ወዳጄ የልብህ ሚዛን ፍትሃዊ የሚሆንልህ ምህረቱ ከኃጢያትህ ይልቅ ሚዛን ሲደፋልህ ነው። ክርስቶስ በጫንቃው ተሸክሞ መስቀል ላይ የተወጠረው የዓለምን ሁሉ ኃጢአት ይዞ ሊያስወግድ ነው። ዛሬ አንተ የምትሰራው ኃጢአት አዲስ ሳይሆን ካንተ በፊት እልፎች የሰሩትን ነው። ክርስቶስም ተሸክሞት የተሰቀለው የእግዚአብሔርን ቁጣ የተቀበለበትን ነው።
እስቲ ልብህን ወደ ሉቃስ ወንጌል ምዕራፍ 7 ስደድና ዘማዊት የነበረችውን ሴት አስብ። ይህች ሴት ገላዋን በመሸጥ የወጣትነት ዘመኗን ተጠቅማበታለች፤ ውበቷን የገንዘብ ማግኛ አድርጋዋለች። ዓመታቶችን በዝሙት ግብር ብትኖርም በሽርፍራፊ ሰዓት ወደ ጌታችን ኢየሱስ መጥታ በደሏ ሁሉ ተሰርዮላታል። ይህች ሴት በደል ኃጢአቷን ክርስቶስ እግር ስር በእንባና በለቅሶ ተናዘዘች እንጂ እንዴት ይህን ኃጢአት ታደርጋለች ብሎ የሚታዘብ ሰው ጋር ሸክሟን አላራገፈችም። ወንድሜ ሰው ጉልበት ላይ ኃጢአትህን ተናዘህ ስታበቃ የምትነሳው ከነኃጢአትህ ነው፤ ክርስቶስ እግር ስር ብቻ ነው የኃጢአትህን ሸክም ስታወርደው ቀና የምትለው፣ በአዲስ ማንነት፣ በንፁህ ህሊና፣ በተቀደሰ መንፈስ ሌላ የምትሆነው። ይህች ሴት ወደ ክርስቶስ ይዛ የመጣችው ከሰመጠችበት የኃጢአት ባህር የሚያወጣት ኢየሱስ ብቻ መሆኑን አምና ነው። ወንዶችን ለዝሙት ትማርክበት የነበረው መንገድ የንስሃ መድኃኒትን አዘጋጀችበት። ለሴሰኝነት ታይበት የነበረው ዓይኗ አሁን የንስሀ እንባ ያፈስሱ ዘንድ ተጠቀመችበት፤ ብዙዎችን በበደል ዓዘቅት ይወድቁ ዘንድ ያጠመደችበት ፀጉሯ አሁን የጌታችንን እግር አበሰችበት፤ ዘማውያንን የማረከችበትን ሽቱ አሁን የጌታችንን እግር ቀባችበት።
ወዳጄ "ንፁህ ህሊና ምቹ ትራስ ነው" ሲባል ሰምቻለሁ፤ እኔም በዚህ ንግግር ተስማምቼበት አንተን እንዲህ ለማለት ተነሳስቻለሁ -- ፈጥነህ ተነሳ በስርቆት እግዚአብሔርን አሳዝነኸዋል? ያለ አግባብ የወሰድከውን ገንዘብ ለባለቤቱ መልስ፤ ይልቅ ጨምረህ ስጥ። አንቺስ እህቴ በአንደበትሽ ሰዎችን በማንጓጠጥ በመስደብ ፈጣሪሽን እንዲሁም ባልንጀራሽን አሳዝነሻል? ይቅር በዪ በበደለው አንደበትሽ ፀሎትን ፀልዪበት፣ የሚረግሙሽን መርቂበት።
ከበደልህ ጋር መኖርህ ከሰለችህ ፈጥነህ ወደ ኢየሱስ ና። እርሱ ወደእውነተኛ ንሰሃ መርቶህ በንፁህ ህሊና እንድትኖር ይረዳኻል፤ በእኛና በእግዚአብሔር መካከል የተገነባውን ኃጢአት ይደረምሳል።
እርጉዝ ሴት ለመውለድ አንደምትቸኩል ሁሉ እግዚአብሔርም ሰውን ለመማር ይቸኩላል።
የጌታ ኢየሱስ ጸጋ ከሁላችሁ ጋር ይሁን!
No comments:
Post a Comment