አስተማሪው ወደ ክፍል ገብቶ በነጩ ሰሌዳ ላይ በያዘው ጥቁር ማርከር አንዲት ነጥብ አደረገ እና ወደ ተማሪዎቹ ዞር በማለት "ምን ይታያችኃል" በማለት ጠየቀ። ሁሉም በክፍል ውስጥ የተገኙ ተማሪዎች በሙሉ ሰሌዳ ላይ ስላዩት አንዲት ጥቁር ነጥብ ብዙ ማብራሪያ ለመምህራቸው ሰጡ።
መምህሩ በጸጥታ ካዳመጠ በኋላ ፈገግ አለና፣ “ሁላችሁም ትኩረታችሁ በጥቁር ነጥብ ላይ ነው፣ ነገር ግን አንዳችሁም በዙሪዋ ያለውን ሰፊ ነጭ ቦታ አልጠቀሳችሁም። ይኽች አንዲት ትንሽዬ ጥቁር ነጥብ ከዚህ ሰፊ ሰሌዳ አንጻር ስትታይ ምንም ናት። ነገር ግን የሁላችሁንም ትኩረት መዝረፍና መውሰድ የቻለችውም እሷ ናት።
በሰው ሕይወትም እንዲሁ ነው። ከብዙና ትላልቅ የጥንካሬ ጎኖች ይልቅ አንዲቷ ድካም ትኩረትን ትዘርፋለች። ነገር ግን ከሰውየው ካልታያችሁ ብዙ ጥንካሬና ትላልቅ አቅም አንጻር ያስተዋላችኋት ድካም ምንም ናት። ብዙ ሰዎች ህይወታቸውን የሚመሩት እንደዚሁ ይመስላል። ትንሽ በሆኑ ጥቁር ነጠብጣቦች፣ ጉድለቶች፣ ኃጢአቶች፣ ስቃዮች ወይም ውድቀቶች ላይ ብቻ በማተኮር በዙሪያቸው ያለውን የጸጋ፣ የመልካምነት እና የበረከት ሰፊ ቦታ ይረሳሉ።
ጥቂቷን የድካም ነጥብ አጉልተን ለመመልከት ስንገደድ ይስተዋላል። ሰው መበርታት ካለው መድከም፣ መቆም ካለው መውደቅ፣ መጎበዝ ካለው መስነፍ አለው። ድካምን ካጎላህ ድካምኽ ይታይሃል፣ ድካምኽ እንዳለ ብርታቱንና ጥንካሬውን ማስቀደም ከቻልክ ትለመልማለህ።
እግዚአብሔር እኛንም በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል የሚያየን እንዲሁ ነው።
እግዚአብሔር እኛን ሲመለከት በኃጢአትና በውድቀት የተሸፈነ ሰሌዳን አያይም። ትኩረታችንን የሳበው፣ በመስቀል ላይ የዓለምን እይታ የሳበው የልጁን ፍጹም ጽድቅ ይመለከታል። ኢየሱስ ያ ‘ጥቁር ነጥብ’፣ የሰማይ እና የምድር ትኩረት። የኃጢአታችንን ጨለማ በራሱ ላይ በማድረግ እንደዚኽ ሰሌዳ ነጭ እና ንጹህ ሆነን እንድንቆም አደረገን።
በሰው ዓይን፣ ያ ጥቁር ነጥብ ፍጽምናን የማይወክልና የማያመለክት ቢሆንም፣ ነገር ግን በእግዚአብሔር እቅድ ውስጥ፣ ያ ጥቁር ነጥብ፣ ኢየሱስ በመስቀል ላይ፣ የመዳን ማዕከል ሆነ። በአንድ ወቅት ኃጢአትን የሚያመለክት የነበረ አሁን የጸጋ ምልክት ሆነ። አሁን በእርሱ በኩል ኃጢአታችን አይታይም፤ የሕይወታችንን ሰሌዳ የሞላው የእርሱ ጽድቅ ብቻ ነው።
የተማሪዎቹ ዓይኖች ወደ ትንሿ ጥቁር ነጥብ እንደተሳቡ፤ ታሪክ ሁሉ እና የሰው ልጅ ወደ ክርስቶስ መስቀል እንጉድ ሲሳቡ ታይተዋል። ለዓለም ትንሽና የማይረባ የሚመስለው የእግዚአብሔር የማዳን ዕቅድ ማዕከል ሆነ። በዚያ መስቀል ላይ፣ እኛ በእግዚአብሔር የጽድቅ ብርሃን እንድንበራ ኢየሱስ የኃጢአትን ጨለማ በራሱ ላይ ወሰደ። እግዚአብሔር አሁን ሲመለከትን እድፈታችንን እና ውድቀታችንን አያይም፤ ኢየሱስን ያየዋል። በአንድ ወቅት ኃጢአትን የሚወክለው ጥቁር ነጥብ የድኅነት ምልክት ሆኗል። ስለዚህ፣ ልባችን ሁል ጊዜ በእግዚአብሔር ፊት ንፁህ በተደረግንበት፣ ይቅር በተባልንበት እና ሙሉ በሆንንበት በክርስቶስ ላይ ያተኩር።
በሚቀጥለው ጊዜ አንድ ትንሽ ጥቁር ነጥብ በሰፊ ነጭ ሰሌዳ ላይ ስታዩ፣ የኢየሱስ መስቀል በታሪክ ውስጥ የታየ ያ የብዙዎችን ዓይን ትኩረት የሳበ ነጥብ ነው። ይኽ ነጥብ ኃፍረታችንን ለመግለጥ የሚታይ ሳይሆን፣ የእግዚአብሔርን ምህረት እና የማዳን ፍቅሩን የሚገልጥ ነው።
የጽሑፉን ጥያቄያዊ ርዕስ "ማን ይታያችኋል?" በሚል ቀይሬዋለሁ!
የእግዚአብሔር ጸጋና ምህረት ይብዛላችሁ!
No comments:
Post a Comment