Tuesday, October 14, 2025

ምን ይታያችኋል?

አስተማሪው ወደ ክፍል ገብቶ በነጩ ሰሌዳ ላይ በያዘው ጥቁር ማርከር አንዲት ነጥብ አደረገ እና ወደ ተማሪዎቹ ዞር በማለት "ምን ይታያችኃል" በማለት ጠየቀ። ሁሉም በክፍል ውስጥ የተገኙ ተማሪዎች በሙሉ ሰሌዳ ላይ ስላዩት አንዲት ጥቁር ነጥብ ብዙ ማብራሪያ ለመምህራቸው ሰጡ። 


መምህሩ በጸጥታ ካዳመጠ በኋላ ፈገግ አለና፣ “ሁላችሁም ትኩረታችሁ በጥቁር ነጥብ ላይ ነው፣ ነገር ግን አንዳችሁም በዙሪዋ ያለውን ሰፊ ​​ነጭ ቦታ አልጠቀሳችሁም። ይኽች አንዲት ትንሽዬ ጥቁር ነጥብ ከዚህ ሰፊ ሰሌዳ አንጻር ስትታይ ምንም ናት። ነገር ግን የሁላችሁንም ትኩረት መዝረፍና መውሰድ የቻለችውም እሷ ናት።

በሰው ሕይወትም እንዲሁ ነው። ከብዙና ትላልቅ የጥንካሬ ጎኖች ይልቅ አንዲቷ ድካም ትኩረትን ትዘርፋለች። ነገር ግን ከሰውየው ካልታያችሁ ብዙ ጥንካሬና ትላልቅ አቅም አንጻር ያስተዋላችኋት ድካም ምንም ናት። ብዙ ሰዎች ህይወታቸውን የሚመሩት እንደዚሁ ይመስላል። ትንሽ በሆኑ ጥቁር ነጠብጣቦች፣ ጉድለቶች፣ ኃጢአቶች፣ ስቃዮች ወይም ውድቀቶች ላይ ብቻ በማተኮር በዙሪያቸው ያለውን የጸጋ፣ የመልካምነት እና የበረከት ሰፊ ቦታ ይረሳሉ።

ጥቂቷን የድካም ነጥብ አጉልተን ለመመልከት ስንገደድ ይስተዋላል። ሰው መበርታት ካለው መድከም፣ መቆም ካለው መውደቅ፣ መጎበዝ ካለው መስነፍ አለው። ድካምን ካጎላህ  ድካምኽ ይታይሃል፣ ድካምኽ እንዳለ ብርታቱንና ጥንካሬውን ማስቀደም ከቻልክ ትለመልማለህ።

እግዚአብሔር እኛንም በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል የሚያየን እንዲሁ ነው።

እግዚአብሔር እኛን ሲመለከት በኃጢአትና በውድቀት የተሸፈነ ሰሌዳን አያይም። ትኩረታችንን የሳበው፣ በመስቀል ላይ የዓለምን እይታ የሳበው የልጁን ፍጹም ጽድቅ ይመለከታል። ኢየሱስ ያ ‘ጥቁር ነጥብ’፣ የሰማይ እና የምድር ትኩረት። የኃጢአታችንን ጨለማ በራሱ ላይ በማድረግ እንደዚኽ ሰሌዳ ነጭ እና ንጹህ ሆነን እንድንቆም አደረገን።

በሰው ዓይን፣ ያ ጥቁር ነጥብ ፍጽምናን የማይወክልና የማያመለክት ቢሆንም፣ ነገር ግን በእግዚአብሔር እቅድ ውስጥ፣ ያ ጥቁር ነጥብ፣ ኢየሱስ በመስቀል ላይ፣ የመዳን ማዕከል ሆነ። በአንድ ወቅት ኃጢአትን የሚያመለክት የነበረ አሁን የጸጋ ምልክት ሆነ። አሁን በእርሱ በኩል ኃጢአታችን አይታይም፤ የሕይወታችንን ሰሌዳ የሞላው የእርሱ ጽድቅ ብቻ ነው።

የተማሪዎቹ ዓይኖች ወደ ትንሿ ጥቁር ነጥብ እንደተሳቡ፤ ታሪክ ሁሉ እና የሰው ልጅ ወደ ክርስቶስ መስቀል እንጉድ ሲሳቡ ታይተዋል። ለዓለም ትንሽና የማይረባ የሚመስለው የእግዚአብሔር የማዳን ዕቅድ ማዕከል ሆነ። በዚያ መስቀል ላይ፣ እኛ በእግዚአብሔር የጽድቅ ብርሃን እንድንበራ ኢየሱስ የኃጢአትን ጨለማ በራሱ ላይ ወሰደ። እግዚአብሔር አሁን ሲመለከትን እድፈታችንን እና ውድቀታችንን አያይም፤ ኢየሱስን ያየዋል። በአንድ ወቅት ኃጢአትን የሚወክለው ጥቁር ነጥብ የድኅነት ምልክት ሆኗል። ስለዚህ፣ ልባችን ሁል ጊዜ በእግዚአብሔር ፊት ንፁህ በተደረግንበት፣ ይቅር በተባልንበት እና ሙሉ በሆንንበት በክርስቶስ ላይ ያተኩር።

በሚቀጥለው ጊዜ አንድ ትንሽ ጥቁር ነጥብ በሰፊ ነጭ ሰሌዳ ላይ ስታዩ፣ የኢየሱስ መስቀል በታሪክ ውስጥ የታየ ያ የብዙዎችን ዓይን ትኩረት የሳበ ነጥብ ነው። ይኽ ነጥብ ኃፍረታችንን ለመግለጥ የሚታይ ሳይሆን፣ የእግዚአብሔርን ምህረት እና የማዳን ፍቅሩን የሚገልጥ ነው።

የጽሑፉን ጥያቄያዊ ርዕስ "ማን ይታያችኋል?" በሚል ቀይሬዋለሁ!

የእግዚአብሔር ጸጋና ምህረት ይብዛላችሁ!

በደልህን ይምረዋል

ወዳጄ የልብህ ሚዛን ፍትሃዊ የሚሆንልህ ምህረቱ ከኃጢያትህ ይልቅ ሚዛን ሲደፋልህ ነው። ክርስቶስ በጫንቃው ተሸክሞ መስቀል ላይ የተወጠረው የዓለምን ሁሉ ኃጢአት ይዞ ሊያስወግድ ነው። ዛሬ አንተ የምትሰራው ኃጢአት አዲስ ሳይሆን ካንተ በፊት እልፎች የሰሩትን ነው። ክርስቶስም ተሸክሞት የተሰቀለው የእግዚአብሔርን ቁጣ የተቀበለበትን ነው።


እስቲ ልብህን ወደ ሉቃስ ወንጌል ምዕራፍ 7 ስደድና ዘማዊት የነበረችውን ሴት አስብ። ይህች ሴት ገላዋን በመሸጥ የወጣትነት ዘመኗን ተጠቅማበታለች፤ ውበቷን የገንዘብ ማግኛ አድርጋዋለች። ዓመታቶችን በዝሙት ግብር ብትኖርም በሽርፍራፊ ሰዓት ወደ ጌታችን ኢየሱስ መጥታ በደሏ ሁሉ ተሰርዮላታል። ይህች ሴት በደል ኃጢአቷን ክርስቶስ እግር ስር በእንባና በለቅሶ ተናዘዘች እንጂ እንዴት ይህን ኃጢአት ታደርጋለች ብሎ የሚታዘብ ሰው ጋር ሸክሟን አላራገፈችም። ወንድሜ ሰው ጉልበት ላይ ኃጢአትህን ተናዘህ ስታበቃ የምትነሳው ከነኃጢአትህ ነው፤ ክርስቶስ እግር ስር ብቻ ነው የኃጢአትህን ሸክም ስታወርደው ቀና የምትለው፣ በአዲስ ማንነት፣ በንፁህ ህሊና፣ በተቀደሰ መንፈስ ሌላ የምትሆነው። ይህች ሴት ወደ ክርስቶስ ይዛ የመጣችው ከሰመጠችበት የኃጢአት ባህር የሚያወጣት ኢየሱስ ብቻ መሆኑን አምና ነው። ወንዶችን ለዝሙት ትማርክበት የነበረው መንገድ የንስሃ መድኃኒትን አዘጋጀችበት። ለሴሰኝነት ታይበት የነበረው ዓይኗ አሁን የንስሀ እንባ ያፈስሱ ዘንድ ተጠቀመችበት፤ ብዙዎችን በበደል ዓዘቅት ይወድቁ ዘንድ ያጠመደችበት ፀጉሯ አሁን የጌታችንን እግር አበሰችበት፤ ዘማውያንን የማረከችበትን ሽቱ አሁን የጌታችንን እግር ቀባችበት።

ወዳጄ "ንፁህ ህሊና ምቹ ትራስ ነው" ሲባል ሰምቻለሁ፤ እኔም በዚህ ንግግር ተስማምቼበት አንተን እንዲህ ለማለት ተነሳስቻለሁ -- ፈጥነህ ተነሳ በስርቆት እግዚአብሔርን አሳዝነኸዋል?  ያለ አግባብ የወሰድከውን ገንዘብ ለባለቤቱ መልስ፤ ይልቅ ጨምረህ ስጥ። አንቺስ እህቴ በአንደበትሽ ሰዎችን በማንጓጠጥ በመስደብ ፈጣሪሽን እንዲሁም ባልንጀራሽን አሳዝነሻል? ይቅር በዪ በበደለው አንደበትሽ ፀሎትን ፀልዪበት፣ የሚረግሙሽን መርቂበት።

ከበደልህ ጋር መኖርህ ከሰለችህ ፈጥነህ ወደ ኢየሱስ ና። እርሱ ወደእውነተኛ ንሰሃ መርቶህ በንፁህ ህሊና እንድትኖር ይረዳኻል፤ በእኛና በእግዚአብሔር መካከል የተገነባውን ኃጢአት ይደረምሳል።

እርጉዝ ሴት ለመውለድ አንደምትቸኩል ሁሉ እግዚአብሔርም ሰውን ለመማር ይቸኩላል።

የጌታ ኢየሱስ ጸጋ ከሁላችሁ ጋር ይሁን!

ከክርስቶስ ጋር ህብረት

 ክርስትና ዋና ክፍል በቀላሉ የምንስማማባቸው እምነቶች ዝርዝር ወይም መከተል ያለብን 'ሃይማኖታዊ' ልማዶች አይደሉም። ህያውና በሆነ፣ በሚለውጥ ህብረት ውስጥ ከክርስቶስ ጋር መሆን ነው። የኃጢያት ይቅርታን ማግኘት በራሱ ውድ የሆነ ነገር ቢሆንም መዳን ግን ከዚህ በላይ ነው፤ ከእግዚአብሔር ልጅ ጋር አንድ የሆንበት እውነታ ነው።  ጳውሎስ ይህንን እውነት ሲጽፍ “ማንም በክርስቶስ ቢሆን አዲስ ፍጥረት ነው፤ አሮጌው ነገር አልፎአል፤ እነሆ፥ አዲስ ሆኖአል” (2ቆሮ. 5፡17) ሲል ጽፏል። በዚህ አንድነት፣ በክርስቶስ መስቀል፣ ሞት፣ መቃብር፣ ትንሣኤ እና ዕርገት ተሳታፊ ሆነናል። ከክርስቶስ ጋር ተሰቅላችኋል፣ ከክርስቶስ ጋር ሞታችኋል፣ ከክርስቶስ ጋር ተቀብራችኋል፣ ከክርስቶስ ጋር ሕይወትን አግኝታችኋል፣ ከክርስቶስ ጋር ተነስታችኋል፣ ከክርስቶስ ጋር . . . የተካፈልናቸው ሌሎች በረከቶች የክርስትና መለዮ ናቸው። እናም በዚህ መከራው መከራችን፤ ሞቱ ሞታችን፤ መቀበሩ መቀበራችን፤ ሕይወቱ ሕይወታችን፤ ትንሳኤው ትንሳኤያችን፤ ክብሩ ክብራች ሆኗል። ምን ቸገረኽ! በቃ፣ የእርሱ ታሪክ ታሪካችን ሆኗል።


በዚህ እውነታ ላይ ሁለንተናችንን ሰጥተን ስናሰላስል መፅናናትን የምናገኝ ሲሆን። ፈጽሞ ልንተው በማንችልበት ኅብረት ውስጥ መሆናችንን እንረዳለን፤ ክርስቶስ ሁልጊዜ ከእኛ ጋር እንዲሁም በእኛ ውስጥ እንደሆነ እንገነዘባለን። ይኽ ደግሞ መጽናናትን ያመጣል፣ ዕረፍትን ይሰጣል፣ የነፍስ ሰላምን ይጠብቃል። ከክርስቶስ ጋር ኅብረት እንዳለን በሚገልጽ እውነት ላይ ማሰላሰል መጽናናትን የሚሰጠን ቢሆንም፣ በሌላ መንገድ ደግሞ ሕይወታችን ምን መምሰል እንዳለበት የሚሞግተንም ጭምር ነው። ከእርሱ ጋር ከተባበርን ትዳራችን፣ ጓደኞቻችን፣ ስራችን እና አሳባችን እንኳን ሳይቀር የእርሱን ህልውና የሚያንፀባርቅ መሆን አለበት። በዚህም ምክንያት "ክርስቶስ በእኔ እንዳለ ሆኜ እየኖርኩ ነውን? ሌሎች የእርሱን ባህሪ በእኔ ውስጥ እያዩ ነውን?" በሚሉ ጥያቄዎች ይሞግተናል።

ከክርስቶስ ጋር ኅብረት ለሥነ-መለኮት መምህራንና ተማሪዎች ብቻ የተሰጠ ረቂቅ ትምህርት አይደለም።  የክርስትና ሕይወት የልብ ምት ነው። ሁሉንም ነገር የሚቀይር እውነት ነው። አሳቦቻችንን፣ አነጋገራችንን፣ አካሄዳችንን በቃ ሁሉን የሚቀይር ነው።

እውነተኛና ሕያው የሆነ እርሱ ወደጥልቅ መረዳት ውስጥ ይከተን ዘንድ፣ አብሮነቱ እስኪሰማን ድረስ ያሳርፈን ዘንድ፣ ጸጋውና ምህረቱ ይብዛልን!

የሰበከው ኢየሱስና የተሰበከው ክርስቶስ

በገሊላ አቧራማ መንገዶችን እየተራመደ፤ ለእግሩ ምቾት ሳር አንጠፉልኝ ሳይል በእነዚያ ኮረብቶች ላይ እየተመላለሰ የሰበከው ኢየሱስ እርሱ ሥጋ የሆነው ቃል ነው። እግዚአብሔር በሰዎች መካከል ሆነ። ለደከሙ ነፍሳት ሕይወትን ተረከ። ከዙፋኑ ሳይሆን ከዚሁ ከአንዲት መንደር መንገድ እምብርት ላይ ቆሞ በርኅራኄ ሰበከ። እርሱ የሆኑ ንድፈ ሐሳቦችን ሳይሆን እውነትን ሰበከ፤ የእውነተኛውን አምላክ ልብ ገለጠ። የተናገረው ቃል ሁሉ ጨለማን የሚያጋልጥ ብርሃን፣ እስራትን የበጣጠሰና ሰንሰለት የሰበረ ፍቅር፤ ሰዎችን ነፃ የሚያወጣ እውነትን ይዞ ነበር።


ያ ሰባኪው ኢየሱስ እንዲህ ብሎ ነበር “እናንተ ደካሞች ሸክማችሁ የከበደ ሁሉ፥ ወደ እኔ ኑ፥ እኔም አሳርፋችኋለሁ” (ማቴ. 11፥28) ይኽ የጥሪ ድምጽ ዛሬም ያለማቋረጥ ይሰማል። አንዴ የተነገረ፣ ለሁል ጊዜ የሚሰማ፤ ለጥቂቶች የተነገረ ለብዙዎች የተስተጋባ ጥሪ። አስባችሁታል፣ መልእክቱ' ኮ 'ወደ እኔ ኑ' ነው። ግንኙነትን የሚያስጀምር፣ መጠጊያን የሚያኖር፣ ዕረፍትን የሚሰጥ ጥሪ ነው። መሸሸጊያ ስፍራን የሚሰጥ ጥሪ ነው። ይኼ ሰባኪው ኢየሱስ ለከሳሾቹ ባሳየው በምሕረቱ፣ በእንባው እና በዝምታው የአብን ፊት ገለጠ። ከእግዚአብሔር ጋር መኖርን እንደ ሩቅ ተስፋ ሳይሆን ንስሐ ለሚገባ ልብ ሁሉ ሕያው የሆነ እውነታ አድርጎ ሰበከ።

ከሞቱና ከትንሳኤው በኋላ ግን ያ ይሰብክ የነበረ ድምጽ ራሱ የሚሰበክ መልእክት ሆነ። አሁን ሐዋርያቱ “መጥታችሁ እርሱን ስሙት” ብቻ አላሉም “በእርሱ እመኑ” እያሉ በጩኸት ተናገሩ። የተሰበከው ክርስቶስ ያው ኢየሱስ ነበር።

መስቀሉ የመቤዠት መልእክትን ለዘላለም የሚያስተጋባበት መድረክ ሆነ። ጳውሎስ “የተሰቀለውን ክርስቶስን እንሰብካለን” (1ኛ ቆሮ. 1፥23) በማለት እርሱን ሰበከ። የተሰበከው ክርስቶስ ኃጢአትን ያሸነፈው አዳኝ፣ በመንፈሱ አሁን በእኛ የሚኖር ከሙታን መካከል የተነሳው ጌታ ነው። እርሱ ያው ኢየሱስ ነው። ከአሁን በኋላ በጊዜ ወይም በቦታ የተገደበ ሳይሆን በሚያምን ሁሉ ልብ ውስጥ የሚገኝ ነው።

ሰባኪውን ኢየሱስን ማወቅ በትህትና፣ በምህረት እና በንጽህና እንዴት መመላለስ እንዳለብን መማር ነው። የተሰበከውን ክርስቶስ ማመን ያለ ፍርሃት፣ በደስታ እና በኃይል በድል መኖር ነው። ሁለቱም በልባችን ሲዋሃዱ የወንጌልን ሙላት እናያለን፤ ጸጋ እና እውነት፣ ፍቅር እና ኃይል፣ መስቀል እና ትንሳኤ ወለል ብሎ ያታየናል።

“ኢየሱስ ክርስቶስ ትናንትና ዛሬ እስከ ለዘላለምም ያው ነው።” — ዕብ. 13፥8