Thursday, October 24, 2024

አቤት የእግዚአብሔር ምሕረት

እግዚአብሔር መልካም ነው። መልካምነቶቹ ከሚገለጽባቸው መንገዶች አንዱ ምሕረቱ ነው። ምሕረት ስጦታ ነው። ምሕረት ስላሳየነው መልካምነት ምላሽ ተደርጎ የሚሰጥ አይደለም። ምሕረት የሰጪውን ልብ የሚያሳይ ነው። አበቃልኝ፣ ሞትኩ፣ ጠፋው፣ ተስፋ የለኝም ያለን ሰው እውነተኛ ተስፋ የሚሰጥ ነው። በነጻነት የመኖር ዕድልን የሚያጎናጽፍ ነው። ከእግዚአብሔር የምንቀበለው ምሕረት “የእግዚአብሔር ምሕረት” ይባላል። እርሱ ዘንድ ወዳለ “ጸጋ” ወደተባለ ዙፋን ስንቀርብ ምሕረቱን እንቀበላለን።

እግዚአብሔር የሚምረን በፈጣሪነት ግዴታው አይደለም። ምሕረት ማድረግ ባሕርይው ስለሆነ ነው። ፍቅር ስለሆነ ነው።  በእግዚአብሔር ዘንድ ትንሽ ወይም ጥቂት የሚባል ምሕረት የለም። ምሕረቱም የማያልቅ ዕልቆ ቢስ ነው። ምሕረቱን የሚለካ አይደለም። ምሕረቱን የሚለካ መለኪያ ምንም የለም።

ምሕረቱ እጅግ የበዛ ታላቅ ነው። ለብዙ ዓመታት የተሰሩ ታላላቅ ኃጢአቶችን የሚምር ነው። የእርሱ ምሕረት እጅግ የተትረፈረፈ ነው። ሚሊዮኖች ተቀብለውታል። ጥቂቶች ይኖሩበታል። ዛሬም አዲስ ነው። ሙሉ ነው። በነጻም የምናገኘው ነው።

የእርሱ ምሕረት ሁል ጊዜ በዙሪያችን ነው። ቀኑን ሙሉ የሚጠብቀን ምሕረቱ ነው። ፀሀይን ሸኝቶ ጨረቃን የሚያሳየን ምሕረቱ ነው። ከሌሊቱ ግርማ የሚያስመልጠን ምሕረቱ ነው። በጠዋት ፀሀይ ከመውጣቷ በፊት የሚቀበለን የጠዋት ስጦታችን ምሕረቱ ነው። ለፈተና እጃችንን እንዳንሰጥ ይጠብቀናል። አስቸጋሪ በሆኑ ሁኔታዎች ውስጥ እንዳንሰጥም መንሳፈፊያችን ነው። በኑሮ ማዕበል ተገፍተን እንዳንወድቅ መቆሚያ ምርኩዛችን ነው።

ምሕረት እየደማ ላለ ልብ ደምን የሚይቆም ዘይት ነው። ለዛለና ለደከመ፣ መሄድ ላቀተው እግር የንጉስ ሰረገላ ነው። ለሚንቀጠቀጠው ለፈራው ልብህ የፍቅር ዕቅፍ ነው።

😔ከጥፋትህ የተነሳ ሰው ሁሉ አበዛኸው ብሎህ ትቶህ ሄዷል። ብዙዎችን ምሕረት አድርጉልኝ ስትላቸው ቢደረግልህም ያው ነኽ አትቀየረም በማለት የመለወጥ ተስፋ እንደሌለህ ተናግረውብህ ይሆናል። ነገር ግን እነርሱ አልፈጠሩህም። የፈጠረህ እግዚአብሔር ነው። መቼም አበዛኸው የማይልህ። ሁሌም ይቅር የሚል እርሱ ነው። ፍጹም በሆነ ፍቅር የሚቀበልህ እርሱ ነው። እርሱ ፊት መቆምን አትፍራ፡፡ እርሱ ምስጢረኛህ ነውና፡፡ ሁል ጊዜም እጆቹ ለምሕረት የተዘረጉ ናቸው፡፡  ምህረቱ እስከ ሺህ ትውልድ ድረስ የሚጠብቅ የታመነ አምላክ እንደሆነ እወቅ፡፡ . . . . እግዚአብሔርን አመስግኑ፡፡

የእግዚአብሔር ምሕረት ከሁላችሁ ጋር ይሁን!


https://t.me/anidSew

“በዚች ዓመት ደግሞ ተዋት”



“እርሱ ግን መልሶ፦ ጌታ ሆይ፥ ዙሪያዋን እስክኰተኵትላትና ፋንድያ እስካፈስላት ድረስ በዚች ዓመት ደግሞ ተዋት። ወደ ፊትም ብታፈራ፥ ደኅና ነው . . .” (ሉቃ. 13፥8-9)

ዘመንን የሰጠ እርሱ እድሜያችንን እየቆጠርን እንድንኖር አደረገ። እድሜን መቁጠር በራሱ መጥፎ አይደለም፤ በእድሜያችን መስራት ያለብንን አለመስራት ነው መጥፎና ክፉ የሆነው። ከላይ ካነበብነው ክፍል ውስጥ የእግዚአብሔርን ምሕረት መመልከት እንችላለን። “በዚች ዓመት ደግሞ ተዋት” እግዚአብሔር ከምሕረቱ የተነሳ አዲስ ቀንን እንድናይ ያደርገናል። ለምን? ለእርሱ የሚሆንን ፍሬ እንድናፈራ። ፍሬውንም ማፍራት እንድንችል የሚያደርገንን  ጸጋውንም አብሮ ነው የሚሰጠን። ሌላ ምን ይባላል ተመስገን ነው እንጂ!

ሕይወታችን እግዚአብሔር የራሱን ታሪክ የሚጽፍበት መጽሐፍ ነው። የራሳችንን ታሪክ ለመጻፍ አንሞክር፤ የእኛ ሕይወት አይደለምና። የራሳችን የሆነን ነገር ለመጻፍ ስንሞክር ነው መኖር የሚገባንን የማንኖረው፣ መሆን የሚገባንን የምንሆነው። ስለዚህ እኛጋ ያለ የእግዚአብሔር ታሪክ ነው። እያንዳንዱ ቀናት የመጽሐፉን ገጽ፤ ዓመታቱ ደግሞ አዲስ ምዕራፍ ጅማሮ እንደሆኑ አስባለው። እናም አዲስ ዓመት ሲመጣ እግዚአብሔር አዲስ ምዕራፍ ጀምሮ ነውና፤ አዲሱ ምዕራፍ

💪ለክርስቶስ ወንጌል እንደሚገባ የምንኖርበት ይሁን።

💪ለወንጌል እውነት እንደአንድ ሰው ሆነን የምጋደልበት ይሁን።

💪በአንድ ልብ በአንድ አሳብ በአንድ መንፈስና በአንድ ነፍስ መኖር ይሁንልን።

💪ለእግዚአብሔር የማይሆኑ ነገሮችን በቃ የማለት አቅም የምንለብስበት ይሁን።

💪የጀመርነው ነገር እስከፍጻሜው ይድረስልን።

💪ያዘንበት ነገር ደስታ ይዞልን ይምጣ።

💪የተሸነፈው ማንነታችን ድልን ያጎናጽፈን።

💪ፍሬን ማፍራት ሥራ ይሁንልን።

💪የደረቀው ነገራችን ይለምልም።

💪ቤታችን የበረከት፤ እንግዳ የሚስተናገድበት ቤት ይሁን።

💪የወለድነው ይደግ።

💪ያላገባችሁ ከእግዚአብሔር የሆነ ትዳር ያግኛችሁ።

የእግዚአብሔር ምሕረት፣ ፍቅርና ጸጋ በሕይወት ዘመናችሁ ሁሉ ይብዛ!

https://t.me/anidSew/62