እግዚአብሔር መልካም ነው። መልካምነቶቹ ከሚገለጽባቸው መንገዶች አንዱ ምሕረቱ ነው። ምሕረት ስጦታ ነው። ምሕረት ስላሳየነው መልካምነት ምላሽ ተደርጎ የሚሰጥ አይደለም። ምሕረት የሰጪውን ልብ የሚያሳይ ነው። አበቃልኝ፣ ሞትኩ፣ ጠፋው፣ ተስፋ የለኝም ያለን ሰው እውነተኛ ተስፋ የሚሰጥ ነው። በነጻነት የመኖር ዕድልን የሚያጎናጽፍ ነው። ከእግዚአብሔር የምንቀበለው ምሕረት “የእግዚአብሔር ምሕረት” ይባላል። እርሱ ዘንድ ወዳለ “ጸጋ” ወደተባለ ዙፋን ስንቀርብ ምሕረቱን እንቀበላለን።
እግዚአብሔር የሚምረን በፈጣሪነት ግዴታው አይደለም። ምሕረት ማድረግ ባሕርይው ስለሆነ ነው። ፍቅር ስለሆነ ነው። በእግዚአብሔር ዘንድ ትንሽ ወይም ጥቂት የሚባል ምሕረት የለም። ምሕረቱም የማያልቅ ዕልቆ ቢስ ነው። ምሕረቱን የሚለካ አይደለም። ምሕረቱን የሚለካ መለኪያ ምንም የለም።ምሕረቱ እጅግ የበዛ ታላቅ ነው። ለብዙ ዓመታት የተሰሩ ታላላቅ ኃጢአቶችን የሚምር ነው። የእርሱ ምሕረት እጅግ የተትረፈረፈ ነው። ሚሊዮኖች ተቀብለውታል። ጥቂቶች ይኖሩበታል። ዛሬም አዲስ ነው። ሙሉ ነው። በነጻም የምናገኘው ነው።
የእርሱ ምሕረት ሁል ጊዜ በዙሪያችን ነው። ቀኑን ሙሉ የሚጠብቀን ምሕረቱ ነው። ፀሀይን ሸኝቶ ጨረቃን የሚያሳየን ምሕረቱ ነው። ከሌሊቱ ግርማ የሚያስመልጠን ምሕረቱ ነው። በጠዋት ፀሀይ ከመውጣቷ በፊት የሚቀበለን የጠዋት ስጦታችን ምሕረቱ ነው። ለፈተና እጃችንን እንዳንሰጥ ይጠብቀናል። አስቸጋሪ በሆኑ ሁኔታዎች ውስጥ እንዳንሰጥም መንሳፈፊያችን ነው። በኑሮ ማዕበል ተገፍተን እንዳንወድቅ መቆሚያ ምርኩዛችን ነው።
ምሕረት እየደማ ላለ ልብ ደምን የሚይቆም ዘይት ነው። ለዛለና ለደከመ፣ መሄድ ላቀተው እግር የንጉስ ሰረገላ ነው። ለሚንቀጠቀጠው ለፈራው ልብህ የፍቅር ዕቅፍ ነው።
😔ከጥፋትህ የተነሳ ሰው ሁሉ አበዛኸው ብሎህ ትቶህ ሄዷል። ብዙዎችን ምሕረት አድርጉልኝ ስትላቸው ቢደረግልህም ያው ነኽ አትቀየረም በማለት የመለወጥ ተስፋ እንደሌለህ ተናግረውብህ ይሆናል። ነገር ግን እነርሱ አልፈጠሩህም። የፈጠረህ እግዚአብሔር ነው። መቼም አበዛኸው የማይልህ። ሁሌም ይቅር የሚል እርሱ ነው። ፍጹም በሆነ ፍቅር የሚቀበልህ እርሱ ነው። እርሱ ፊት መቆምን አትፍራ፡፡ እርሱ ምስጢረኛህ ነውና፡፡ ሁል ጊዜም እጆቹ ለምሕረት የተዘረጉ ናቸው፡፡ ምህረቱ እስከ ሺህ ትውልድ ድረስ የሚጠብቅ የታመነ አምላክ እንደሆነ እወቅ፡፡ . . . . እግዚአብሔርን አመስግኑ፡፡
የእግዚአብሔር ምሕረት ከሁላችሁ ጋር ይሁን!
https://t.me/anidSew