Thursday, October 24, 2024

“በዚች ዓመት ደግሞ ተዋት”



“እርሱ ግን መልሶ፦ ጌታ ሆይ፥ ዙሪያዋን እስክኰተኵትላትና ፋንድያ እስካፈስላት ድረስ በዚች ዓመት ደግሞ ተዋት። ወደ ፊትም ብታፈራ፥ ደኅና ነው . . .” (ሉቃ. 13፥8-9)

ዘመንን የሰጠ እርሱ እድሜያችንን እየቆጠርን እንድንኖር አደረገ። እድሜን መቁጠር በራሱ መጥፎ አይደለም፤ በእድሜያችን መስራት ያለብንን አለመስራት ነው መጥፎና ክፉ የሆነው። ከላይ ካነበብነው ክፍል ውስጥ የእግዚአብሔርን ምሕረት መመልከት እንችላለን። “በዚች ዓመት ደግሞ ተዋት” እግዚአብሔር ከምሕረቱ የተነሳ አዲስ ቀንን እንድናይ ያደርገናል። ለምን? ለእርሱ የሚሆንን ፍሬ እንድናፈራ። ፍሬውንም ማፍራት እንድንችል የሚያደርገንን  ጸጋውንም አብሮ ነው የሚሰጠን። ሌላ ምን ይባላል ተመስገን ነው እንጂ!

ሕይወታችን እግዚአብሔር የራሱን ታሪክ የሚጽፍበት መጽሐፍ ነው። የራሳችንን ታሪክ ለመጻፍ አንሞክር፤ የእኛ ሕይወት አይደለምና። የራሳችን የሆነን ነገር ለመጻፍ ስንሞክር ነው መኖር የሚገባንን የማንኖረው፣ መሆን የሚገባንን የምንሆነው። ስለዚህ እኛጋ ያለ የእግዚአብሔር ታሪክ ነው። እያንዳንዱ ቀናት የመጽሐፉን ገጽ፤ ዓመታቱ ደግሞ አዲስ ምዕራፍ ጅማሮ እንደሆኑ አስባለው። እናም አዲስ ዓመት ሲመጣ እግዚአብሔር አዲስ ምዕራፍ ጀምሮ ነውና፤ አዲሱ ምዕራፍ

💪ለክርስቶስ ወንጌል እንደሚገባ የምንኖርበት ይሁን።

💪ለወንጌል እውነት እንደአንድ ሰው ሆነን የምጋደልበት ይሁን።

💪በአንድ ልብ በአንድ አሳብ በአንድ መንፈስና በአንድ ነፍስ መኖር ይሁንልን።

💪ለእግዚአብሔር የማይሆኑ ነገሮችን በቃ የማለት አቅም የምንለብስበት ይሁን።

💪የጀመርነው ነገር እስከፍጻሜው ይድረስልን።

💪ያዘንበት ነገር ደስታ ይዞልን ይምጣ።

💪የተሸነፈው ማንነታችን ድልን ያጎናጽፈን።

💪ፍሬን ማፍራት ሥራ ይሁንልን።

💪የደረቀው ነገራችን ይለምልም።

💪ቤታችን የበረከት፤ እንግዳ የሚስተናገድበት ቤት ይሁን።

💪የወለድነው ይደግ።

💪ያላገባችሁ ከእግዚአብሔር የሆነ ትዳር ያግኛችሁ።

የእግዚአብሔር ምሕረት፣ ፍቅርና ጸጋ በሕይወት ዘመናችሁ ሁሉ ይብዛ!

https://t.me/anidSew/62

No comments:

Post a Comment