃይል በተስፋ እንድትበዙ በማመናችሁ ደስታንና ሰላምን ሁሉ ይሙላባችሁ።” (ሮሜ 15፥13)

Tuesday, January 6, 2026

 በደም የተከተበ ምስክርነት


የቀደሙት አባቶችና እናቶች ክርስቲያን በመሆናቸው ብቻ ያለፉበት የመከራ እቶን፣ ለዛሬዋ ቤተ ክርስቲያን የጸና መሠረትና የሕይወት ዘር የሆነ ታላቅ ታሪክ ነው። በጥንቷ ሮም ስደት በበረታበት ዘመን፣ ክርስትናን መምረጥ ማለት ሞትን እንደ ጓደኛ መቅጠር ማለት ነበር። እነዚያ ቅዱሳን ግን ከምድራዊው ሰላም ይልቅ ሰማያዊውን አክሊል በመናፈቅ፣ በደማቸው የታተመ የጽናት ምስክርነትን ጥለውልን አልፈዋል።

በመጀመሪያዎቹ ሦስት መቶ ዓመታት፣ ክርስቲያኖች በሮማውያን ነገሥታት ዘንድ እንደ መንግሥት ጠላት ይታዩ ነበር። ምክንያቱም 'ጌታችን ቄሣር ነው' ብለው ለመናገር ባለመፍቀዳቸውና ለሮም አማልክት ባለመስገዳቸው ነው። በዚህም ምክንያት በታሪክ መጻሕፍት ውስጥ የሚዘገንኑና ልብን የሚሰብሩ መከራዎች በእነርሱ ላይ ደርሰዋል፤ ለአራዊት ተጥለዋል፣ በእሳት ተቃጥለዋል፣ እንዲሁም በሰይፍ ተሰይፈዋል። በተለይም በኔሮን፣ በዲዮቅልጥያኖስና በዶሜጥያኖስ ዘመን ደማቸው እንደ ውኃ ፈስሷል። ይኽ ሁሉ መከራ ግን አስቀድሞ በጌታ የተነገረ ነበር፣ “በዓለም ሳላችሁ መከራ አለባችሁ፤ ነገር ግን አይዞአችሁ፤ እኔ ዓለምን አሸንፌዋለሁ” (ዮሐ. 16፥33)። የሚያስደንቀው እውነታ መከራው በበዛ ቁጥር የክርስቲያኖች ቁጥር ይበልጥ መጨመሩ ነው። ታላቁ የቤተ ክርስቲያን አባት ተርቱሊያን እንደተናገረው፣ “የሰማዕታት ደም ለቤተ ክርስቲያን ዘር ነው”፤ አንዱ ሲሞት አሥሩ ይተኩ ነበር። ምንአልባት ይኽ ጠፍቶ ይሆን የምንበዛበት ፍጥነት 'እንደእንትን' ቀስ ያለው።

እነዚህ ቅዱሳን መከራውን የተቀበሉት በለቅሶ ሳይሆን በዝማሬና በደስታ ነበር። እንደ ቅዱስ ፖሊካርፕ ያሉ አባቶች በእሳት ሊቃጠሉ ሲሉ፣ “ለሰማንያ ስድስት ዓመታት አገለገልኩት፤ እርሱም ክፉ አላደረገብኝም፤ ታዲያ እንዴት አምላኬንና አዳኜን እክዳለሁ?” በማለት ለሞት ሳይንበረከኩ ለክርስቶስ ያላቸውን ፍቅር አሳይተዋል። ሴቶችና ሕፃናት እንኳ ሳይቀሩ “ክርስቶስን ክዱ” ሲባሉ፣ በመስቀል ላይ የፈሰሰውን ፍቅር እያሰቡ አንገታቸውን ለሰይፍ ይሰጡ ነበር። ይህ ጽናት የመጣው ከራሳቸው ኃይል ሳይሆን፣ “የክርስቶስ ሥቃይ በእኛ ላይ እንደ በዛ፥ እንዲሁ መጽናናታችን ደግሞ በክርስቶስ በኩል ይበዛልናልና” (2ቆሮ. 1፥5) እንደሚለው ቃሉ፣በመከራው መካከል አብሯቸው ከቆመውና ሸክማቸውን ካቀለላቸው ከመንፈስ ቅዱስ ረዳትነት ነው።

በዚያ የስደት ዘመን፣ ክርስቲያኖች መኖሪያቸው በምድር ላይ አልነበረም። ስደት ሲበረታባቸው “ካታኮምብ” (Catacombs) ወደተባሉ ከመሬት በታች ያሉ ጠባብ ዋሻዎችና የመቃብር ስፍራዎች ተሰደዋል። በዚያ ጨለማ ውስጥ ሆነው ያመልኩ፣ ይጸልዩና ይማሩ ነበር። “ዓለም አልተገባቸውምና በምድረ በዳና በተራራ፥ በዋሻና በምድር ጕድጓድ ተቅበዘበዙ (ተንከራተቱ)” (ዕብ. 11፥38) ተብሎ እንደተጻፈው፣ በዚያ የጭንቅ ወቅት ነበር እንደ 'ዓሣ' (Ichthys) ያሉ ሚስጥራዊ ምልክቶችን በመጠቀም አንዱ ሌላውን የሚያውቀው (በዚኽ ምልክት ዙሪያ ሰፋ ባለ መልኩ እመለስበታለሁ)። ዛሬ የምንጠቀምባቸው ታላላቅ የነገረ መለኮት ትምህርቶችና የጸሎት ሥርዓቶች የተወለዱት በእንደዚህ ዓይነት መከራና ስደት ውስጥ ሆነው አባቶች በጠበቁት እምነት ነው።

ዛሬ እኛ ያለ ምንም ስጋት በነፃነት ስናመልክ፣ የእነዚያን ቅዱሳን መስዋዕትነት ማሰብ ይኖርብናል። የቀደሙት አባቶች መከራውን የታገሱት ለጊዜያዊ ጥቅም ሳይሆን ለዘላለማዊ ክብር ነው። የእነርሱ ጽናት ዛሬም ለእኛ ታላቅ ትምህርት ነው፤ ዓለም ብትጠላንም፣ መከራ ቢበዛብንም፣ በክርስቶስ ያለን ተስፋ ግን የማይናወጥ መሆኑን ያሳዩናል። እምነት ዋጋ እንደሚያስከፍል፣ ያ ዋጋም ወደማይጠፋ የሕይወት አክሊል (ያዕ. 1፥12፤ ራዕ. 2፥10) እንደሚያደርስ የእነርሱ ሕይወት ሕያው ምስክር ነው።

“በፈተና የሚጸና ሰው የተባረከ ነው፤ ከተፈተነ በኋላ ለሚወዱት ተስፋ ስለ እርሱ የሰጣቸውን የሕይወትን አክሊል ይቀበላልና።” (ያዕ. 1፥12) 

“ልትቀበለው ያለህን መከራ አትፍራ . . . እስከሞት ድረስ የታመንህ ሁን የሕይወትንም አክሊል እሰጥሃለሁ።” (ራዕ. 2፥10)
 
ዛሬ ላይ ክርስትናን የሃብት ማካበቻ ሲደረግ ማየቱ እጅግ ያማል፤ አባቶቻችን በደማቸው የገነቧት ቤተ ክርስቲያን ዛሬ ላይ የንግድ መድረክ ስትሆን ማየት የሕሊና ቁስል ነው፤ አባቶቻችን ስለ እውነት አንገታቸውን ለሰይፍ በሰጡበት በዚያ ቅዱስ ስፍራ፣ ዛሬ ስለ ምድራዊ ብልጽግና ብቻ የሚጮኹ ድምፆች መብዛታቸው ልብ ይሰብራል። የቀደሙት ቅዱሳን "መስቀሌን ተሸክሜ እከተልሃለሁ" ብለው የክርስቶስን መከራ ሲካፈሉ፣ ዛሬ ግን መስቀሉን ጥለው "እንዴት ባለጸጋ እሆናለሁ?" በሚል ስስት ተጠምደዋል። መስቀሉን ተሸክሞ መከተል ቀርቶ፣ መስቀሉን ለምድራዊ ጥቅም መሸከሚያ ማድረግ የተለመደ ሆኗል። ቅዱስ ጳውሎስ “ብዙዎች ለክርስቶስ መስቀል ጠላቶቹ ሆነው ይመላለሳሉ . . . ሆዳቸው አምላካቸው ነው፥ ክብራቸው በነውራቸው ነው፥ አሳባቸውም ምድራዊ ነው” (ፊል. 3፥18-19) በማለት የተነገረው ቃል ዛሬ በዓይናችን ፊት ሲፈጸም ይታያል። የቀደሙት ቅዱሳን “ስለ ክርስቶስ ሁሉን አጣሁ” ሲሉ፣ ዛሬ ላይ ግን “በክርስቶስ ስም ሁሉን አከማቸሁ” የሚሉ ድምፆች እንዴት እንበዙ። ጳውሎስ አሁንም “አእምሮአቸውም በጠፋባቸው እውነትንም በተቀሙ፥ እግዚአብሔርን መምሰል ማትረፊያ የሚሆን በመሰላቸው” (1ጢሞ. 6፥5) ሲል የገለጻቸው ሰዎች ዓይነት ዛሬ ላይ በዝተዋል። ዛሬ ላይ ሰማዕትነት በምቾት፣ ጽናትም በጥቅም ተተክቷል። ጥንት ክርስቲያኖች ወደ አናብስት ጉድጓድ ሲወረወሩ ስለ እምነታቸው ይዘምሩ ነበር፤ ዛሬ ላይ ግን ጥቅማችን በትንሹ ሲነካ እምነታችንን ለመሸጥ አንሰቀስቅም። “ገንዘብን መውደድ የክፉት ሁሉ ሥር ነውና” (1ጢሞ. 6፥10) የሚለው ቃል ዛሬ ላይ በብዙዎች ሕይወት ውስጥ በተግባር እየታየ ነው። ዛሬ ላይ ወንጌል ሰውን ወደ ሰማይ የሚያስገባ የሕይወት መንገድ መሆኑ ቀርቶ፣ ምድር ላይ እንዴት ባለጸጋ መሆን እንደሚቻል የሚመከርበት 'የስኬት ጥበብ' ተደርጎ ተወስዷል። አባቶች በጨለማ ዋሻ ውስጥ ሆነው የሰማይን ብርሃን ያዩ ነበር፤ ዛሬ ላይ ግን በኤሌክትሪክ መብራት በደመቁ አዳራሾች ውስጥ ሆነን የውስጥ ጨለማችንን ማሸነፍ አቅቶናል። በካታኮምብ (ዋሻ) ውስጥ ሆነው በጨለማ የሚያበሩት ቅዱሳን፣ ለነፍሳቸው እንጂ ለሥጋቸው አልተጨነቁም ነበር። ዛሬ ግን በዘመናዊ ሕንጻዎችና በድምቀት ውስጥ ሆነን፣ የውስጥ ማንነታችን ግን በመንፈሳዊ ድርቅ ተመቷል። ጌታችን “ሰው ዓለሙን ሁሉ ቢያተርፍ ነፍሱንም ቢያጐድል ምን ይጠቅመዋል?” (ማቴ. 16፥26) ያለውን መሠረታዊ ጥያቄ ዘንግተን በምድራዊው ሩጫ ተጠምደናል። 'ሰው' ብቻ ሆነናል። ዛሬ ላይ ለሰማያዊው አክሊል ከመጨነቅ ይልቅ ለምድራዊው ዝና የምንሮጥበት ፍጥነት ያስፈራል። “ዓለምን ወይም በዓለም ያሉትን አትውደዱ” (1ዮሐ. 2፥15) የሚለው መለኮታዊ ትእዛዝ በስልጣንና በንብረት ፍቅር ተውጧል። ወንጌል በነጻ የተሰጠ የሕይወት ስጦታ ሆኖ ሳለ፣ ዛሬ ግን እንደ ሸቀጥ ለሽያጭና ለትርፍ መገኛ ሲውል ማየት እጅግ ያሳዝናል። የጥንቶቹ አባቶች የክርስቶስን ፍቅር በደማቸው ሲመሰክሩ፣ ዛሬ ግን ብዙዎች  ክርስትናን "መሰላል" በማድረግ ለዝናና ለሥልጣን መውጫ ሲጠቀሙበት ይታያል። ዛሬ ግን በከንቱ ጩኸትና በተስፋ ቃል ሽያጭ የሰውን ልብ የሚያደነዝዙ በዝተዋል። ሰዎች ራሳቸውን የሚወዱ ይሆናሉና፥ ገንዘብን የሚወዱ፥ ትምክህተኞች፥ ትዕቢተኞች፥ ተሳዳቢዎች፥ ለወላጆቻቸው የማይታዘዙ፥ የማያመሰግኑ፥ ቅድስና የሌላቸው፥ ፍቅር የሌላቸው፥ ዕርቅን የማይሰሙ፥ ሐሜተኞች፥ ራሳቸውን የማይገዙ፥ ጨካኞች፥ መልካም የሆነውን የማይወዱ፥ ከዳተኞች፥ ችኩሎች፥ በትዕቢት የተነፉ፥ ከእግዚአብሔር ይልቅ ተድላን የሚወዱ ይሆናሉ፤” (2ጢሞ. 3፥2-4) ተብሎ የተጻፈው የስህተት ዘመን ላይ መሆናችን እርግጥ ነው።

ስለዚህ ዛሬ ላይ ቆመን ወደኋላ መመልከት ያስፈልገናል። የአባቶቻችንን የጽናት መንገድ ትተን በስስት መንገድ ላይ የምንጓዝ ከሆነ፣ ስማችን ክርስቲያን ቢባልም መንፈሳችን ግን ከጥንቶቹ አማኞች፣ ቅዱሳንና ሰማዕታት ጋር ዝምድና አይኖረውም። እግዚአብሔር ያን የጽናት መንፈስ ለእኛም ይስጠን። በመከራ ውስጥ የሚገኝ ደስታን፣ በሞት ፊት የማይደነግጥ እምነትን ተምረን ለክብሩ እንድንቆም ጸጋው ይርዳን።

የጌታ ሰላም ለሁላችሁ ይሁን!

ያልተቀደሰ ጥማት

በዚኽ በሩጫና በውጥረት በናወዘ ዓለም ውስጥ ሁላችንም አንድ የጋራ ምስጢር አለን፤ እርሱም 'ጥማት' ነው። የተሻለ ሥራ ስናገኝ፣ የሚያምር ቤት ስንሠራ፣ ዝናና እውቅናን ስንጎናጸፍ 'ጥማታችን' የሚያበቃ ይመስለን ይሆናል። ነገር ግን ድል ባደረግን ቁጥር ውስጣችን "ገና ነው፣ አልሞላም" የሚል ባዶነት ይጮኻል። ይኽ ባዶነት የቁሳቁስ እጥረት ሳይሆን፣ የነፍስ ርሃብ ነው። የሰው ልጅ የተፈጠረው ከምድር ቢሆንም፣ በውስጡ ግን ሰማያዊ 'ጥማት' ተተክሏል። ይኽን ጥማት ደግሞ በምድራዊ መጠጥ ለማርካት መሞከር የባዶነት ትልቁ ምክንያት ነው።


በዮሐንስ ወንጌል ምዕራፍ 4 ላይ የምናገኛት ሳምራዊቷ ሴት፣ የዘመናችን ወጣትና ጎልማሳ ትክክለኛ ምሳሌ ናት። እርሷም እንደ እኛ ደስታን ፍለጋ ብዙ ደጅ ጠንታለች፤ ብዙ "የጉድጓድ ውኃዎችን" ቀድታለች። ነገር ግን ጌታ ኢየሱስ በጉድጓዱ አጠገብ አግኝቶ እንዲህ አላት፦ "ከዚህ ውኃ የሚጠጣ ሁሉ እንደገና ይጠማል፤ እኔ ከምሰጠው ውኃ የሚጠጣ ሁሉ ግን ለዘላለም አይጠማም" (ዮሐ. 4፥13-14)።

ዛሬም ዓለም የምታቀርብልን 'ውኃ' (ገንዘብ፣ ሥልጣን፣ ሱስ፣ ጊዜያዊ ደስታ) ለጥቂት ጊዜ ያደነዝዘን ይሆናል እንጂ ጥማታችንን አይቆርጥም። ዓለማዊ ስኬት ጨው እንደተቀላቀለበት ውኃ ነው፤ በጠጣነው ቁጥር ይበልጥ ያስጠማናል፣ አያረካንም።

ታላቁ የሥነ-መለኮት ሊቅ አውግስጢኖስ (Augustine of Hippo) Confessions በተሰኘው መጽሐፉ የመጀመሪያው ምዕራፍ የመጀመሪያው አንቀጽ ላይ፣ "አቤቱ ለራስህ ፈጠርኸን፣ ልባችንም በአንተ ውስጥ እስካላረፈ ድረስ ሰላም(ዕረፍትን) አያገኝም" በማለት ተናግሮ ነበር። በልባችን ውስጥ እግዚአብሔር ብቻ ሊሞላው የሚችል አንድ ክፍተት አለ። ይኽን ክፍተት በሰው፣ በንብረት ወይም በዝና ለመሙላት መሞከር ባዶ ቅርጫት ውስጥ ውኃ የመቅዳት ያህል ነው። ጎልማሳው በሥራው ስኬት ውስጥ፣ ወጣቱ በቴክኖሎጂና በዝነኝነት ውስጥ የሚፈልገው ያ ባዶነት፣ በእውነቱ ያለበት የፈጣሪ ናፍቆት ነው። ነፍሳችን የጠፋችበትን ቤት እየፈለገች ነው፤ ያ ቤት ደግሞ ክርስቶስ ነው።

መመለስ የሚጀምረው 'ጎድሎኛል' ብሎ ከማመን ነው። በገዛ ጥረታችን ሰላምን ለመፍጠር የምናደርገው ሩጫ ደክሞናል? ነፍሳችን በኃጢአትና በዓለም ጭንቀት ዝላለች? ጌታ ዛሬም በታላቅ ድምፅ "ማንም የተጠማ ቢኖር ወደ እኔ ይምጣና ይጠጣ" (ዮሐ. 7፥37) ይለናል። ኢየሱስን መከተል 'ኃይማኖታዊ' ግዴታ ሳይሆን፣ ከተጠማንበት በረሃ ወደ ሕይወት ወንዝ መሻገር ነው። እርሱ የሚሰጠን ሰላም ዓለም እንደሚሰጠው አይደለም፤ የማይለወጥ፣ የማይጠፋና የማይሰረቅ ሰላም ነው።

ወዳጄ ሆይ! የልብህን ባዶነት በጊዜያዊ ነገሮች ለመሸፈን አትታገል፤ ጥማትህ የእግዚአብሔር ጥሪ ነው። ይኽ ጥሪ ወደ ቀደመው ማንነትህ፣ ወደ ፈጣሪህ ፍቅርና ወደ እውነተኛው ዕረፍት እንድትመለስ የሚጋብዝህ የሰማይ ድምፅ ነው። ዛሬም ጌታ በልብህ ደጅ ቆሞ ያንኳኳል፤ የልብህን በር ከከፈትክለት እርሱ ይገባል፣ የጎደለውንም ማንነትህን ሞልቶ የተረፈ ሕይወት ይሰጥሃል። ባዶነትህን ወደ ሙላት፣ ጥማትህን ወደ ዕርካታ ለመለወጥ ኢየሱስ ዛሬም ታማኝ ነው። ወደ እርሱ ተመለስ፤ እውነተኛው ሕይወት እርሱ ነውና!

እግዚአብሔር በዓለም ሩጫ የዛሉ ነፍሶቻችንን ወደ ራሱ ይመልስ፤ የልባችንንም ጥማት በማይጠፋው ፍቅሩ ያርካው! ከንቱውን ትተን ዘላለማዊውን እንድንይዝ ጸጋው ይርዳን!

የጌታ ኢየሱስ ዕረፍት ይብዛላችሁ!

https://t.me/anidSew

ክርስትና በመስቀል እንጂ 'በኪስ' አይለካም፤ በቃ አይለካም!

'አውቃለሁ' በሚል ትዕቢት ውስጥ የታሰረ ልብ፣ አዲስ እውነትን ለመቀበልም ሆነ የቆመበትን ስህተት ለመረዳት ይቸገራል። 'ለብዙ ዓመታት አስተምሬያለሁ' ወይም 'አባቶቼ ሰብከውታል' የሚለው መመኪያ፣ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ዕውቀትን ሳይሆን ሃይማኖታዊ ኩራትን ነው የሚገልጸው። ይሁን እንጂ፣ መጽሐፍ ቅዱስን ማወቅ ማለት ቁጥሩንና ምዕራፉን መጥቀስ ሳይሆን፣ የመስቀሉን ቃል በተግባር መኖር ነው። ብዙዎች ስለ ክርስቶስ ቢሰብኩም፣ ክርስቶስን ግን በሕይወታቸው አያውቁትም፤ አንዳንዴም የረሱት ይመስላል።

ዛሬ ላይ 'ድህነት የክርስትና መገለጫ አይደለም' የሚሉ ድምፆች ሲበዙ መስማት ልብን ይሰብራል። ይኽ አባባል የመጽሐፍ ቅዱስን ገጽ ገልጦ ያላነበበ፣ ያነበበ እንኳ ቢሆን ከምድራዊ ነገር ጋር የተጋባ፣ የመስቀሉን ምስጢር ያልተረዳና የአባቶችን የጽናት ታሪክ የዘነጋ ትውልድ ጩኸት ነው። ክርስትና የሚለካው በባንክ ደብተር ሳይሆን በልብ ቅድስና ነው፤ ክርስትና የሚለካው በምቾት ሳይሆን በመከራ ውስጥ በሚገኝ ጽናት ነው። ድህነትን የውድቀት ምልክት አድርገው የሚሰብኩ ሰዎች፣ ጌታቸው ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱ 'ራሱን የሚያሳርፍበት ማሳረፊያ የሌለው' ድሃ ሆኖ መመላለሱን እንዴት ዘነጉት? ደሞ'ኮ ጌታ 'ደሃ' አልነበረም ሲሉም አይሸማቀቁም።

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደዚህ ዓለም ሲመጣ የተወለደው በቤተ መንግሥት ሳይሆን በከብቶች በረት ውስጥ ነው። የሰማይና የምድር ጌታ ሆኖ ሳለ፣ ለእኛ ሲል ድሃ ሆነ። ሐዋርያው ጳውሎስም "እስከዚህ ሰዓት ድረስ እንራባለን፥ እንጠማለን፥ እንራቆታለን... ሲሰድቡን እንመርቃለን" (1ቆሮ. 4፥11-12) በማለት የሐዋርያነት ሕይወት ከምድራዊ ቅንጦት የራቀ መሆኑን መስክሯል። ድህነት የክርስትና መገለጫ ካልሆነ፣ ታዲያ ሐዋርያቱ 'ክርስቲያን አልነበሩም' ሊባሉ ነው? ክርስትና በምድራዊ ጥሪት ሳይሆን በሰማያዊ ተስፋ የተሞላ ሕይወት ነው።

መጽሐፍ ቅዱስ "በእምነት ባለ ጠጎች እንዲሆኑ . . . እግዚአብሔር የዚህን ዓለም ድሆች አልመረጠምንም?" (ያዕ. 2፥5) ይላል። እውነተኛ ባለጸግነት በእግዚአብሔር ዘንድ ባለጸጋ መሆን ነው። ዛሬ ድህነትን የሚጸየፉ ሰዎች፣ ነፍሳቸው በኃጢአት መዝለሏንና በመንፈሳዊ ድህነት ውስጥ መውደቃቸውን ማየት ተስኗቸዋል። እግዚአብሔር ሰውን የሚመዝነው ባለው ንብረት ሳይሆን በውስጣዊ ማንነቱ ነው። በአልዓዛር ቁስልና ድህነት ውስጥ ያለ ክብር፣ በባለጸጋው ሰውዬ ቅንጦት ውስጥ ካለው ውርደት ይበልጣል።

ክርስትና ''ተመችቶኝ ልኑር'' የሚሉ ሰዎች መንገድ ሳይሆን "መስቀሉን ተሸክመው የሚከተሉ" ጀግኖች ጉዞ ነው። ዛሬ "ድህነት አይገባኝም" የሚለው ትውልድ፣ ነገ "መከራም አይገባኝም" ማለቱ አይቀርም። ይኽ ደግሞ ክርስቶስን ያለ መስቀሉ መፈለግ ነው። ሰማዕታት የሞቱት፣ አባቶች ጫካና በረሃ የወደቁት ለምድራዊ ሀብት አልነበረም፤ ይልቁንም "ከክርስቶስ ፍቅር ማን ይለየናል?" በማለት በድህነትና በራብ ውስጥ ሆነው ለዘላለማዊው ክብር ስለቆሙ ነው።

ሀብታም መሆን ኃጢአት አይደለም፣ ድሃ መሆንም ጽድቅ አይደለም። ነገር ግን 'ድህነት የክርስትና መገለጫ አይደለም' ብሎ ድሆችን ማሳቀቅና ክርስትናን ከገንዘብ ጋር ማያያዝ ግን ታላቅ ስህተት ነው። ክርስትና ባለን ነገር የመርካት፣ በሌለን ነገር ደግሞ እግዚአብሔርን የመማጸን ጥበብ ነው። ወዳጄ ሆይ! በምድራዊ ድህነት ውስጥ ሆነህ ሰማያዊው ንጉሥ ካንተ ጋር ከሆነ አንተ ከሁሉ በላይ ባለጸጋ ነህ። ድምፅህ ከሰባኪያን ጩኸት ይልቅ የጌታን ቃል ይስማ፤ እርሱ "በምድር ሀብት አታከማቹ" ብሎናልና! ልባችሁ በምድራዊ ሀብት ሳይሆን በሰማያዊ ጸጋ ይሙላ! በድህነት ውስጥ ክብርን፣ በችግር ውስጥ ምስጋናን የሚሰጥ አምላክ ያጽናችሁ! በክርስቶስ ዘንድ ባለጸጋ ሆናችሁ እንድትገኙ ጸጋው ይርዳን!

የጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ ከመንፈሳችሁ ጋር ይሁን!


https://t.me/anidSew

መንገድ . . .እውነት . . . ሕይወት

በጥልቁ የሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ፣ ከጥንት እስከ ዛሬ ድረስ ሰው የማይረካ ጥማቱን የሚያረካበትን "ሕይወት"፣ ከጨለማ የሚወጣበትን "እውነት" እና ወደ ሰላም ወደብ የሚደርስበትን "መንገድ" ፍለጋ ዓለምን ሲዞር ኖሯል። በታሪክ መድረክ ላይ የተነሱ ብዙ መምህራን 'መንገዱን ላሳያችሁ' አሉ፣ ብዙ ፈላስፋዎችም 'እውነትን ልንገራችሁ' ብለው ሞከሩ፣ ብዙ መሪዎችም 'ሕይወታችሁን ላቅልላችሁ' በማለት ቃል ገቡ፤ ነገር ግን ማንም ቢሆን 'መንገዱ እኔ ነኝ' ለማለት የደፈረ የለም። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ግን በዮሐንስ ወንጌል 14፥6 ላይ "እኔ መንገድና እውነት ሕይወትም ነኝ፤ በእኔ በቀር ወደ አብ የሚመጣ የለም" ብሎ ሲናገር፣ እርሱ ጠቋሚ ብቻ ሳይሆን የጥያቄዎቻችን ሁሉ መድረሻ መሆኑን አበሰረ። ይኽ ቃል በሰውና በእግዚአብሔር መካከል ተበጥሶ የነበረውን ግንኙነት የሚቀጥል መለኮታዊ ድልድይ ነው።


ኢየሱስ ክርስቶስ "መንገድ" ሲሆን፣ የሰው ልጅ በገዛ ጥረቱ ሊደርስበት ያልቻለውን የእግዚአብሔርን ጽድቅና ቅድስና የምንወርስበት ብቸኛ መተላለፊያ ሆነ። እኛ ደክመንና ተሳስተን በጠፋንበት በዚያ የኃጢአት በረሃ ውስጥ፣ እርሱ መጥቶ የሰማዩን ደጅ ከፈተልን። እርሱ "እውነት" ሲሆን ደግሞ፣ ዓለም በሐሰትና በከንቱ ፍልስፍና የሸፈነችውን የመኖር ትርጉም ገለጠልን። እውነት በክርስቶስ ዘንድ ሐሳብ ብቻ አይደለችም፤ እውነት በክርስቶስ ዘንድ የሚታይና የሚዳሰስ ማንነት ነው። እርሱን ማወቅ ማለት ከጥርጣሬ ባርነት ነፃ መውጣትና በጽኑ መሠረት ላይ መቆም ነው። "ሕይወት" ሲሆን ደግሞ፣ በሞት ጽላሎት ውስጥ ለነበረው የሰው ልጅ የዘላለም ተስፋን ሰጠ። ይኽም ሕይወት የልብ ትርታ ብቻ ሳይሆን፣ ከፈጣሪ ጋር ለዘላለም የመኖር መለኮታዊ ጸጋ ነው።

በመጨረሻም፣ ይኽ ቃል የክርስትናን ብቸኝነትና ፍጹምነት ያረጋግጣል። ክርስቶስ "ከመንገዶች አንዱ" ሳይሆን "ብቸኛው መንገድ" ነው፤ "ከእውነቶች አንዱ" ሳይሆን "ፍጹሙ እውነት" ነው፤ "ከሕይወት አማራጮች አንዱ" ሳይሆን "የሕይወት ምንጭ" ነው። ወደ አብ ለመድረስ ከእርሱ በቀር ሌላ በር፣ ሌላ ስም፣ ሌላም ዋስትና የለም። ዛሬም በዚኽ መንገድ ላይ የምንራመድ፣ በዚኽ እውነት የምንመራና በዚኽ ሕይወት የምንኖር ሁሉ ከቶ አንጠፋም። የዓለም መጨናነቅና የኑሮ ውጥረት ቢበረታም፣ መንገዱ ክርስቶስ የሆነለት ሰው መድረሻው የታወቀ ነው፤ እርሱም ሰማያዊውና ዘላለማዊው የእግዚአብሔር እቅፍ ነው።

መንገዳችን ክርስቶስ፣ እውነታችን ደግሞ ቃሉ፣ ሕይወታችንም መንፈሱ ይሁን። ከመንገዱ ሳንወጣ፣ በእውነቱ ታጥበን፣ በሕይወቱ ለምልመን ለዘላለም እንድንኖር ጸጋው ይርዳን።

የጌታ ኢየሱስ ጸጋ ከመንፈሳችሁ ጋር ይሁን!


ከ . . . እስከአሁን ድረስ እግዚአብሔር ረድቶናል!

https://t.me/anidSew

ትጋት . . . ትጋት . . . ትጋት!

በክርስትና ሕይወት ውስጥ "ጸጋ" የእግዚአብሔር ስጦታ ሲሆን፣ "ትጋት" ደግሞ ለዚያ ስጦታ የምንሰጠው ምላሽ ነው። ትጋት ማለት በጊዜያዊ ስሜት ላይ ሳይሆን በጽኑ ዓላማ ላይ ተመስርቶ ወደ ፊት መገስገስ ነው። ብዙዎች በምኞትና በህልም ዓለም ውስጥ ሲኖሩ፣ ትጉሃን ግን ተኝተው የሚያልሙትን ነቅተው ይሠሩታል። ትጋት ሰነፍ ሊወጣው የማይችለው ተራራ ቢመስልም፣ ለወጣው ግን ዓለምን የሚያይበት ሰፊ አድማስ ነው።


ትጋት ማለት ዝም ብሎ መሥራት ሳይሆን፣ ሕይወትን ትርጉም ባለው መሠረት ላይ የመገንባት ጥበብ ነው። እግዚአብሔር ዓለምን የፈጠረው በቃሉ ቢሆንም፣ የሰው ልጅን ዕጣ ፈንታ ግን "በትጋት" ውስጥ አሥሮታል። ትጋት በነፍስ ውስጥ እንደሚነድ እሳት ነው፤ ድካምን የሚያቀልጥ፣ ተራራን የሚያንቀሳቅስና ከባዶነት ውስጥ ተስፋን የሚቀዳ ነው። ብዙዎች ሕይወት በአጋጣሚ የምትለወጥ ይመስላቸዋል፤ እውነታው ግን ሕይወት የምትለወጠው እግዚአብሔር በሰጠን ጸጋና እኛ በምናክለው ትጋት መካከል በሚፈጠር ቅዱስ ጥምረት ነው። ጸጋ ሰማያዊውን በር ሲከፍት፣ ትጋት ደግሞ በዚያ በር እንድንገባ ጉልበት ይሆነናል። በትጋት የታጀበ ሕይወት የሰነፎችን ምኞት ሰባብሮ፣ በክርስቶስ ወደተዘጋጀው የክብር ማማ የሚያደርስ ብቸኛው የተግባር መሰላል ነው።

መንፈሳዊ ሕይወት ያለ ትጋት እንደማይንቀሳቀስ መኪና ነው። መጸለይ ስንፈልግ ብቻ መጸለይ፣ ስሜታችን ሲነሳሳ ብቻ ቃሉን ማንበብ ሳይሆን፣ በማንኛውም ሁኔታ ውስጥ በጽናት መቆም ትጋት ነው። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ "ለሥራ ከመትጋት አትለግሙ፤ በመንፈስ የሚቃጠሉ ሁኑ፤ ለጌታ ተገዙ" (ሮሜ 12፥11) በማለት ያዘናል። ትጋት በውስጣችን ያለውን የእግዚአብሔርን እሳት የሚጭር መቆስቆሻ ነው። መንፈሳዊ ድንዛዜ የሚመጣው ከኃጢአት ብቻ ሳይሆን፣ ካለማገልገልና ካለመትጋት ጭምር ነው፤ ቀላል ይመጣል።

እግዚአብሔር ሰነፍን አይባርክም፤ ምክንያቱም በረከቱን የሚቀበልበት እጅ የለውም። መጽሐፍ ቅዱስ "የትጉህ እጅ ትገዛለች፤ የታካች እጅ ግን ትገብራለች" (ምሳ. 12፥24) ይላል። ትጋት ማለት በሥራ ቦታህ፣ በትምህርትህና በኃላፊነትህ ሁሉ ለሰው ሳይሆን "ለጌታ እንደምትሠራ" መሥራት ነው። ትውልድ በኑሮውና በቤተሰቡ ውስጥ ስኬታማ የሚሆነው፣ እግዚአብሔር በሰጠው ጊዜና ጉልበት በትጋት ሲጠቀምበት ነው። ትጋት ድህነትን የሚያባርር፣ መተማመንን የሚፈጥርና ለሰው ፊት እንዳንጋለጥ የሚያደርግ 'የክብር መንገድ' ነው።

ትጋት የአንድ ቀን ሩጫ ሳይሆን የዘወትር ጉዞ ነው። ብዙዎች በታላቅ ግለት ይጀምራሉ፣ በጥቂት መሰናክሎች ግን ይቆማሉ። እውነተኛ ትጋት ግን በውድቀት ውስጥ መነሳትን፣ በድካም ውስጥ መበርታትን ያካትታል። በትጋት ውስጥ የሚታለፍ መከራ የባሕርይ ጥንካሬን ይፈጥራል፤ ያ ጥንካሬ ደግሞ ተስፋን ያመጣል።

ትጋት በእግዚአብሔር መታመንን አይተካም፤ ይልቁንም በእግዚአብሔር መታመናችንን የምናሳይበት ተግባራዊ መንገድ ነው። ዛሬ የምትተክለው የትጋት ዘር፣ ነገ የዕረፍት ፍሬ ሆኖ ይጠብቅሃል። ሰነፍ ነገን እየተመኘ ዛሬን ያባክናል፤ ትጉህ ግን ዛሬን እየሠራ ነገን በድል ይቀበላል። እንግዲህ በጸሎት፣ በእግዚአብሔር ቃል ጥናትና በዕለት ተዕለት ሥራህ ትጉህ ሁን። የድካምህ ውጤት በምድር ስኬት፣ በሰማይ ደግሞ "አንተ በጎና የታመንህ ባሪያ" የሚል የክብር አቀባበል ይሆናል!

እግዚአብሔር ሰነፍ ምኞትን ከውስጣችን ነቅሎ፣ ትጉህና ለክብሩ የሚቀኑ ልቦችን ይስጠን! ድካማችን በበረከት፣ ጥረታችን በድል ታጅቦ ለታላቁ ክብር ያብቃን!

የጌታ ሰላም ለእናንተ ይሁን!

https://t.me/anidSew

Monday, January 5, 2026

ምሕረትና እውነት ተስማሙ . . .

በሰማይና በምድር መካከል ካሉት ታላላቅ ግጭቶች አንዱ በምሕረት እና በእውነት መካከል ያለው ግጭት ይታይ ነበር። እውነት "ኃጢአት የሠራች ነፍስ ትሞታለች" ብላ ስትፈርድ፣ ምሕረት ደግሞ "ይቅርታ ይደረግላት" ብላ ትማጸናለች። እውነት የእግዚአብሔርን ቅድስናና ጽድቅ ስታሳይ፣ ምሕረት ደግሞ ጥልቅ ፍቅሩንና ርኅራኄውን ትገልጣለች። እነዚህ ሁለት ባሕርያት ሳይጋጩ፣ አንዱ ሌላውን ሳይሽረው እንዴት ሊገናኙ ይችላሉ? ይኽ ምስጢር የተገለጠው በሰው አእምሮ ሳይሆን በቀራኒዮ መስቀል ላይ ነው። በመስቀል ላይ እውነት ዋጋዋን አገኘች፣ ምሕረትም መንገዷን ከፈተች።


እውነት ፊት መቆም ያስፈራል። እውነት ስለ እኛ ማንነት የምትመሰክረው ምስክርነት ደስ የሚያሰኝ አይደለም። "ሁሉ ኃጢአትን ሠርተዋል የእግዚአብሔርም ክብር ጎድሏቸዋል" (ሮሜ 3፥23) የሚለው የእውነት ቃል የሁላችንንም ውድቀት ያሳያል። እውነት ኃጢአትን በደል፣ በደልን ደግሞ ሞት ብላ ትጠራዋለች። ያለ እውነት ምሕረት ትርጉም የላትም፤ ምክንያቱም ጥፋተኛ መሆናችንን ካላመንን ይቅርታ አያስፈልገንም። እውነት መስታወት ናት፤ የቆሸሸውን ማንነታችንን አውጥታ ታሳየናለች።

ምሕረት ደግሞ እግዚአብሔር የማይገባንን ሲሰጠንና የሚገባንን (ቅጣትን) ሲያስቀርልን የምናይበት መለኮታዊ ቸርነት ነው። ምሕረት "ወደ እኔ ኑ" ትላለች፤ ምሕረት የወደቀውን ታነሳለች፣ የቆሰለውን ትጠግናለች። ነገር ግን ምሕረት ብቻዋን ብትቆም ኖሮ "እግዚአብሔር ለኃጢአት ግድ የለውም" የሚያስኝ መስሎ ይታይ ነበር። እግዚአብሔር ግን ፍጹም ፈራጅ በመሆኑ ኃጢአትን ሳይቀጣ ማለፍ አይችልም። ስለዚህ ምሕረት እውነትን የምታረካበት መንገድ ፈለገች።

መዝሙረኛው ዳዊት “ምሕረትና እውነት ተገናኙ፤ ጽድቅና ሰላም ተስማሙ” (መዝ. 85፥10) እንዳለ፣ ይኽ 'መሳሳም' የተከናወነው በክርስቶስ መስቀል ላይ ነው። በመስቀል ላይ እግዚአብሔር ለኃጢአት ያለውን ጥላቻ (እውነትን) በልጁ ላይ ገለጠ፤ ለኃጢአተኛው ያለውን ፍቅር (ምሕረትን) ደግሞ በደሙ አፈሰሰ። እውነት የምትፈልገው የሞት ዋጋ በክርስቶስ ተከፈለ፤ ምሕረት የምትመኘው ነፃነት ደግሞ ለእኛ ተሰጠን። በመስቀል ላይ እግዚአብሔር ጻድቅም (እውነትን ጠባቂ)፣ ኃጢአተኛውንም የሚያጸድቅ (መሐሪ) ሆኖ ተገለጠ።

ዛሬም በሕይወታችን ውስጥ በእውነትና በምሕረት መካከል እንዋዥቃለን። እውነት ስህተታችንን ስትነግረን ተስፋ እንቆርጣለን፤ ምሕረትን ብቻ ስናስብ ደግሞ በኃጢአት እንዘናጋለን። ነገር ግን ክርስቶስን ስንመለከት ሁለቱንም በአንድ ላይ እናገኛለን። እርሱ "እውነትን" እንድንጋፈጣትና ንስሐ እንድንገባ ያደርገናል፤ "በምሕረቱ" ደግሞ አቅፎ ያጸናናል። ወዳጄ፣ እውነትህን ይዘህ ወደ ምሕረት ዙፋን ቅረብ። ኃጢአትህ እውነት ቢሆንም፣ የእርሱ ምሕረት ግን ከዚያ በላይ እውነት ነው። በምሕረትና በእውነት መገናኛ ውስጥ የሚገኘውን ያንን ሰማያዊ ሰላም ዛሬ ተለማመደው!

እውነት ማንነታችንን ብታጋልጥም፣ ምሕረቱ ግን በደላችንን ደመሰሰች። በእውነት ታጥበን፣ በምሕረት ለምልመን ለዘላለም ለመኖር ጸጋው ይርዳን!

የጌታ ኢየሱስ ሰላምና ምሕረት ለሁላችሁ ይሁን!

https://t.me/anidSew

. . . ለሥጋዊው ሰው ሞት ቢመስልም፣ ለመንፈሳዊው ሰው ግን የደስታና የክብር ጎዳና ነው!

በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ ታላቁ ድል የተመዘገበው በጦር ሜዳ ሳይሆን በጎልጎታ ኮረብታ ላይ፣ ራስን ለሌሎች አሳልፎ በመስጠት ፍቅር በተገለጠበት መስቀል ላይ ነው። ክርስትና ማለት ስለ ክርስቶስ ማውራት ብቻ ሳይሆን፣ እርሱ በሄደበት የሕይወት ጎዳና መጓዝ ነው። ይኽ ጎዳና ደግሞ "ራስን መካድ" በሚባል ድልድይ ይጀምርና "መስቀልን መሸከም" በሚባል ጽናት ይቀጥላል። ራስን መካድ ማለት የራስን "እኔነት" ሞት ፈርዶ፣ በእግዚአብሔር "አንተነት" ውስጥ አዲስ ሕይወትን ማግኘት ነው። ይኽ ጉዞ የመሸነፍ ሳይሆን የበላይነት፣ የመጥፋት ሳይሆን የመገኘት፣ የሞት ሳይሆን የትንሣኤ መንገድ ነው።


ራስን መካድ ማለት ማንነትን ማጥፋት ሳይሆን፣ ትክክለኛውን ማንነት ለማግኘት ሲባል የራስን ፈቃድ፣ ስሜትና ፍላጎት ለእግዚአብሔር ፈቃድ ማስገዛት ነው። የሰው ልጅ ውድቀት የጀመረው "እንደ እግዚአብሔር እሆናለሁ" በሚል ራስን የማግነን መንፈስ ነበር፤ መዳኑ ደግሞ "እንደ ቃልህ ይሁንልኝ" በሚል ትሕትና ይጀምራል። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንዲህ ብሏል፣ "እኔን መከተል የሚወድ ቢኖር፥ ራሱን ይካድ መስቀሉንም ተሸክሞ ይከተለኝ።" (ማቴ. 16፥24)። ራስን መካድ ማለት ከራስ "እኔነት" ዙፋን ወርዶ ክርስቶስን በዚያ ዙፋን ላይ ማንገሥ ነው።

መስቀል የመከራ ምልክት ብቻ ሳይሆን፣ የፍጹም ታማኝነትና የድል አርማ ነው። መስቀልን መሸከም ማለት በክርስቶስ ምክንያት የሚመጣውን ተቃውሞ፣ መገለልና መከራ በፍቅር መቀበል ነው። ይኽ ጉዞ የሚከፈል ዋጋ ቢኖረውም፣ ዋጋው ግን ከሚገኘው ክብር ጋር ሊነጻጸር አይችልም። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ "ከክርስቶስ ጋር ተሰቅያለሁ፤ እኔም አሁን ሕያው ሆኜ አልኖርም ክርስቶስ ግን በእኔ ይኖራል" (ገላ. 2፥20) ሲል እንደገለጸው፣ መስቀሉን መሸከም ለዓለም የመሞትና ለክርስቶስ የመኖር ምስጢር ነው።

የክርስትና ሕይወት አያዎ (Paradox) የተሞላ ነው። ለማግኘት ማጣት፣ ለመኖር መሞት ያስፈልጋል። ዘር መሬት ውስጥ ወድቃ ካልሞተች ብቻዋን ትቀራለች፤ ከሞተች ግን ብዙ ፍሬ ታፈራለች። እኛም የገዛ ፈቃዳችንንና ሥጋዊ ምኞታችንን ስንሰዋ፣ በውስጣችን ያለው መለኮታዊ ሕይወት ይለመልማል። "ነፍሱን ሊያድን የሚወድ ሁሉ ያጠፋታል፤ ስለ እኔ ግን ነፍሱን የሚያጠፋ ሁሉ ያገኛታል" (ማቴ. 16፥25)። ይኽ ቃል በምድር ላይ ያለውን ጊዜያዊ እርካታ ትተን፣ ሰማያዊውንና ዘላለማዊውን ሃብት እንድንይዝ ይጋብዘናል።

ራስን የመካድ መንገድ በመጀመሪያ ሲታይ ጠባብና አስቸጋሪ ቢመስልም፣ ውስጥ ውስጡን ግን ሰላምና እረፍት የሞላበት ነው። መስቀሉን የተሸከመ ሰው ከዓለም ጭንቀትና ከራስ ወዳድነት ዕስራት ነፃ ይወጣል። መንፈሱ በእግዚአብሔር ፊት ትሁትና ንቁ ይሆናል። ይኽ መንገድ የክርስቶስን ፈለግ መከተል በመሆኑ፣ መጨረሻው የትንሣኤ ብርሃንና የማይጠፋ የክብር አክሊል ነው። መስቀል የሌለበት ክርስትና ትንሣኤ የሌለው ጉዞ ነው፤ ስለዚህ መስቀላችንን በደስታና በምስጋና ልንሸከመው ይገባል።

መስቀሉን መሸከም ለጥቂቶች የተሰጠ ልዩ ጥሪ ሳይሆን፣ የክርስቶስን ፍቅር ለቀመሰ ሰው ሁሉ የሚሆን የሕይወት መመሪያ ነው። መስቀላችንን ስንሸከም የምንከተለው ከእኛ ጋር አብሮ የሚራመደውን፣ ሸክማችንን የሚያቀልልንንና ድካማችንን ወደ ኃይል የሚለውጠውን አዳኝ ነው። ራሳችንን በካድን ቁጥር እግዚአብሔር በእኛ ውስጥ ይገለጣል፤ መስቀላችንን በከበድን ቁጥር ሰማያዊው ክብር ይቀርበናል። በዓለም ውስጥ ራስን አሸንፎ ለክርስቶስ ለመኖር ስንነሳ የዚያን ጊዜ ዓለምን በማሸነፍ እንኖራለን። ከምድራዊው መቃብር ማዶ የማይጠፋውና የዘላለማዊው የትንሣኤ ብርሃን ይጠብቀናል!

በመስቀሉ ጥላ ስር የምናገኘው እረፍት፣ ራስን በመካድ ውስጥ የሚገኘው እውነተኛ ነፃነት በሁላችንም ሕይወት ላይ ይብራ። 

የክርስቶስ ፍቅር ከእኛ ጋር ይሁን!

https://t.me/anidSew

የሕይወት ሜዳ እና ሰማያዊው VAR

 በአረንጓዴው ሳር ላይ በሚደረገው የእግር ኳስ ጨዋታ፣ የሰው ዓይን ሊያያቸው የማይችሉ ስህተቶችን ለመለየትና ፍትሕን ለማረጋገጥ VAR (Video Assistant Referee) እንደ ዋና ዳኛ ረዳት ሆኖ ይሠራል፤ ስሜትን ይገታል፣ የታመነ ውሳኔንም ይሰጣል። ይኽ ቴክኖሎጂ በስፖርቱ ዓለም አዲስ ክስተት ቢሆንም፣ የሰው ልጅ ሕይወት ግን ከተፈጠረ ጀምሮ በማያንቀላፋና ሁሉን በሚያይ መለኮታዊ "VAR" ሥር ነው። ሕይወት ዝም ብሎ የሚፈስ ወንዝ ሳይሆን፣ እያንዳንዱ እንቅስቃሴው፣ አሳቡና ድብቅ ምኞቱ በሰማያዊው ማያ ላይ የሚመዘገብበት ታላቅ የፍርድ አደባባይ ነው።


በሕይወት ጨዋታ ውስጥ የምናስቆጥራቸው "ጎሎች" ወይም ስኬቶች ሁሉ በሰዎች ዘንድ እውቅና ሊያገኙ ይችላሉ፤ ነገር ግን እውነተኛው ዳኛ እግዚአብሔር ወደ ኋላ ተመልሶ (Review) የሚያየው የጎሉን መቆጠር ብቻ ሳይሆን፣ አኳኋኑንና የልባችንን ቅንነት ነው። መጽሐፍ ቅዱስ በሮሜ 2፥16 ላይ “ይህም እግዚአብሔር በኢየሱስ ክርስቶስ እኔ በወንጌል እንዳስተማርሁ በሰው ዘንድ የተሰወረውን በሚፈርድበት ቀን” በማለት እንደሚናገር፣ በሰው ዓይን የተሸሸገው ተንኮል፣ በጨለማ የተደረገው በደልና ማንም ያላየው "Offside" ሁሉ በዚያ ሰማያዊ ስክሪን ላይ በግልጽ ይታያል። እግዚአብሔር እንደ ሰው ፊት አይቶ ሳይሆን፤ እንደ ቃሉ ሕግና እንደ ልብ ንጽሕና ይፈርዳል።

ከዚህም በላይ፣ በኳስ ሜዳ ላይ አንድ ተጫዋች ሕግ ጥሶ ሲገኝ በVAR ታይቶ ከጨዋታ እንደሚወገድ ሁሉ፣ እኛም በሕይወት ሩጫችን ከመለኮታዊው መስመር ወጥተን የምናደርገው ሩጫ ዋጋ የለውም። በ2ኛ ጢሞቴዎስ 2፥5 ላይ እንደተጻፈ፣ “ደግሞም በጨዋታ የሚታገል ማንም ቢሆን፥ እንደሚገባ አድርጎ ባይታገል፥ የድሉን አክሊል አያገኝም”። በሕይወታችን የምናተርፈው ትርፍና የምናከማቸው ሀብት በመለኮታዊው መመዘኛ ሲታይ "Double Touch" ወይም በሐሰት የተገኘ ከሆነ፣ በመጨረሻው የፍርድ ፊሽካ ወቅት ውድቅ መሆኑ አይቀሬ ነው። እያንዳንዱ ንግግራችንና ድርጊታችን በሰማይ መዝገብ "Pending Decision" በሚል ጥንቃቄ ተመዝግቦ ይቆያል።

ይሁን እንጂ የሰማዩ VAR ከምድራዊው የሚለይበት አንድ አስደናቂ ሚስጥር አለው፤ እርሱም የንስሐ ዕድል ነው። በኳስ ሜዳ VAR ጥፋትን አጋልጦ ለቅጣት ሲዳርግ፣ የእግዚአብሔር ቃል ግን ስህተታችንን አሳይቶ ለንስሐና ለዕርቅ ይጋብዘናል። በ1ኛ ዮሐንስ 1፥9 መሠረት፣ ኃጢአታችንን ብንናዘዝ እርሱ ይቅር ሊለንና ጨዋታችንን በንጽሕና እንድንቀጥል ሊያደርገን የታመነ ነው። ይኽ ሰማያዊ ግምገማ እኛን ለመቅጣት ብቻ ሳይሆን፣ ወደ ቀጥተኛው መንገድ እንድንመለስና የሕይወትን ዋንጫ እንድንበላ የሚረዳን መለኮታዊ ረዳታችን ነው።

ሕይወታችን በሰዎች ፊት የምናሳየው ድራማ ሳይሆን በእግዚአብሔር ፊት የምንኖረው እውነት ነው። በስታዲየም ውስጥ ያሉት በሰላሳና በአርባ ካሜራዎች የታገዙ ዳኞች ሊሳሳቱ ይችላሉ፤ ሁሉን የሚመለከተው የፈጣሪ ዓይን ግን መቼም አይሳሳትም። ስለዚህ ዛሬ በሕይወት ሜዳ ላይ ስንሮጥ፣ በስተመጨረሻ "Decision is Goal" ወይም "Decision is Valid" የሚል የጽድቅ ውሳኔ እንድናገኝ፣ በቅንነት፣ በሕግና በፍቅር መጫወት ይኖርብናል። ምክንያቱም እውነተኛው ድል የሚለካው በሰው ጭብጨባ ሳይሆን፣ በታላቁ ዳኛ ፍጹም ፍርድ ነውና።

ይድረስ፣ ከበለስ በታች ሳለህ ለታየኸው!

https://t.me/anidSew

የዘላለም ሊቀ ካህን

የኢየሱስ ክርስቶስ ሊቀ ካህንነት ከሰው ልጆች ሥርዓትና ከሕግ በላይ የሆነ፣ በመለኮታዊ መሐላ የጸና የዘላለም አገልግሎት ነው። እርሱ እንደ አሮን ሥርዓት ሳይሆን፣ የማይጠፋ ሕይወት ኃይል ባለው "እንደ መልከ ጼዴቅ ሥርዓት" ለዘላለም ካህን ሆኖ ተሹሟል። ይህ አገልግሎት በምድራዊ መቅደስ ሳይሆን፣ በእውነተኛይቱ ድንኳን በሰማያት በእግዚአብሔር ቀኝ የሚከናወን ነው። ዕብራውያን 7፡25 እንደሚለው፣ እርሱ ስለ እነርሱ ሊያማልድ ዘወትር በሕይወት ይኖራልና በእርሱ ወደ እግዚአብሔር የሚመጡትን ፈጽሞ ሊያድናቸው ይችላል።


ክርስቶስ ሊቀ ካህን የሆነው በሌላ ፍጡር ደም ሳይሆን፣ በገዛ ደሙ አንዴ ወደ ቅድስተ ቅዱሳን በመግባት የዘላለምን ቤዛነት አግኝቶልናል። እርሱ መሥዋዕቱም፣ መሥዋዕቱን አቅራቢውም ነው። እንደ ብሉይ ኪዳን ካህናት በየቀኑ መሥዋዕት ማቅረብ አያስፈልገውም፤ ምክንያቱም ራሱን አንድ ጊዜ አሳልፎ በመስጠት የኃጢአትን ግድግዳ ደምስሷል። ይህ አገልግሎት ለሰው ልጅ የእርቅ መንገድን የከፈተና ወደ ጸጋው ዙፋን በድፍረት እንድንቀርብ ያደረገ ታላቅ የምሥራች ነው።

ክርስቶስን የመሥዋዕታችን ሊቀ ካህን፣ የድካማችን ረዳትና የነፍሳችን ጠባቂ ነው። ክርስቶስ አማላጅ ብቻ ሳይሆን፣ ወደ አብ የምንቀርብበት ብቸኛው "በር" ነው። እርሱ ብቻ የአብን ስውር ምስጢር የሚያውቅና ወደ አብ የሚያደርስ ነው። ክርስቶስ በሰማያዊው መሠዊያ ላይ ጸሎታችንን የሚያሳርግ፣ በቅድስናውም እኛን የሚቀድስ ዘላለማዊ መካከለኛ ነው።

የክርስቶስ ሊቀ ካህንነት ዛሬ ላይ ላለን ክርስቲያኖችም ትልቅ መጽናኛ ነው። እርሱ በድካማችን ሊራራልን የማይችል አይደለም፤ ነገር ግን በነገር ሁሉ ከኃጢአት በቀር እንደ እኛ የተፈተነ፣ ስለሆነ፣ ለሚፈተኑት ሊረዳቸውና ሊራራላቸው ይችላል (ዕብ. 4፥15)። በሰማይ ያለን ጠበቃና ሊቀ ካህን ዛሬም ስለ እኛ ይቆማል፤ የኃጢአታችንን ክስ በደሙ ዋጋ ይሽራል። የእርሱ አገልግሎት በሞት አይገታም፤ ምክንያቱም እርሱ ለዘላለም ሕያው ነው። አማኞች በዚህ ታላቅ ሊቀ ካህን ተመርኩዘን ወደ ጸጋው ዙፋን እንቀርባለን። እርሱ በሰማያዊው መቅደስ ለእኛ ስፍራን ያዘጋጃል፣ በመንፈስ ቅዱስ አማካኝነትም ከእግዚአብሔር ጋር ያለንን አንድነት ያጸናል። የክርስቶስ ሊቀ ካህንነት የክርስትና እምነት እምብርትና የዘላለም ሕይወት ዋስትናችን ነው።

የጌታ ሰላም ይብዛላችሁ!

ክርስቶስ የተሰደደባት 'ቤተ ክርስቲያን'

ዛሬ ቤተ ክርስቲያን በሥጋዊ ግርማ አብባ፣ በመንፈሳዊ ድህነት እየማቀቀች ትገኛለች። ትልቁና ዘግናኝ ውድቀቷም ሕንፃዋ መፍረሱ ሳይሆን፣ "ሕያው ክርስቶስን" በመቃብር ድንጋይ በሚመስሉ ሥርዓቶችና በሰዎች ዝና ስር ቀብራው መገኘቷ ነው። 'ቤተ ክርስቲያን' ዛሬ ከመንፈሳዊ የሕይወት ምንጭነት ይልቅ፣ ባለቤቱ የተገፋባትና ግዑዝ ሥርዓቶች የነገሱባት "የባዶነት አዳራሽ" ለመሆን ተቃርባለች። ይህ ዛሬ የምናየው ውድቀት የውጫዊ ውበት መጨመር ሳይሆን፣ የውስጣዊ ማንነት መንጠፍ ነው።


መድረኮቻችን በብርሃን ተጥለቅልቀዋል፤ ጩኸታችን ሰማይ ይነካል፤ ዝማሬዎቻችንም የሰውን ስሜት የመግዛት አቅም አላቸው። ሆኖም ግን ይህ ሁሉ ትርኢት "ባለቤቱ በሌለበት የሚካሄድ የሰርግ ድግስ" ነው። 'ቤተ ክርስቲያን' ዛሬ ክርስቶስን የመስበክ ሳይሆን፣ ክርስቶስን የመተካት አባዜ ተጠናውቷታል። በወርቅ በተለበጡ ዙፋኖች ላይ ሰዎች ነግሰዋል፤ በክርስቶስ ስም የሚነግዱ ነጋዴዎችም ቤቱን የወንበዴዎች ዋሻ አድርገውታል። የናዝሬቱ ኢየሱስ ግን ዛሬም በደጅ ቆሞ ያንኳኳል፤ በገዛ ቤቱ ውስጥ የመግቢያ ፈቃድ የሚያጣ ስደተኛ ሆኗል።

የመዳን ጉልበት የነበረው የመስቀሉ ቃል፣ ዛሬ በሰው ፍልስፍናና በሥነ-ልቦና ወሬ ተተክቷል። ራስን መካድ የሚለው ሕያው ጥሪ፣ "ራስን ማግነን" በሚል ስውር መርዝ ተለውጧል። 'ቤተ ክርስቲያን' ዓለምን ልትቀድስ ተጠርታ ሳለ፣ ዛሬ ግን ዓለምን ለመምሰል ትንፋሿ እስኪያልቅ ትሮጣለች። ክርስቶስን የመከተል ትርጉሙ "መስቀል መሸከም" መሆኑ ቀርቶ "ጥቅም መሰብሰብ" ወደሚል ንግድ ወርዷል።

'ቤተ ክርስቲያን' ከምድራዊ ክብር ማማዋ ላይ ወርዳ፣ ራሷን ለዋጀው ክርስቶስ ካልተንበረከከች፣ የምትሸከመው ስም የሞት ምስክርነት ብቻ ይሆናል። የክርስቶስ መገኘት የሌለበት ጉባኤ "ቅዱስ" ሊባል አይችልም፤ ሕንፃው የቱንም ያህል ቢጸዳ፣ የባለቤቱ መንፈስ ካልነገሰበት ድንጋይ ለብሶ የቆመ መቃብር ነው። ዛሬ የምንሰማው ድምፅ የንስሐ ጥሪ ሊሆን ይገባል፤ ምክንያቱም ክርስቶስ በሌለባት 'ቤተ ክርስቲያን' ውስጥ ድነት የለም፣  ክርስቶስ በሌለባት 'ቤተ ክርስቲያን' የባዶነት መገለጫ ብቻ ናት። ሰዓቱ የሕንፃ ማማዎችን የምንገነባበት ሳይሆን፣ የተሰደደውን የናዝሬቱን ኢየሱስን ወደ ማዕከላችን የምንመልስበት የመጨረሻው የጸጋ ሰዓት ነው። ጌታን ከደጅ አውጥቶ በቤቱ መጋበዝ አይቻልም!

ይመልሰን!

ነገ የሚባል የለም፤ ያለው ዛሬ ብቻ ነው!

"ነገ" የሚባለው ረጅም ጉዞ፣ ሩቅ የሚታይ አድማስ ሳይሆን በዛሬው ማህፀን ውስጥ የሚረገዝ ፅንስ ነው። ብዙዎች የነገውን ወርቃማ ፀሐይ በናፍቆት እየጠበቁ፣ በእጃቸው ያለውን የዛሬውን ፋኖስ ያጠፋሉ። በሚያምር የታሪክ ማማ ላይ ለመቀመጥ ያልማሉ፤ ነገር ግን ያ ማማ የሚቆምበትን የመሠረት ድንጋይ ዛሬ ለመቅረጽ ይፈራሉ፤ ይታከታሉ።


መጽሐፍ ቅዱስ “አንተ ታካች፥ ወደ ገብረ ጕንዳን ሂድ፥ መንገድዋንም ተመልክተህ ጠቢብ ሁን” (ምሳ. 6፥6) እንደሚል፣ ታላቅነት የሚገኘው በታታሪነት ውስጥ ነው። ማወቅ ያለብህ ታላቅ እውነት ግን ይኽ ነው፣ ታሪክ የሚጻፈው በታላላቅ መድረኮች ጩኸት ሳይሆን፣ ማንም በማያይህ በዛሬው የብቻነት ትግልህና በታማኝነትህ ውስጥ ነው። ጌታችን በቃሉ “አንተ በጎ ታማኝም ባሪያ፤ በጥቂቱ ታምነሃል፥ በብዙ እሾምሃለሁ፤ ወደ ጌታህ ደስታ ግባ” (ማቴ. 25፥21) እንዳለ፣ የነገው የክብር ዙፋን የሚገኘው በዛሬው ታማኝነት ልክ ነው።

ዛሬ የምታፈሰው ላብ፣ ነገ የምትጠጣው ጣፋጭ ውሃ ይሆናል። ዛሬ በመከራ የምትቀብረው ዘር፣ ነገ በትውልድ ጥላ የሚሆን ታላቅ ዛፍ ሆኖ ይበቅላል። “በልቅሶ የሚዘሩ በደስታ ይለቅማሉ። በሄዱ ጊዜ፥ ዘራቸውን ተሸክመው እያለቀሱ ተሰማሩ፤ በተመለሱ ጊዜ ግን ነዶአቸውን ተሸክመው ደስ እያላቸው ይመጣሉ” (መዝ. 126፥5-6)።

ስለዚህ የነገን ታሪክ ለመጻፍ ብዕር አትፈልግ፤ ይልቅስ የዛሬን ሰዓት እንደ መጥረቢያ ተጠቀምባት።

የዛሬው ድካምህ፣ የነገው ኩራትህ ነው!

የእግዚአብሔርን ፈቃድ የመፈለግ የፍቅር ጉዞ

የሰው ልጅ ሕይወት በብዙ ሺህ በሚቆጠሩ ምርጫዎች የተሞላች እንቆቅልሽ ናት። በየቀኑ በቆምንባቸው አደባባዮች ሁሉ "የትኛው መንገድ ይሻለኛል? የፈጠረኝ አምላክስ ከእኔ ምን ይፈልጋል?" የሚለው ጥያቄ በውስጣችን ያስተጋባል። ብዙዎቻችን የእግዚአብሔርን ፈቃድ እንደ አንድ የተሰወረና በድካም ሊፈለግ እንደሚገባ "የቀበርነው ሀብት" አድርገን እንቆጥረዋለን። ነገር ግን የእግዚአብሔር ፈቃድ ከእኛ የተደበቀ ሚስጥር ሳይሆን፣ እርሱ ሊያሳየን የሚፈልገውና በየእርምጃችን የሚገለጥ ድንቅ ብርሃን ነው። መዝሙረኛው ዳዊት እንደሚለው፦ "ሕግህ ለእግሬ መብራት፥ ለመንገዴም ብርሃን ነው" (መዝ. 119፥105)። ይህንን ፈቃድ ማወቅ ደግሞ ከውሳኔዎቻችን በፊት የልባችንን ትርታ ከእግዚአብሔር ጋር ማስተካከልን የሚጠይቅ የፍቅር ጉዞ ነው።


የእግዚአብሔርን ፈቃድ መፈለግ ልክ ጭጋጋማ በሆነ መንገድ ላይ መኪና እንደመንዳት ነው። የፊታችን ያለውን ኪሎ ሜትር በሙሉ ማየት ባንችልም፣ መብራታችን ግን ለሚቀጥለው ጥቂት ሜትር በቂ ብርሃን ይሰጠናል። ይህ ጉዞ ሳቢ የሚሆነው ደግሞ የእግዚአብሔርን ፈቃድ የማወቅ ጥማታችን ከውጤቱ በላይ ሲበልጥ ነው። ብዙዎቻችን ፈቃዱን የምንፈልገው "ስህተት ላለመሥራት" ወይም "ውጤታማ ለመሆን" ብለን ቢሆንም፣ እግዚአብሔር ግን ፈቃዱን የሚገልጥልን ከእርሱ ጋር እንድንነጋገርና እንድንቀራረብ ስለሚፈልግ ነው። እርሱ የሕይወታችን "ጂፒኤስ" ብቻ ሳይሆን አብሮን የሚጓዝ የቅርብ ወዳጃችን ነው። ስለዚህ ትኩረታችን መሆን ያለበት "የት ልሂድ?" በሚለው ላይ ብቻ ሳይሆን "ከማን ጋር ልሂድ?" በሚለው ላይ መሆን አለበት፤ እርሱን ስንይዝ መንገዱ ራሱ ግልጽ እየሆነ ይመጣል። መጽሐፍ እንደሚል፦ "በመንገድህ ሁሉ እርሱን እወቅ፥ እርሱም ጎዳናህን ያቀናልሃል" (ምሳ. 3፥6)።

አንዳንድ ጊዜ ግን እግዚአብሔርን አጥብቀን ስንጠይቅ እርሱ ዝምታን ይመርጣል። ይህ ዝምታ "አልሰማሁህም" ማለት ሳይሆን "እመነኝ" የሚል መለኮታዊ ግብዣ ሊሆን ይችላል። ፈቃዱን ለማወቅ በምንጥርበት ጊዜ የምናሳልፈው የጥበቃ ጊዜ ባህሪያችን የሚቀረጽበት ወርቃማ ወቅት ነው። እግዚአብሔር ከምንሠራው ሥራ ይልቅ ለምንሆነው ማንነት ትልቅ ዋጋ ይሰጣል። ስለዚህ መልሱ እስኪመጣ የምንጠብቅበት ትዕግሥት ራሱ የእግዚአብሔር ፈቃድ አካል ነው። በዚያ ዝምታ ውስጥ የእምነት ጡንቻችን ይጠነክራል፣ የእርሱንም ድምፅ ከገዛ ፍላጎታችን መለየት እንጀምራለን። ነቢዩ ኢሳይያስ እንደተናገረው፦ "እግዚአብሔርን በመተማመን የሚጠባበቁ ግን ኃይላቸውን ያድሳሉ፤ እንደ ንስር በክንፍ ይወጣሉ" (ኢሳ. 40፥31)።

ከዚህም ባለፈ እግዚአብሔር በሁኔታዎችና በተዘጉ በሮች ቋንቋ ይናገረናል። አንዳንድ ጊዜ እኛ በከፍተኛ ጉጉት የምንመኘው በር በሃይል ይዘጋል። ያኔ ልባችን ሊሰበርና ግራ ልንጋባ እንችላለን፤ ነገር ግን የተዘጋ በር የእግዚአብሔር ጥበቃ መግለጫ መሆኑን መረዳት አለብን። "አይሆንም" የሚለው መልስ ራሱ አንዱ የፈቃዱ መገለጫ ነው። ወደፊት ቆም ብለን ስንመለከት ያ የተዘጋ በር ካልተፈለገ አደጋ እንደጠበቀን ወይም የተሻለ በር እንድናንኳኳ እንደገፋን እንረዳለን። የእግዚአብሔር ፈቃድ ሁልጊዜ እኛ ያቀድነው ሳይሆን፣ ለእኛ የሚበጀው ነው። ምክንያቱም ሐሳቡ ከሐሳባችን፣ መንገዱም ከመንገዳችን እጅግ የላቀ ነው (ኢሳ. 55፥8-9)።

በእነዚህ ሁሉ ውሳኔዎች መካከል ደግሞ "የውስጥ ሰላም" እንደ ትልቅ ኮምፓስ ያገለግለናል። የእግዚአብሔር ፈቃድ ሲሆን፣ በሁኔታዎች መካከል ትልቅ ዕረፍት አለ። ዓለም ሁሉ ግራ ቢጋባና ነገሮች ባይስተካከሉም እንኳ፣ በውስጣችን ያለው መረጋጋት እግዚአብሔር ከእኛ ጋር መሆኑን ያረጋግጥልናል። ሐዋርያው ጳውሎስ እንዳስተማረው፣ "በክርስቶስ ኢየሱስ ልባችሁንና አሳባችሁን የሚጠብቀው ከሰው እውቀት በላይ የሆነው የእግዚአብሔር ሰላም ይገዛላችሁ" (ፊል. 4፥7)። በአንጻሩ ደግሞ በሰው ዓይን ትክክል የሚመስል ነገር ግን በውስጣችን ዕረፍት የሚነሳን ከሆነ፣ ቆም ብለን ማሰብ ይኖርብናል። ያ የውስጥ ሰላም መንፈስ ቅዱስ እኛን የሚመራበት ረቂቅ ድምፅ ነው። ይህ ሰላም ደግሞ ሁልጊዜም ከመጽሐፍ ቅዱስ ቃል ጋር ይስማማል፤ ምክንያቱም ከቃሉ ውጪ የሆነ የእግዚአብሔር ፈቃድ የለምና። በየቀኑ በቃሉ ውስጥ ስንኖር፣ አስተሳሰባችን መለኮታዊውን ድግግሞሽ መያዝ ይጀምራል፤ ያኔ ፈቃዱን ማወቅ አስቸጋሪ ስራ መሆኑ ቀርቶ የሕይወት ዘይቤ ይሆናል።

በመጨረሻም፣ የእግዚአብሔርን ፈቃድ መፈለግ ማለት አንድን ደረቅ መመሪያ መከተል ሳይሆን፣ ሕያው ከሆነ አምላክ ጋር አብሮ መጋዝ ነው። ውሳኔዎቻችን ስህተት ሊሆኑ ቢችሉም እንኳ፣ እርሱ ግን በመንገዳችን ላይ ወደ ፈለገው ወደብ ሊያደርሰን የታመነ ነው። ሕይወትህን በእርሱ እጅ ስታስቀምጥ፣ ፈቃዱ በሕይወትህ እንዲፈጸም መፍቀድህ ብቻ ሳይሆን፣ አንተም በፈቃዱ ውስጥ ደስተኛና ውጤታማ ትሆናለህ። "አቤቱ ፈቃድህን ለማድረግ አስተምረኝ፥ አንተ አምላኬ ነህና" (መዝ. 143፥10) ስትለው፣ እርሱ ሕይወትህን በማንም የሰው ጥበብ ሊሳል የማይችል ውብ ስዕል አድርጎ ይቀርጸዋል።

እግዚአብሔርን ፈቃድ ዕወቅ፤ ዛሬውኑ ፈቃዱን ለሚገልጥልህ ጌታ ልብህን አስገዛ። ወደፊት ለመራመድ አትፍራ፤ የእግዚአብሔር ፈቃድ ካንተ እቅድ በላይ ጥንቁቅ ነውና ዛሬውኑ የመጀመሪያውን የእምነት እርምጃ ተራመድ። ፈቃዱን ለመፈለግ ሳይሆን፣ ፈቃዱን ለመኖር ተነሳ! ዛሬ የራስህን መንገድ ለጥቂት ጊዜ ገታ አድርግና፣ አምላክህን እንዲህ በለው፦ 'ጌታ ሆይ፤ እኔ ዝግጁ ነኝ፣ አንተ ግን መሪዬ ሁን፤ ፈቃድህ በሕይወቴ ይሁን።'

የጌታ የኢየሱስ ጸጋ ይብዛላችሁ!

የዘላለም ንጋት . . .

በታሪክ ማህደር ውስጥ ካሉ ክስተቶች ሁሉ እጅግ ታላቅና አስደንጋጭ፣ ነገር ግን ለሚጠባበቁት እጅግ ናፍቆት የሆነው ያ ቀን ይመጣል። ዓለም በልማዷ በምትታመስበት፣ የሰው ልጆች በምድራዊ ጭንቀትና በትዕቢት በታወሩበት በዚያ ድንገተኛ ሰዓት፣ ሰማይ እንደ ጥቅልል ይከፈታል። ያን ጊዜ የሰው ልጅ ታሪክ አቅጣጫውን ለዘላለም ይለውጣል። የሰማይ መከፈት ብቻ ሳይሆን፣ ለእውነተኞቹ የዘላለም ንጋት የሚጀምርበት፣ የሞትና የህመም ጥላ የሚያበቃበት ያ የክብር ቀን ነው።


ያ ቅጽበት ልክ እንደ ዓይን ጥቅሻ ፈጣን ነው። የመላእክት አለቃ ድምፅና የእግዚአብሔር መለከት ሲነፋ፣ ምድር ከዚህ ቀደም ሰምታው የማታውቀውን ድምፅ ትሰማለች። ያ ድምፅ ለዓለም ፍርድ፣ ለቅዱሳን ግን የሰርግ ጥሪ ነው። በክርስቶስ ሆነው ያንቀላፉት ቅዱሳን መቃብራቸውን ሰብረው በክብር ይነሳሉ። የማይበሰብሰውና የማይሞተው አዲሱ ማንነታቸው ከምድር አፈር ውስጥ እንደ ጸሐይ ብርሃን ፈንጥቆ ይወጣል። ሞት ድል ተመትቶ፣ መቃብር ባዶውን ቀርቶ፣ ቅዱሳን ከጌታቸው ጋር ለመገናኘት ወደ ሰማይ ይተኮሳሉ።

ከዚያም እኛ በሕይወት የምንኖረው፣ ድካምና መከራ የሰለቸን፣ በናፍቆት አይኖቻችን የፈዘዙት፣ በቅጽበት እንለወጣለን። ይህ የሚሞተው ስጋችን የማይሞተውን ይለብሳል። የምድር ስበት ሊይዘን አይችልም፤ የአየር ክልል ጋሬጣ ሊያግደን አይችልም። ልክ ብረት ወደ ማግኔት እንደሚሳብ፣ እኛም ወደ ወደደንንና ነፍሳችንን በደሙ ወደ ዋጀው ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ እንሳባለን። በአየር ላይ ከጌታ ጋር ስንገናኝ፣ ያኔ የእንባ ዘመን ያበቃል፤ የጋሬጣና የእሾህ ምድር ወደ ኋላችን ትቀራለች።

በደመና መካከል የምናየው ፊቱ እንደ ጸሐይ የሚበራውን፣ እጆቹ የፍቅሩን ምልክት፣ የችንካሩን ጠባሳ፣ የያዙትን፣ የነፍሳችንን እረኛ ነው። ያኔ "ጌታ ሆይ እስከመቼ?" ብለን የጠየቅነው ጥያቄ በክብር መልስ ያገኛል። ፍጹም በሆነ ሰላም፣ በማያልቅ ደስታና በከበረ ዝማሬ እንከበባለን። ሙሽራይቱ ቤተክርስቲያን ከሙሽራው ክርስቶስ ጋር ለዘላለም ትዋሀዳለች። ያ ቀን የድካማችን ማብቂያ፣ የሩጫችን ግብና የፍቅራችን ፍጻሜ ነው።

እስከዚያው ግን ልባችን "ጌታ ኢየሱስ ሆይ ና!" እያለ ይቃትታል። በምድር ላይ ስንመላለስ እንደ እንግዳና እንደ መጻተኛ ነው፤ ምክንያቱም ቤታችን እዚህ አይደለምና። ዓይኖቻችን ወደ ሰማይ ተተክለዋል፣ ጆሮዎቻችን የመለከቱን ድምፅ ለመስማት ተዘጋጅተዋል። ያ የተባረከ ተስፋችን፣ የክብር አክሊላችንና የነፍሳችን መልሕቅ እርሱ ኢየሱስ ክርስቶስ በክብር ተመልሶ ይመጣል። መምጣቱም እጅግ ቅርብ ነው!

🙏🙏ከፀሐይ መውጫ እስከ መጥለቂያዋ ድረስ ስምህ ይባረክ፤ የነፍሳችን እረኛና የዘላለም ንጉሥ ሆይ! ከምድር ስበትና ከዓለም ድካም ነጥቀህ ወደ ቅድስናህ ፊት እስከምትወስደን ድረስ በናፍቆት እንጠባበቅሃለን፤ ማራናታ፣ ጌታ ኢየሱስ ሆይ በቶሎ፣ በፍጥነት ና!🙏🙏

💪ለእናንተ ነው . . . ለእነርሱ አይደለም!❤️

 ልባችሁ ለጠፉት የሚራራ፣ እጆቻችሁ የተሰበሩትን ለመጠገን የሚዘረጋ፣ ከእግዚአብሔር ለሚመጣላችሁ ጥሪ መንፈሳችሁ የሚቀጣጠል፤ ይኽ ለእናንተ ነው።


የእግዚአብሔርን ሳይሆን የራሳቸውን መንግስት ለመመስረትና ለመገንባት የሚፋጠኑ 'መሪዎች'፤ የዝና ጥማት የሚያሰክራቸው፣ የገንዘብ ፍቅር ቃጠሎ የሚያነዳቸው፣ ሕዝቡን የራሳቸውን ግብ ለመፈጸም መጠቀሚ መሣሪያቸው ያደረጉ ብዙ 'አገልጋዮች' ነን የሚሉትን 'እነእንትናን' አይታችኋል። የአገልግሎትን ትክክለኛ ድርጊት የጣሰ ተግባር ነው። ወይ የአገልግሎትን ጥሪ መካድ ነው።፤ ወይ ደግሞ ጠሪው እግዚአብሔር ያልሆነበት 'የአገልግሎት ሥራ' ነው።

ቀረብ ብላችሁ ስሙኝ፤ በደንብ አድምጡኝ። የእነርሱ ውድቀት፣ በተሳሳተ መንገድ ላይ መሆናቸው የእናንተን ጥሪ አይገልጸውም። የእነርሱ ነገሮችን compromise የማድረግ ድርጊታቸው የእናንተን ጸጋ cancel አያደርገውም። (ያው አንዳንድ እንግሊዘኛ ቃላትን ልጠቀም ብዬ ነው፤ 'እነእንትና' ጸሐፊው 'የተማረ' ይመስላቸዋልና ነው፤ እናንተ ደግሞ አሁን ይኼ እንግሊዘኛ መሆኑ ነው? እንዳትሉ። ሰፍሬ ለክቼ በእነርሱ ልክ ነው ያስቀመጥኩት፤ እነዚህን ቃላቶች 'እነእንትና' በጣም ይወዷቸዋል)

ዓለም 'በቤተክርስቲያን' መድረኮች ላይ ያቆመቻቸው በቂ CEOs አሏት። በጣም ብዙ ዝነኛና ታዋቂ የሆኑ ራሳቸውን 'እረኞች' በማድረግ የሚያታልሉ celebrities አሏት። ዓለም የራባት፤ ቤተክርስቲያንም የናፈቀችው እውነተኛ አገልጋይ ነው። የፍቅር ዘማቾች፤ ራሳቸውን የከዱ የክርስቶስ አምባሳደሮች፣ የኢየሱስ ወኪሎች፤ አድነኝ እያለ ለሚጮኽ ድምጽ ፈጣን ምላሽን የሚሰጡ ተወርዋሪ ከዋክብት። እኔን የማያውቁ፣ ሁልጊዜ ንግግራቸው እርሱ (ኢየሱስ ክርስቶስ) የሆነላቸው። ዓለም እኚኽ ያስፈልጓታል። ለዓለም የምታስፈልጉ፣ እግዚአብሔርን የምትወዱት እናንተ አስታውሱ . . .

👉 ጥሪያችሁ ከሰው ሳይሆን ከእግዚአብሔር ነው።
የእናንተን 'ዕጣ ፈንታ' ቁልፍ የያዘ አንድም ፓስተር የለም። የእናንተ ሹመት፣ ማረጋገጫችሁ በጸጥታ 'ከሆነ ቦታ' ከጠራችሁ ከእርሱ የመጣ ነው። ሳሙኤል በሌሊት በእግዚአብሔር እንጂ በኤሊ አልተጠራም። ዳዊት የተቀባው በሜዳ ላይ ነው እንጂ በቤተ መንግሥት አልነበረም። ሰው እጁን ሊጭንባችሁ ይችላል ነገር ግን መንፈስ ቅዱስ ነው የሚለያችሁ። የተዘጋው የሰው በር የተከፈተውን የእግዚአብሔርን በር እንድትጠራጠሩ እንዲያደርጋችሁ አትፍቀዱለት።

👉 ተምሳሴታችሁ፣ አርአያችሁ፣ ምሳሌያችሁ ክርስቶስ እንጂ የሆነ 'ታዋቂ' ሰው አይደለም። ኢየሱስን ተመልከቱ። ሕንጻ አልነበረውም፤ የማስታወቂያ ቡድንም ሆነ የፖለቲካ ተጽእኖ የሚያደርግበት አልነበረውም። እግሩ አቧራማ፣ የደከመ አካል፣ ለሰዎች ደግሞ የተሰበረ፣ የሚያዝን፣ የሚራራ ልብ ነበረው። የብዙዎችን እግር አጠበ። ለምጻሞችን ነካ።  ከኃጢአተኞች ጋር በላ። መሪነትን አገልጋይነት፣ ታላቅነት ደግሞ ትህትና እንደሆነ ገልጿል። ትዕቢተኞችን ለማየት ስትፈተኑ ወደ መስቀል ተመለስ።  ያ የእናንተ ሞዴላችሁ ነው። ያ የእናንተ ኃይላችሁ ነው።

👉 ልባችሁን ጠብቁ፤ እልከኛ አታድርጉት። በግብዝ ሰዎችና በድርጊቶቻቸው ማዘን ትክክል ቢሆንም ያ ሀዘን ወደ ቂምና ምሬት አይለወጥ። ያላችሁን ስሜት በንፅህና ጠብቁ፣ ልባችሁን ለስላሳ የሆነና ለፍቅር የተከፈተ አድርጉት። መራራ እረኛ መራራ መንጋ ብቻ ነው የሚመራው። ህመማችሁ ርህራሄን እንጂ ትችታችሁን አያቀጣጥል።

👉 የዝግጅት ጊዜህ የተቀደሰ ነው። ይህ ትግል፣ ይህ በሰው ችላ የመባል ስሜትን እግዚአብሔር የሚያየው ነው። በእናንተ ውስጥ ምን አይነት ነገር እየፈጠረ እንደሆነ እናንተው ታውቃላችሁ። እግዚአብሔር ግን በእርሱ ብቻ እንድትመኩ እያስተማራችሁ ነው። የመድረክ ፍላጎትን ገፎ በእናንተ ውስጥ እርሱ የሚጠቀምበትን ባህሪ እየገነባ ነው። እግዚአብሔር በእናንተ ውስጥ በትኛውም የትዕቢት ማዕበል የማይናወጥ የትሕትና መሠረትን እየገነባ ነው።

👉 'በተለየ መንፈስ' ተነሱ። ሌሎቹ እንዲሆኑ የምትፈልጉትን መሪ፤ እንዲኖራችሁ የምትመኙት መሪ እናንተው ሁኑት። የሚያስፈራና የሚያስፈራራ ሳይሆን ኃይልን የምትሰጡ ሁኑ። የሌሎችን ስኬት የምታከብሩ ሁኑ እንጂ በሌሎች ስኬት ስጋት አይሰማችሁ። ማይክራፎኑን የምትሰጡ፣ መጪውን ትውልድ የምትመክሩ፣ የሚዲያ ሳይሆን የአገልጋዮችን legacy የምትገነቡ ሁኑ። እንደ በርናባስ የጳውሎስን አቅም አይቶ ለእርሱ ጥብቅና እንደቆመለት ሁኑ። መንግሥቱ የሚባዛው በልግስና እንጂ በስግብግብነት አይደለም።

ለእነርሱ👹 ተቀብዬ እስክመለስ . . .  ለእናንተ የተቀበልኩትን እነሆኝ ብያለሁ።

የጌታ የኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ ከመንፈሳችሁ ጋር ይሁን!

ተጻፈ ከአንድ ሰው በብዙ ሰዎች በኩል ይደርስ ዘንድ ለአንድ ሰው!

AI በአማኙ ሕይወት፡ መረጃን ከቅባት፣ ማሽንን ከህብረት የመለየት ጥበብ

በታሪክ ውስጥ የሰው ልጅን አኗኗር በእጅጉ ከቀየሩ ግኝቶች መካከል ሰው ሰራሽ አስተውሎት (Artificial Intelligence) ግንባር ቀደሙን ስፍራ እየያዘ ይገኛል። እንደ አማኝ ይህንን ቴክኖሎጂ ስንመለከት በሁለት ጽንፎች መካከል ልንወድቅ እንችላለን፤ አንደኛው በፍርሃት ርቆ መቆም ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ ያለ ምንም ጥንቃቄ ራስን አሳልፎ መስጠት ነው። ነገር ግን መጽሐፍ ቅዱሳዊው እይታ "ሁሉን መርምሩ፤ መልካሙንም ያዙ" (1 ተሰ. 5:21) በሚለው መርህ እንድንመራ ያሳስበናል። AI መረጃን የማቀነባበር እንጂ እስትንፋሰ መለኮት ያለበት "ነፍስ" ያለው ፍጥረት እንዳልሆነ መረዳት የመጀመሪያው እርምጃ ነው። እግዚአብሔር ለሰው ልጅ ዓለምን እንዲገዛና እንዲያለማ የሰጠው ጥበብ ውጤት ቢሆንም፣ ይህ መሣሪያ ፈጣሪውን የሚተካ ሳይሆን ለፈጣሪ ክብር የሚውል ሊሆን ይገባል። ሆኖም ይህ ቴክኖሎጂ በውስጡ የያዘው "ሁሉን አዋቂነት" የሚመስል ባህሪ አማኙን ከእውነተኛው የጥበብ ምንጭ እንዳያርቀው ከፍተኛ ጥንቃቄ ያስፈልጋል።


የAI አጠቃቀማችን ከክርስቲያናዊ ስነ-ምግባር አንጻር ሲመዘን ትልቁ ፈተና "ታማኝነት" ላይ ያርፋል። ዛሬ AI ድርሰቶችን ሊጽፍ፣ ስብከቶችን ሊያዘጋጅ ወይም ጥልቅ የሆኑ የሥነ መለኮት ትንታኔዎችን ሊሰጥ ይችላል። እዚኽ ጋር ግን አንድ ሞጋች ጥያቄ መነሳት አለበት፦ "ይህ ውጤት ከልቤ የፈለቀ ነው ወይስ የማሽን ውጤት?" መንፈሳዊ ሕይወት በዋነኝነት ከእግዚአብሔር ጋር የሚደረግ የግል ትጋትና ግንኙነት ውጤት ነው። አንድ አማኝ የAI ውጤቶችን እንደ ግል መንፈሳዊ ልምምዱ አድርጎ ማቅረብ ሲጀምር፣ ውስጣዊ ማንነቱና ውጫዊ ገጽታው መለያየት ይጀምራል። እግዚአብሔር የሚፈልገው የእኛን ድካም፣ ጥረትና ከልብ የሚመነጭ ምስጋና እንጂ በማሽን የተቀነባበረ ፍጹም የሚመስል ግን "ባዶ" የሆነ ጽሑፍ አይደለም። ቴክኖሎጂው ጥልቅ የሆኑ አሳቦችን ሊያቀነባብር ቢችልም፣ የመንፈስ ቅዱስን ቅባትና የልብ መለወጥን ሊተካ አይችልም። ስለዚህ ቴክኖሎጂውን እንደ ረዳት እንጂ እንደ ምንጭ አለመመልከት ለቅንነትና ለታማኝነት ሕይወታችን ወሳኝ ነው።

በመቀጠልም፣ AI በሰው ልጅ "ብቸኝነት" እና "ማኅበራዊ ትስስር" ላይ የሚያመጣው ተጽዕኖ በከፍተኛ ሁኔታ ሊሞገት የሚገባው ጉዳይ ነው። የሰው ልጅ "ብቻውን ይሆን ዘንድ መልካም አይደለም" ተብሎ እንደመፈጠሩ፣ ህብረትና ግንኙነት የሰውነቱ መገለጫዎች ናቸው። ይሁን እንጂ የAI አጠቃቀማችን ከሰዎች ጋር ካለን ቀጥተኛ ግንኙነት ይልቅ ከማሽኖች ጋር የምናደርገውን መስተጋብር እያበረታታው ነው። በዲጂታል ዓለም ውስጥ የሚሰጡ "ሰው ሰራሽ" ማጽናኛዎችና ምክሮች እውነተኛውን የወንድማማችነት መጽናናትና የቤተክርስቲያንን ኅብረት ሊተኩ አይገባም። ቤተክርስቲያን የክርስቶስ አካል እንጂ የዲጂታል መረጃዎች ስብስብ አይደለችም። AI አንዳች ስሜት ሳይኖረው "እግዚአብሔር ይወድሃል" ሊል ይችላል፤ አማኝ ግን ይህንን የሚለው ከክርስቶስ ፍቅር ተካፋይ በመሆንና ከሚሰማው ርኅራኄ በመነሳት ነው። ቴክኖሎጂው መረጃን ሊያቀርብ ይችላል እንጂ ፍቅርን፣ እምነትንና ተስፋን ሊያስተላልፍ አይችልም። በመሆኑም አጠቃቀማችን ሰዎችን ወደ ማሽን ሳይሆን ወደ ሕያው እግዚአብሔርና ወደ እውነተኛው የወንድማማችነት ሕብረት የሚመራ ሊሆን ይገባል።

ሌላው እጅግ አሳሳቢው ነጥብ የAI "ሥልጣን" (Authority) ጉዳይ ነው። ብዙ ጊዜ ቴክኖሎጂው የሚሰጠንን መልስ እንደ መጨረሻ እውነት የመቀበል ዝንባሌ ይታይብናል። ነገር ግን AI መረጃዎችን የሚያቀነባብረው በውስጡ ከተጫኑለትና በዓለም ላይ ካሉ መረጃዎች በመሆኑ፣ የዓለማዊውን አስተሳሰብ (Worldview) እና አድሎአዊነትን ሊያንጸባርቅ ይችላል። መጽሐፍ ቅዱስ "የእውነትን ቃል በትክክል" (2 ጢሞ. 2:15 አ.መ.ት.) ማስረዳትን እንደሚጠይቀን፣ ከAI የምናገኛቸውን መልሶች በቃለ እግዚአብሔር መፈተን ይኖርብናል። AI መንፈሳዊ ጥያቄዎቻችንን ሲመልስ የመስቀሉን ሞኝነት፣ የጸጋን ጥልቀትና የመንፈስ ቅዱስን ምሥጢራዊ አሠራር ላያካትት ይችላል። ይልቁንም እምነት ወደ ስነ-ልቦናዊ ቀመር ወይም ወደ ሰብአዊ ጥበብ ብቻ ሊያወርደው ይችላል። ስለዚህ የእኛ መንፈሳዊ ብስለት የሚለካው ቴክኖሎጂውን በመቃወም ሳይሆን፣ በቴክኖሎጂው መካከል የእግዚአብሔርን ድምፅ ለይቶ በማወቅና ሰብአዊ ክብራችንን ጠብቀን በመመላለስ ነው።

በመጨረሻም፣ የAI አጠቃቀማችን ለስንፍና በር እንዳይከፍት መጠንቀቅ አለብን። መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት፣ መጸለይና መንፈሳዊ ነገሮችን ማሰላሰል ድካምንና ትጋትን የሚጠይቁ የዲሲፕሊን ሥራዎች ናቸው። AI እነዚህን ሂደቶች "አሳጥሮ" ሲያቀርብልን፣ እኛ ሳንለወጥ እውቀት ብቻ እንድንሰበስብ ሊያደርገን ይችላል። እውነተኛ መንፈሳዊ እድገት የሚመጣው ግን በመረጃ ብዛት ሳይሆን በቃሉ ውስጥ በምናሳልፈው ሰዓትና በመንፈስ ቅዱስ መታደስ ነው። AIን ስንጠቀም ሁልጊዜም "ይህ መሣሪያ ለእግዚአብሔር ክብር፣ ለቤተክርስቲያን እድገትና ለሰዎች በረከት እየዋለ ነው? ወይስ እኔን ከመንፈሳዊ ጥጋትና ከእውነተኛ ትጋት እያራቀኝ ነው?" ብለን ራሳችንን መጠየቅ የዘመኑ የጥበብ መጀመሪያ ነው። ቴክኖሎጂው አገልጋያችን እንጂ አምላካችን እንዳይሆን፣ በአልጎሪዝም በተሞላው ዓለም ውስጥ በእግዚአብሔር አምሳያ መፈጠራችንንና የክርስቶስ ምስክሮች መሆናችንን አንዘንጋ።

🤔ለማሰላሰል የሚረዱ ነጥቦች🤔

1. AIን ስጠቀም (ለምሳሌ ለስብከተ፣ ለጽሑፍ ወይም ለጥናት) የራሴን ድካምና ትጋት እየተካሁበት ነው ወይስ እያገዝኩበት? AIን ተጠቅሜ የምሰራቸው እነዚህና የመሳሰሉት ሥራዎች በእግዚአብሔር ፊት "የእኔ" ተብለው ሊቀርቡ የሚችሉ ናቸው? ወይስ መንፈሳዊ አቋራጭ እየፈለግኩ ነው?

2.የAI መልሶች መጽሐፍ ቅዱሳዊ እውነትን እየደገፉ ነው ወይስ በዘመኑ አስተሳሰብ የተበረዙ ናቸው? መለየት የምችልበት መንፈሳዊ ንቃት አለኝ? በቴክኖሎጂ አማካኝነት የማገኛቸውን መረጃዎች በመጽሐፍ ቅዱስ እውነት የመመዘን ልምድ አለኝ?

3.ቴክኖሎጂው ከሰዎች ጋር ባለኝ የቀጥታ ግንኙነትና በቤተክርስቲያን ተሳትፎዬ ላይ ቦታ እየቀማኝ ይሆን?

👉 ስለዚህ ዘመኑን የሚዋጅ ጥበብ ይኑረን፤ ቴክኖሎጂው የምርምራችን ረዳት እንጂ የልባችን ጌታ፣ የጥናታችን መሣሪያ እንጂ የመንፈሳዊ ማንነታችን ምንጭ እንዳይሆን በንቃት እንመላለስ።

የጌታ የኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ ከመንፈሳችሁ ጋር ይሁን!

ኢየሱስ የሚለውን ስም ምስጢርና ኃይል መረዳት

ይህ ስም ተራ ስያሜ ሳይሆን፣ የአጽናፈ ዓለሙን በር የሚከፍት ሚስጥራዊ ቁልፍ፣ የሰማይና የምድርን የኃይል ሚዛን የሚቀይር የሥልጣን ማኅተም ነው። «በኢየሱስ ስም» የሚለው ሐረግ በብዙዎቻችን አንደበት እንደ ልማድ ቢመላለስም፣ ከቃላቱ ጀርባ ያለው ኃይል ግን ተራሮችን የመንቀልና ታሪክን የመቀየር አቅም ያለው የሰማይ «ቪዛ» ነው። ዛሬ የዚህን ስም ጥልቀት፣ በሃይማኖታዊ ክፈፍ ውስጥ ብቻ ሳይሆን በመንፈሳዊው ዓለም ሕግጋት ውስጥ ያለውን ድንቅ ሚስጥር እንፈታዋለን።


አንድ አምባሳደር በባዕድ አገር ቆሞ ሲናገር፣ የሚከበረው የእርሱ ቁመት ወይም የንግግር ችሎታ ሳይሆን ከጀርባው ያለው የአገሩ መንግሥት ግርማ ነው። «በኢየሱስ ስም» ስንል እኛም ልክ እንደዚሁ የሰማያዊው መንግሥት ባለሙሉ ሥልጣን ወኪሎች መሆናችንን እያወጀን ነው። ይኽ "በኢየሱስ ስም" የሚለው ሐረግ "እኔ የራሴን ጉዳይ ለማስፈጸም አልመጣሁም፤ የመጣሁት በላከኝና ሥልጣኑን በሰጠኝ በክርስቶስ ስም ነው" የሚል የዲፕሎማሲያዊ ጥንካሬ መግለጫ ነው። ቅዱስ ጳውሎስ ይህንን የሥልጣን ልዕልና ሲገልጸው "በሰማይና በምድር ከምድርም በታች ያሉት ሁሉ ለኢየሱስ ስም ይንበረከኩ ዘንድ..." (ፊልጵስዩስ 2፡10) በማለት የስሙን ግርማ ያረጋግጥልናል።

ይሁን እንጂ የዚህን ስም ኃይል በተሳሳተ መንገድ የመረዳት አዝማሚያዎች በብዙዎች ዘንድ ይስተዋላሉ። ትልቁ ስህተት ይህንን ቅዱስ ስም እንደ "አስማታዊ ቃል" መቁጠር ነው። ብዙዎች «በኢየሱስ ስም» የሚለውን ሐረግ እንደ አንድ ፎርሙላ በመጠቀም፣ በራሳቸው ፈቃድና ስሜት የፈለጉትን ነገር እንዲያገኙ የሚያስገድዱ ይመስላቸዋል። ነገር ግን ይህ ስም የግል ምኞት ማስፈጸሚያ ሳይሆን፣ የመለኮታዊ ፈቃድ ማረጋገጫ ነው። ያለ ግንኙነት ስሙን መጥራት በሐዋርያት ሥራ 19 ላይ እንደተጠቀሱት እንደ አስቄዋ ልጆች ኃይል አልባ ከመሆን አልፎ ለጥቃት ያጋልጣል።

ስለዚህ ስም ጥልቀት የጥንት ቤተክርስቲያን አባቶችም አስገራሚ ምሥክርነት አላቸው። በሁለተኛው ክፍለ ዘመን የነበረውና የታላቁ የሐዋርያው ዮሐንስ ደቀ መዝሙር የሆነው ቅዱስ አግናጥዮስ (Ignatius of Antioch) ስሙን መጥራት ብቻ ሳይሆን ስሙን "መልበስ" እንደሚገባ ያስተምር ነበር። በተመሳሳይ ሁኔታ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ (John Chrysostom) ይህ ስም ለክፉ መናፍስት መባረሪያና ለታመሙት ፈውስ መሆኑን ሲገልጽ፣ ስሙን በእምነት መጥራት "የሰማይን ሠራዊት ለረድኤት መጥራት" እንደሆነ ያስተምር ነበር። ለአፈወርቅ፣ «በኢየሱስ ስም» ማለት ሰማያዊው ንጉሥ ለልጆቹ የሰጠውና ፈጽሞ የማይከሽፍ የመከላከያ መሣሪያ ነው።

በቴክኖሎጂው ዓለም የተቆለፉ መረጃዎችን ለመክፈት ትክክለኛውን የይለፍ ቃል ማወቅ የግድ እንደሚለው ሁሉ፣ በመንፈሳዊው ዓለምም በረከቶችን ለመቀበልና መሰናክሎችን ለመስበር የተሰጠን ብቸኛ የይለፍ ቃል «ኢየሱስ» የሚለው ስም ነው። ጌታችን ራሱ ሲያስተምር "እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ አብ በስሜ የምትለምኑትን ሁሉ ይሰጣችኋል።" (ዮሐንስ 16፡23) በማለት የስሙን ቁልፍነት አረጋግጦልናል። ስሙን መጥራት ሰማያዊው ቤተ መዛግብት ለጥያቄያችን ምላሽ እንዲሰጥ የሚያዝ ትእዛዝ መሆኑን ማስተዋል ይገባል።

ታላቁ የመጽሐፍ ቅዱስ መምህር ጆን ኔልሰን ዳርቢ (John Nelson Darby) ደግሞ ይኽንን ስም ከአማኙና ከክርስቶስ አንድነት አንፃር በጥልቀት ይተነትነዋል። ዳርቢ እንደሚለው፣ በኢየሱስ ስም መጸለይ ማለት ክርስቶስ በአብ ፊት ካለው ቦታና መብት ተካፋይ መሆን ማለት ነው። እኛ በራሳችን ኃጢአተኝነት ብንወቀስም፣ በስሙ ስንቀርብ ግን አብ የሚሰማን ልክ ልጁን ኢየሱስን እንደሚሰማው አድርጎ ነው። ዳርቢ ይህንን "በተወደደው በእርሱ ተቀባይነት ማግኘት" በማለት ይገልጸዋል።

ሌላኛው የተሳሳተ ምልከታ ስሙን እንደ "ጸሎት ማሳረጊያ ምልክት" ብቻ መመልከት ነው። ብዙ ጊዜ ጸሎታችንን "በኢየሱስ ስም አሜን" ብለን የምንዘጋው ንግግራችንን ለመጨረስ እንደምንጠቀምበት ነጥብ ነው። ነገር ግን ስሙ ጸሎቱን "የሚዘጋ" ሳይሆን "ወደ አምላክ ዙፋን የሚያደርስ" ድልድይ ነው። ሐዋርያው ጴጥሮስ ለሽባው ሰው "በናዝሬቱ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ተነሣና ተመላለስ" (ሐዋርያት ሥራ 3፡6) ባለ ጊዜ፣ ስሙ የማሳረጊያ ቃል ሳይሆን የአንካሳውን ማንነት የቀየረ የሕይወት ኃይል ነበር።

በጥንቱ ባሕል የአንድን ሰው ስም መጥራት ያንን ሰው "መውረስና መልበስ" ጭምር ነበር። እኛም በዚህ ስም ስንጠቀም፣ የክርስቶስን ጽድቅ እንደ ልብስ እየለበስን ነው። በእግዚአብሔር ፊት ስንቆም አብ የሚያየው የእኛን ስህተት ሳይሆን፣ በእኛ ላይ የታተመውን የልጁን ስም ነው። ይህ ስም ለድካማችን ጉልበት፣ ለኀዘናችን መጽናኛ፣ ለውድቀታችን ደግሞ የትንሣኤ ኃይል ሆኖ ይገለጣል።

እናም፣ «በኢየሱስ ስም» የሚለው ቃል የደካሞች መጠጊያ፣ የድል አድራጊዎች መዝሙርና የፍጥረት ሁሉ መገዣ ነው። ይኽ ስም ሲጠራ ዝምታ ይሰበራል፣ ሰንሰለቶች ይበጠሳሉ፣ ጨለማም ብርሃን ይሆናል። ይኽንን ስም በልማድ ሳይሆን በኃይል፣ በጥርጣሬ ሳይሆን በእምነት ስንጠራው፣ የማይቻለው ይቻላል፤ የማይታለፈውም መንገድ ይሆናል። በእርግጥም መጽሐፍ እንደሚል፦ "መዳን በሌላ በማንም የለም፤ እንድንበት ዘንድ ለሰዎች የተሰጠ ከሰማይ በታች ሌላ ስም የለምና" (ሐዋርያት ሥራ 4፡12)።

ስለዚህ ይህንን ስም ስትጠራው እንደ ተራ ቃል ሳይሆን፣ የሰማይን ደጅ እንደሚያንኳኳ የሥልጣን ቁልፍ አድርገህ ይዘህው ውጣ፤ ምክንያቱም በዚህ ስም ፊት የማይበረከክ ጉልበት፣ የማይፈታ እንቆቅልሽና የማይሸነፍ ጨለማ የለምና!

የኢየሱስ ጸጋ ከመንፈሳችሁ ጋር ይሁን!

. . . የሚፈስ ወርቃማ መስመር

 "ጌታ ሆይ! ደምህ በደም ሥሮቻችን ውስጥ ይፍሰስ፤ ሕይወትህም በሕይወታችን ውስጥ ይኑር። በደሙ የታተመ ማንኛውም ሰው የሞት መልአክ አይነካውም" ቅዱስ ኤፍሬም ሶርያዊ (Ephrem the Syrian)


የኢየሱስ ክርስቶስ ደም በመጽሐፍ ቅዱስ ገጾች ውስጥ የሚፈስ ወርቃማ መስመር ነው። ይህ ደም ከፍጥረት መጀመሪያ ጀምሮ እስከ ዘላለም መጨረሻ ድረስ የእግዚአብሔርን የማዳን ጥበብ የሚገልጥ ታላቅ ምስጢር ነው። ደሙ ዝም ብሎ የሕይወት ማለፍ ምልክት አይደለም፤ ይልቁንም የሞት ኃይል የተሸነፈበት፣ የሰማይና የምድር ሰላም የታወጀበት፣ እንዲሁም አማኞች ወደ ቅድስተ ቅዱሳኑ በድፍረት የሚገቡበት ብቸኛ በር ነው። መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚለው፦ "“እንግዲህ፥ ወንድሞች ሆይ፥ በመረቀልን በአዲስና በሕያው መንገድ ወደ ቅድስት በኢየሱስ ደም በመጋረጃው ማለት በሥጋው በኩል እንድንገባ ድፍረት ስላለን፥” (ዕብ. 10፥19-20)። በመስቀል ላይ የፈሰሰው እያንዳንዱ ጠብታ ደም፣ በእግዚአብሔር ፊት ዋጋችን ምን ያህል እጅግ ውድ እንደሆነ የሚናገር የፍቅር ፊርማ ነው።

የደሙ ኃይል እኛን ከኃጢአት ቅጣት ማዳን ብቻ ሳይሆን፣ ከኃጢአት መገኘትና ከሕሊና ወቀሳም ጭምር ነጻ የማውጣት ብቃት አለው። ጆን ኔልሰን ዳርቢ ስለ ደሙ ኃይል ሲናገር፣ ደሙ በእግዚአብሔር ፊት ያለንን ቦታ እንዴት እንደሚቀይረው እንዲህ በማለት በጥልቀት ይገልጻል፦ "ደሙ በእግዚአብሔር ፊት ያለኝን የኃጢአት ዕዳ ብቻ ሳይሆን የከፈለው፣ እኔን ራሴን በእግዚአብሔር ፊት ተቀባይነት እንዲኖረኝ አድርጎኛል።" ይህ ሐሳብ "የልጁም የኢየሱስ ክርስቶስ ደም ከኃጢአት ሁሉ ያነጻናል" (1 ዮሐንስ 1፡7) ከሚለው የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ጋር ይስማማል። እግዚአብሔር ወደ እኔ ሲመለከት የሚያየው ኃጢአቴን ሳይሆን፣ የልጁን የከበረ ደም ዋጋ ነው። ይኽ ማለት ደሙ እንደ መጋረጃ ኃጢአታችንን ይሸፍናል ብቻ ሳይሆን፣ እንደ አዲስ ፍጥረት አጥቦ ያነጻናል።

ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ደግሞ የደሙን ግርማ ሞገስና ውስጣዊ ውበት በምስጢር ይገልጠዋል። "ይህ ደም የነፍሳችን ውበት ነው፤ የልባችን ጌጥ ነው፤ የሕሊናችንም ብርሃን ነው" ይላል። ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ አክሎም የደሙን አስፈሪነት ለጠላት ሲገልጽ፦ "ይህን ደም ከተቀበልን በኋላ እንደ አንበሳ እሳት እንደሚተፉ ሆነን እንመለሳለን፤ ለሰይጣንም የሚያስፈራ እንሆናለን" ይላል። ይህ መንፈሳዊ ድል በመገለጥ መጽሐፍ ላይ፦ "እነርሱም ከበጉ ደም የተነሣ ከምስክራቸውም ቃል የተነሳ ድል ነሡት" (ራእይ 12፡11) ተብሎ ተጽፏል።

ቅዱስ ኤፍሬም፣ የክርስቶስን ደም ከታሪካዊ ክስተትነት ባለፈ ወደ ግላዊና ሕያው ግንኙነት ያመጣዋል። "ጌታ ሆይ! ደምህ በደም ሥሮቻችን ውስጥ ይፍሰስ" ሲል፣ ደሙ ከማንነታችን ጋር የሚዋሐድ ሰማያዊ ሕይወት መሆኑን ያሳየናል። የክርስቶስ ሕይወት በእኛ ሕይወት ውስጥ መኖር የሚጀምረው፣ በደሙ በኩል ካለው ከዚህ ጥልቅ መዋሐድ የተነሳ ነው።

በመቀጠልም ቅዱስ ኤፍሬም የደሙን የጥበቃ ኃይል ከብሉይ ኪዳኑ የፋሲካ በግ ደም ጋር በማመሳሰል "በደሙ የታተመ ማንኛውም ሰው የሞት መልአክ አይነካውም" ይላል። ይህም በኦሪት ዘጸአት ላይ ተጽፎ እንደሚገኘው፦ "ደሙም ባላችሁበት ቤቶች ምልክት ይሆንላችኋል፤ ደሙንም ባየሁ ጊዜ ከእናንተ አልፋለሁ" (ዘጸአት 12፡13) ከሚለው ታሪክ የመጣ ምስጢር ነው። ዛሬ ደግሞ የክርስቶስ ደም በነፍሳችንና በሥጋችን ላይ የታተመ ማኅተም ነው። ይህ ማኅተም ባለበት ቦታ የዘላለም ሞት ሥልጣን የለውም፤ የዲያብሎስም የጥፋት ቀስት አይደርስም።

ይህ የደሙ ኃይል አማኙን ከፍርሃት ነጻ ያወጣዋል። ሞት ለሌላው አስፈሪ ጨለማ ሲሆን፣ በክርስቶስ ደም የታተመው ሰው ግን ሞትን እንደ ድልድይ ብቻ ይመለከተዋል። ምክንያቱም በደም ሥሩ ውስጥ የሚፈሰው የክርስቶስ ሕይወት የማይሞትና የማይጠፋ ነው። ቅዱስ ጳውሎስ "በኢየሱስ ክርስቶስም በሆነው ቤዛነት በኩል እንዲያው በጸጋው ይጸድቃሉ" (ሮሜ 3፡24) እንዳለ፣ በደሙ የታተመ ሕይወት ሰማያዊ ጥበቃ የማይለየው የተከለለ ክልል ነው።

ስለሆነም፣ የክርስቶስ ደም መፍሰስ የፍቅር ጥግ ብቻ ሳይሆን የሕይወት ዋስትናችን ነው። ይህ ደም በውስጣችን ሕይወትን ይዘራል፣ በውጫችን ደግሞ ጥበቃን ያቆማል። እኛም እንደ ቅዱስ ኤፍሬም "ደምህ በደም ሥሮቻችን ውስጥ ይፍሰስ" እያልን በጸሎት ስንማጸን፣ ራሳችንን ለዘላለም ሕይወትና ለማይሸነፍ መለኮታዊ ጥበቃ አሳልፈን እየሰጠን ነው። ደሙ የፈሰሰው እንዲያው አይደለም፤ "በገዛ ደሙ የዋጃትን የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን" (ሐዋርያት ሥራ 20፡28) የራሱ አድርጎ ለማተም እንጂ።

የክርስቶስ ደም የኃጢአታችን መደምሰሻ ብቻ ሳይሆን፣ ከምድር ወደ ሰማይ የምንሻገርበት ብቸኛ የሕይወት ዋስትናችንና ለጠላት የማንበገዝበት ሰማያዊ ማኅተማችን ነው።

የጌታ ጸጋ ይብዛላችሁ!

በእርሱ ዘንድ የለውጥ ጥላ የለም . . . በሚለዋወጥ ዓለም ውስጥ የማይለወጠው ማንነት!

በዙሪያህ ያለውን ዓለም ተመልከት፤ ሁሉም ነገር በለውጥ ማዕበል ውስጥ ነው። የያዝከው ስልክ ያረጃል፣ ወቅቶች ይፈራረቃሉ፣ ስሜቶችህ እንደ አየር ሁኔታ ይዋዥቃሉ፣ እንዲያውም መስተዋት ውስጥ ስታይ የምታየው ፊትህ እንኳ ከዓመት ዓመት እየተለወጠ ነው። እኛ የፍጥረት ልጆች ሁልጊዜ "በመሆን" (Becoming) ሂደት ውስጥ ያለን ፍጥረታት ነን። ዛሬ ካለንበት ነገ የተሻለ ዕውቀት ልንጨብጥ፣ ወይም ደግሞ የነበረንን ጉልበትና ጤና ልናጣ እንችላለን። በእኛ ውስጥ ሁልጊዜም ገና ያልደረስንበት "ሊሆን የሚችል" (Potentiality) አቅም የታቀፈ ነው። ነገር ግን፣ በዚህ ሁሉ መለዋወጥ ውስጥ፣ በፍጹም የማይለወጥ፣ አንድም ስንዝር የማይናወጥ "ታላቅ ማንነት" አለ። በክርስቲያን ዕቅበተ-እምነት ስሙ መጀመሪያ ተጠቃሽ የሆነው ኖርማን ጋይስለር እንደሚያስረዳው፣ እግዚአብሔር "ፍጹም ሕያው" (Pure Actuality) ነው። ይህ ማለት 'እግዚአብሔር መሆን የሚገባው ሁሉ ቀድሞውኑ ነው' ማለት ነው! እርሱ ራሱን ለሙሴ ሲገልጥ "ያለና የሚኖር" (I AM WHO I AM) ብሎ መጥራቱ (ዘጸ. 3፥14)፣ እርሱ ምንጊዜም በሙላቱ የሚኖር፣ የማይጨምርና የማይቀንስ አምላክ መሆኑን ያረጋግጥልናል።


እግዚአብሔር "ፍጹም ሕያው" በመሆኑ በእርሱ ዘንድ "ገና ወደፊት የሚሆን" ወይም "ሊጨመር የሚችል" አዲስ ባሕርይ የለም። ለምን መሰለህ? ምክንያቱም እርሱ ቀድሞውኑ ፍጹም ሙላት ስለሆነ ነው! ለፀሐይ አዲስ ብርሃን መጨመር እንደማይቻል፣ ወይም ከባሕር ላይ ውኃ ማጉደል እንደማይቻል ሁሉ፣ በእግዚአብሔር ማንነት ላይ የሚጨመር አዲስ ጥበብም ሆነ የሚቀነስ ኃይል የለም። መዝሙረኛው የእግዚአብሔርን ዘላለማዊነትና ሙሉነት “ተራሮች ሳይወለዱ፥ ምድርም ዓለምም ሳይሠሩ፥ ከዘላለም እስከ ዘላለም ድረስ አንተ ነህ” (መዝ. 90፥2) በማለት ያወድሳል።

ይኽ እውነት ከእግዚአብሔር ጋር ያለንን ግንኙነት በምን ያህል ጥልቅ ሁኔታ እንደሚቀይረው እስኪ አስበው። እኛ ሰዎች ዛሬ የምንወደውን ሰው ነገ ልንጠላው እንችላለን፤ ዛሬ የገባነውን ቃል ነገ አቅም አጥተን ልናጥፈው እንችላለን። እግዚአብሔር ግን "ፍጹም ሕያው" በመሆኑ፣ ባሕርዩ ለሰከንድ እንኳ ዝንፍ አይልም። እግዚአብሔር ነገ ከዛሬ ይበልጥ ሊያፈቅርህ አይችልም፤ ምክንያቱም ፍቅሩ ቀድሞውኑ ፍጹም (Pure) ነው። እግዚአብሔር ነገ ከዛሬ ይበልጥ ሊያውቅ አይችልም፤ ምክንያቱም ዕውቀቱ የመጨረሻው ጫፍ ላይ ነው። ያዕቆብ ይኽንን ሲያጠናክር፣ “በጎ ስጦታ ሁሉ ፍጹምም በረከት ሁሉ ከላይ ናቸው፥ መለወጥም በእርሱ ዘንድ ከሌለ በመዞርም የተደረገ ጥላ በእርሱ ዘንድ ከሌለ ከብርሃናት አባት ይወርዳሉ” (ያዕ. 1፥17)። ይህ የእግዚአብሔር "ፍጹም መሆን" ወደ ሌላኛው ትልቅ ባሕርይው ማለትም ወደ "አለመለወጡ" (Immutability) ይመራናል። እርሱ በጊዜና በሁኔታዎች የማይታጠር፣ ሁልጊዜም በሙላቱ የሚኖር "ያለና የሚኖር" አምላክ ነው።

በዚህ በሚለዋወጥና በሚያናውጥ ዓለም ውስጥ፣ እንዲህ ዓይነት አምላክ መኖሩ ለክርስቲያን ትልቁ እፎይታ ነው። ኑሮህ ቢመሰቃቀል፣ ጤናህ ቢታወክ ወይም ዓለም ብትናወጥ፣ አንተ የተደገፍከው ግን ፈጽሞ አይናወጥም። እግዚአብሔር "ፍጹም ሕያው" ከሆነ፣ የሰጠን ተስፋና ለእኛ ያለው ፍቅርም እንደ ባሕርዩ የማይለወጥና ጽኑ ነው። "እኔ እግዚአብሔር አልለወጥም፤" (ሚል. 3፥6) የሚለው ቃል ከስሜታዊ መጽናኛነት ባለፈ፣ በእግዚአብሔር "ፍጹም መሆን" ላይ የተመሠረተ ጽኑ መለኮታዊ እውነት ነው። እርሱ ትናንትና ዛሬ እስከ ለዘላለምም ያው ነው (ዕብ. 13፥8)። ታዲያ ይህ የማይለወጥ አምላክ፣ በአንተ ሕይወት ውስጥ ስላለው ዕቅድና ዓላማ ምን ይል ይሆን?

የጌታ ሰላም ይብዛላችሁ!

የልብ ትርታን የሚሻው መለኮታዊ ጥሪ

 “የዝማሬህንም ጩኸት ከእኔ ዘንድ አርቅ፤ የመሰንቆህንም ዜማ አላደምጥም” (አሞጽ 5፥23)


በቅድስት ሰማያትና በምድር መረገጫ መካከል የሚሰማው መለኮታዊ ድምፅ፣ ከጥበብ ድርድር ይልቅ የልብን ንጽሕና አጥብቆ ይሻል። ነቢዩ አሞጽ በዘመናት ሰሌዳ ላይ የቀረጸው “የዜማህን ጩኸት ከእኔ አርቅ” የሚለው ኃይለኛ መለከት፣ አምልኮን በዜማ ውበት ለሚለኩ ሁሉ የሚሰነዘር መለኮታዊ ወቀሳ ነው። ይህ ቃል እግዚአብሔር ሙዚቃን እንደሚጠላ ሳይሆን፣ ከዜማው ጀርባ ያለውን "ባዶነት" እንደሚጸየፍ የሚያሳይ የሰማይ መለከት ነው። ይህ ቃል እግዚአብሔርን ደስ ለማሰኘት በምንተጋበት መድረክ ላይ፣ የቃላቶቻችን ድምቀት የውስጣችንን ጨለማ እንዳይሸፍን የሚሰጥ ከባድ ማስጠንቀቂያ ነው። የአሞጽ 5:23 ማስጠንቀቂያ የሚያስታውሰን፣ እግዚአብሔር ሙዚቃን ሳይሆን ሙዚቀኛውን፣ መዝሙርን ሳይሆን ዘማሪውን አስቀድሞ እንደሚመለከት ነው። እግዚአብሔር በቅንነት ባልተቃኘ ዝማሬ ውስጥ የሚሰማው ዜማን ሳይሆን የባዶነትን ጩኸት ነው፤ ምክንያቱም በሰማይ ሚዛን ላይ የድምፅ ውበት ሳይሆን የሕይወት ቅድስና ነው የሚመዘነው። ሕይወት በኃጢአት የዛገ ከሆነ፣ የበገናው ድምፅ በመለኮታዊው ጆሮ ዘንድ እንደ ዝገት ድምፅ ይቆጠራል።

በሰው ጆሮ ዘንድ እንደ ማር የሚጣፍጥ የበገና ድምፅ፣ ከጽድቅ ሕይወት ሲነጠል በፈጣሪ ፊት የሚረብሽ ጩኸት ይሆናል። ልብ በቅናት፣ በጥልና በዐመፅ በታወከበት ሁኔታ የሚቀርብ አምልኮ፣ እንደ ቃየል መስዋዕት መዓዛው ፊቱን ያዞራል። መዝሙረኛው ዳዊት በመዝሙሩ፣ “የእግዚአብሔር መስዋዕት የተሰበረ መንፈስ ነው” (መዝ. 51፥17) እንዳለ፣ ጌታ የሚፈልገው በከበረ ድምፅ የታጀበ ውሸትን ሳይሆን፣ በትሕትና የቀረበ እውነትን ነው። እግዚአብሔር የሚናፍቀው የአውታሮችን ንዝረት ሳይሆን የታማኝነትን ትርታ ነው፤ የሚሰማውም የዘማሪውን ዜማ ሳይሆን የሰውዬውን ማንነት ነው። “ይህ ሕዝብ በአፉ ወደ እኔ ይቀርባልና፥ በከንፈሮቹም ያከብረኛልና፥ ልቡ ግን ከእኔ የራቀ ነው” (ኢሳ. 29፥13) ተብሎ እንደተጻፈ፣ የከንፈር ፍሬ የልብ መስዋዕት ካልታከለበት ድምፁ እንደ ጠፋ መብረቅ፣ ውበቱም እንደ ደረቀ አበባ ነው።

እውነተኛ አምልኮ በቤተ መቅደስ ተጀምሮ በቤተ መቅደስ የሚያበቃ ሥነ-ሥርዓት አይደለም። ይልቁንም በጎዳና ላይ ለወደቀው የሚራራ፣ ለተበደለው ፍትሕን የሚሻ፣ በጨለማ ውስጥ ለሚኖሩ የጽድቅ ብርሃን የሚሆን ሕይወት ነው። እውነተኛም ዝማሬ የሚጀምረው ከጉሮሮ ሳይሆን ከፍትሕ ምንጭ ነው፤ አምልኮም ትርጉም የሚኖረው “ፍርድ እንደ ውኃ፥ ጽድቅም እንደማይደርቅ ፈሳሽ” (አሞጽ 5፥24) በሕይወታችን ውስጥ መፍሰስ ሲጀምር ብቻ ነው። እውነተኛ አምልኮ ማለት ለታረዘው ልብስ መሆን፣ ለተራበው እንጀራ መቆረስ፣ ለተበደለው ፍትሕ መቆም ነው። እነዚህ የጽድቅ ፍሬዎች በሌሉበት፣ በቤተ መቅደስ የሚደረግ ድምቀት ሁሉ "ባዶ ጩኸት" (1ቆሮ. 13፥1) ነው። ጌታ ከበገናው ድምፅ ይልቅ ለተበደለው የሚቆምለትን እጅ፣ ከዜማው መወራረድ ይልቅ ለተራበው የሚቆረስን ጽድቅ ይመርጣል። ያለ ጽድቅ የሚደረግ ሃይማኖታዊ ድምቀት ሁሉ እንደ መቃብር ላይ አበባ ነው፤ ውጪው ያምራል፣ ውስጡ ግን የሕይወት ትንፋሽ የለውም። እውነተኛው አምላኪ በመንፈስና በእውነት የሚሰግድ ነው፤ እርሱም ቃሉን በተግባር የሚተረጉም፣ ሕይወቱን ደግሞ በቅዱስ ወንጌል ቅኝት የቀመረ ጥበበኛ ነው።

ከአድማስ ባሻገር የሚሰማው የሰማይ ጌታ ጥሪ፣ ወደ ዜማዎቻችን ድምቀት ሳይሆን ወደ ልባችን ቅንነት እንድንመለስ ነው። ዝማሬያችን በሰማይ መቅደስ ፊት እንደ ጣፋጭ ዕጣን ይወጣ ዘንድ፣ መጀመሪያ የሕይወታችን አውታር በንስሐና በፍቅር መቃኘት አለበት። ያን ጊዜ የበገናችን ድምፅ የሰማይን ደጅ ይከፍታል፣ ዜማችንም ከመለኮታዊው መዝሙር ጋር ይዋሃዳል። ሕይወታችን ቅኔ፣ ተግባራችን ዜማ፣ ፍቅራችን ደግሞ ጣፋጭ የበገና ድምፅ ሆኖ በፈጣሪ ፊት ይቅረብ። ያን ጊዜ ዝማሬያችን ጩኸት መሆኑ አብቅቶ፣ በሰማያዊው መዝገብ ላይ እንደ ጣፋጭ መዓዛ ይጻፋል።

ጌታ ሆይ! ከከንፈር አምልኮ አርቀህ ወደ ልብ እውነት አቅርበን፤ ዝማሬያችንም በአንተ ፊት የፍቅር እንጉርጉሮ እንጂ ባዶ ጩኸት አይሁን። ጌታ ሆይ! የመዝሙሬ ድምፅ ሳይሆን የልቤ ትርታ ደስ ያሰኝህ። አፌ ሲዘምር እጄም ጽድቅን ይሥራ። 'በገናዬን' ከመምታቴ በፊት ውስጤን በቅዱስ መንፈስህ አቃኘው። እንደ ሰማያዊው መዝሙር፣ ሕይወቴ "ቅዱስ፣ ቅዱስ፣ ቅዱስ" የሚል የታማኝነት ምስክር ይሁን።

ጌታ ይፈውሰን!