የመንፈስ ፍሬ ግን . . . ራስን መግዛት ነው፡፡ ገላ. 5:22, 23
የመንፈስ ቅዱስ ፍሬ የክርስትና ሕይወት እውነተኛ ባህሪ ነው፡፡ ሐዋርያው ጳውሎስ በገላ. 5:22-23 ዘጠኝ የተለያየ ገጽታ ያሏቸውን ፍሬዎች ጠቅሷል፡፡ አንድ ሰው የሚሰጡትን መንፈሳዊ ስጦታዎችና መክሊቶች ተጠቅሞ ለእግዚአብሔር ስለሚሠራው ሥራ የመንፈስ ፍሬ በቀጥታ የሚነግረን ነገር ባይኖረውም ነገር ግን ግለሰቡ እንዴት ለእግዚአብሔር ሊኖር እንደሚገባ በግልጽ ያሳየናል፡፡ ስለ ግለሰቡ ማንነት ፍንጭ ይሰጠናል፡፡ በገላ. 5፡22-23 የተጠቀሱት ሁሉም መልካም ምግባሮች በኢየሱስ ውስጥ ተገልጠው መታየት ችለዋል፡፡ በመሆኑም የመንፈስ ፍሬ በመንፈስ ቅዱስ አማካይነት እውን መሆን የቻለው በእኛ ውስጥ በሚኖረው የኢየሱስ ክርስቶስ ሕይወት ነው፡፡ የመንፈስ ፍሬ በእኛ ውስጥ በሚከናወነው የመንፈስ ቅዱስ ስራ አማካኝነት የሚታይ የጸባይና የሕይወት ለውጥ ጭምር ነው፡፡ በእራሳችን የእግዚአብሔር ልጆች መሆን እንዳልቻልን ሁሉ በእራሳችን የባህርይ ለውጥ ወይም መንፈሳዊ ፍሬዎችን ማምጣት አንችለም፡፡
የመንፈስ ፍሬ ሙሉ ለሙሉ ሰብዓዊ በሆነ ጥረት ብቻ ልናገኘው የምንችለው ነገር አይደለም፡፡ አንዳንዶቹን ተመሳሳይነት ያላቸውን መልካም ምግባሮች በጎ ፈቃደኝነትን አብልጠን በመለማመድ ልናፈራቸውም ሆነ ገልጠን ልናሳያቸው ብንችልም ነገር ግን ይህ ሁኔታ መንፈስ ቅዱስ በእኛ ውስጥ ከሚሠራው ጋር ተመሳሳይ አይደለም፡፡ “ስለ በጎ ፈቃዱ መፈለግንም ማድረግንም በእናንተ የሚሠራ እግዚአብሔር ነውና።” ፊል. 2፡13 እኛ የእግዚአብሔር ልጆች የምናደርጋቸው ማንኛውም አይነት መልካም ነገሮች ሁሉ መንፈስ ቅዱስ በእኛ ውስጥ የሚሠራው ስራ ውጤት ናቸው፡፡
በክርስትና ሕይወት እውነተኛ ፍሬ የምናፈራበት ቀዳሚ ምስጢር በክርስቶስ መኖር ነው፡፡ እርሱ በእኛ፤ እኛ በእርሱ፡፡ ከክርስቶስ ውጪ እውነተኛ የመንፈስ ፍሬ ማፍራት አንችልም፡፡ የመንፈስ ፍሬ ከውጪ የሚጫንብን ነገር ሳይሆን በውስጣችን የሚኖረው የክርስቶስ ሕይወት ውጤት ነው፡፡ የመንፈስ ፍሬ--የወይኑ ግንድ ከሆነው ክርስቶስ፤ ቅርንጫፍ ወደ ሆኑት አማኞች የሚፈስ የእርሱ ሕይወት ውጤት መሆኑን ኢየሱስ በዮሐ. 15፡1-11 ይነግረናል፡፡ ፍሬውን የሚያሳድገው በኢየሱስ የሚሠራው አምላካዊ ሥራ ነው፡፡ የአማኙ ኃላፊነት በክርስቶስ መኖር ነው፡፡ ክርስቶስ ሃሳባችንን ሲሞላው በድርጊቶቻችን የሚገለጥ ይሆናል፡፡ ኢየሱስ በእኛ ውስጥ ሕያው ሆኖ ይኖራል፡፡ ክርስቶስ በእኛ ውስጥ የኖረው ህይወት በውስጣችን ፍሬ ስለሚያፈራ በምላሹ የእርሱን ባህርይ የምናንጸባርቅና የምናሳይ እንሆናለን፡፡ የመንፈስ ፍሬ በመንፈስ ቅዱስ አማካይነት በክርስቶስ ተከታዮች ውስጥ የሚያፈራ የኢየሱስ ባህርይ ነው፡፡
ራስን መግዛት በገላትያ 5:22 ከተጠቀሱ የመንፈስ ቅዱስ ፍሬዎች አንዱ መሆኑን ብዙዎቻችን እናውቃለን። ሁላችንም ባንሆን አንዳንድ ጊዜ ራሳችንን መግዛት አቅቶን መሆን የማይገባንን ሆነን ራሳችንን አሳዛኝና አላስፈላጊ ሁኔታዎች ውስጥ እናገኘዋለን። ብዙ ጥፋትም አድርሰን እናውቃለን። ራስን መግዛት እንደየሰው ዓላማ የተለያየ ቢሆንም በሁሉም የሥራ እና የኃይማኖት መስክ የተወደደ ነገር ነው። ራስን ስለ መግዛት መማርና ኑሮውን መለማማድ ከባድ ቢሆንም ወደ እምነት ብስለት ይመራናል። መድኃኒት ይመራል ነገር ግን ጤንነትን ይሰጣል። አንዳንድ ጊዜ የጌታ ቃል ምክርም እንደ መድኃኒት ነው። መንፈሳዊ ጤንነትንንና እድገታችንን ይጠብቃል። ከዛሬ በመጀመር በሁለት ተከታታይ ክፍሎች ራስን ስለመግዛት እንወያለን፡፡ የውይይታችን ዓላማም በእምነታችን ጉዞ ራሳችንን መግዛት ወይንም መቆጣጣር በሚያቅተን ነገር ላይ አሸናፊነትን እንድናገኝ መርዳት ነው፡፡
በአሁኑ ወቅት፣ ራስን ስለ መግዛት መወያታቸን አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
በዛሬው ጊዜ በሰዎች ላይ የሚደርሱት አብዛኞቹ ችግሮች የሚመነጩት ራስን ካለመግዛት ነው። አንዳንዶች ራሳቸውን መግዛት ስለሚያቅታቸው ከትምህርት ወይም ከሥራ ጋር በተያያዘ ዛሬ ነገ የማለት ልማድ የሚታይባቸው ከመሆኑም ሌላ የሚጠበቅባቸውን ነገር በትጋት ለማከናወን ይቸገራሉ። በተጨማሪም ራሳቸውን የማይገዙ ሰዎች ተሳዳቢዎች፣ ሰካራሞችና ዓመፀኞች ሲሆኑ፣ አላስፈላጊ ዕዳ ውስጥም ሊዘፈቁ እንዲሁም ለፍቺ፣ ለሱስ፣ ለእስር፣ ለስሜት ቀውስና ለዝሙት ተጋላጮች ናቸው፡፡ እነዚህ ችግሮች ራስን አለመግዛት ከሚያስከትላቸው መዘዞች መካከል ጥቂቶቹ ናቸው። በግልጽ ማየት እንደሚቻለው ራሳቸውን መግዛት የሚያቅታቸው ሰዎች በራሳቸውም ሆነ በሌሎች ላይ ጉዳት ያስከትላሉ። የሚያሳዝነው ራስን የመግዛት ችግር ከዕለት ወደ ዕለት እየተባባሰ መምጣቱ ነው። አውቀውም ይሁን ሳያውቁ ድርጊታቸው በራሳቸውም ሆነ በሌሎች ላይ የሚያስከትለውን መዘዝ ሳያገናዝቡ ፍጹም ባልሆነው ሥጋቸው ምኞት እየተነዱ ሕይወታቸውን እንዳሻቸው የሚመሩ ብዙዎች አሉ። ሰዎች ክፉ ነገር እንዲያደርጉ ለሚቀርብላቸው ጥያቄ እምቢ ለማለት አቅሙም ፍላጎቱም እንደሌላቸው ከመቼውም ጊዜ በበለጠ በዘመናችን ጎልቶ ይታያል።
በዘመናችን ያለውም ባሕል ራስን መግዛትን አያበረታታም። እንደፈለጉ መሆንን በሚያበረታታው ባሕላችን አዋቂዎችም ሆንን ልጆች የፈለግነውን እንድናደርግ የሚያነሳሳ መልእክት ሁልጊዜ ይዥጎደጎድብናል። በቅን ልቦና ተነሳስተው ምክር የሚለግሱንም ሆኑ ለገንዘብ ሲሉ የማይረባ ምክር የሚሰጡን ሰዎች ምንጊዜም ስሜታችንን ማስተናገድ እንዳለብን ሲናገሩም እንሰማለን። ሰው ያጨሳል ማጨስ እንደሚጎዳ በማስረጃ አስደገፎ ያወራሃል ግን ያጨሳል ግን ይሞታል ግን ያውቀዋል ግን አቅም የለውም እውቀቱ አድማሱን ለማስፋት ያክል ነው እንጂ ስሜቱን ለመግታትና ለመቆጣጠር አላገዘውም፡፡ ክርስቲያኖች እንደመሆናችን መጠን ይህ መሆኑ አያስገርመንም፤ ምክንያቱም “በመጨረሻው ቀን የሚያስጨንቅ ዘመን እንዲመጣ ይህን እወቅ። ሰዎች . . . ራሳቸውን የማይገዙ . . . ይሆናሉ”፡፡ 2 ጢሞ. 3:1-3 በመጨረሻዎቹ ቀናት” ውስጥ እንደምንኖር ከሚያሳዩት ምልክቶች መካከል አንደኛው ታዲያ ሰዎች “ራሳቸውን የማይገዙ” መሆናቸው ነው፡፡ በዚህ በመጨረሻው ዘመን ውስጥ ክርስቲያኖች እራሳቸውን ከሌሎች የሚለዩበትን አንዱን የሆነውን ራስን የመግዛት ባህሪን እያሳዩና እያንፀባረቁ መኖር አለባቸው፡፡
ራስን መግዛት ስንል ምን ማለታችን ነው?
ራስን መግዛት ከውስጣችን ሊወጣ የሚታገለንን ማናቸውንም የስጋ ፍላጎትና ምኞትን መቆጣጠርና መግዛት ራስን መግዛት ይባላል፡፡ ራስን መግዛት ማለት ስሜትን መቆጣጠር፤ መሻትን ማሸነፍ፤ ሁለንተናን ለእግዚአብሔር ፈቃድና ክብር ማስገዛት ማለት ነው፡፡ ራስን መግዛት ከውስጥ የሚመነጩ እና ከውጭ የሚመጡ ግፊቶችን መቋቋም መቻል ነው፡፡ ራስን መግዛት ለቁጣ፣ ለቂም በቀልና ለጥላቻ፣ ለሥጋዊ ጥቅም፣ ለስካር . . . ወዘተ በአምሮአችንና በልባችን ግፊት ከሚመጣ ፈተና ራስን ማዳን እና ለሌሌችም ምስክር መሆን ነው። ራስን መግዛት ብዙ የሥጋ እና የዓለም ክብር ግብዣዎችን እምቢ ማለት ነው፡፡ ራስን መግዛት በሀሳብ፣በቃላትና በተግባር የሚገለጥ ነገር ነው።
. . . ይቀጥላል
ሀብታሙ መረሳ
07/03/2012 ዓ.ም