Monday, October 15, 2018

መንገዱን . . .

ደስተኛ እንደሆንክ ይሰማሃል? ከሆነ ደስተኛ ያደረገህ ምንድን ነው? ቤተሰብህ፣ ሥራህ ወይስ ሃይማኖትህ ነው? አሊያም ደግሞ ደስተኛ ሊያደርግህ የሚችልን ነገር በተስፋ እየተጠባበቅክ ይሆናል፤ ለምሳሌ ትምህርትህን የምትጨርስበትን፣ ጥሩ ሥራ የምትይዝበትን፣ በማህበረሰቡ የከበሬታን ወንበር ሊያስገኙ የሚችሉ ሥራዎችን የምትሰራበትን አሊያም አዲስ ቤትና መኪና የምትገዛበትን ጊዜ በጉጉት እየጠበቅክ ሊሆን ይችላል።

ብዙ ሰዎች አንድ ግብ ላይ ሲደርሱ ወይም የፈለጉትን ነገር ሲያገኙ ደስታ ይሰማቸዋል። ይሁን እንጂ እንዲህ ያለው ደስታ ለምን ያህል ጊዜ ይዘልቃል? በአብዛኛው ለረጅም ጊዜ የሚዘልቅ አይደለም፤ ይህ ደግሞ ለሐዘን የሚዳርግ ነው።

ደስታ ‘አንጻራዊ ዘለቄታ ያለው የደህንነት ስሜት’ የሚል ፍቺ ተሰጥቶታል። በተጨማሪም ከእርካታ አንስቶ ጥልቅና ከፍተኛ እስከሆነ ውስጣዊ ፍስሐ ድረስ ባሉት ስሜቶች እንዲሁም እነዚህ ስሜቶች እንዲቀጥሉ ባለን ተፈጥሯዊ ፍላጎት ይንጸባረቃል።

ታዲያ እውነተኛና ዘለቂ የሆነውን የደስታ ስሜት ከየት ነው ማግኘት የምንችለው? ሁል ጊዜ ያለጭንቀት ባለን ነገር እየተደሰትን መኖር የምንችለው የደስታችን ምንጩ ከወዴት ሲሆን ነው? መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል
" . . . ስለዚህ ከባልንጀሮችህ ይልቅ እግዚአብሔር አምላክ የደስታ ዘይትን ቀባህ።" (መዝሙረ ዳዊት 45:7) እንዲሁም " በልቤ ደስታን ጨመርህ፤ ከስንዴ ፍሬና ከወይን ከዘይትም ይልቅ በዛ።" (መዝሙረ ዳዊት 4:7) ስለዚህ እውነተኛና ዘላቂ ደግሞም እጅግ ብዙ የሆነውን ደስታ ማግኘት የምንችለው ከእግዚአብሔር ነው። ይኽ ሲሆን አለኝታችን ደስታ ነው (መጽሐፈ ምሳሌ 10:28)፤ የልባችንም ደስታ ሁልጊዜ እንደ ግብዣ ነው።  (መጽሐፈ ምሳሌ 15:15)

በዚህ በተሻለው የኪዳን ዘመን ውስጥ ስንኖር እግዚአብሔርን ያረካ፣ ያስደሰተ ለሰውም ፍፁም ሰላምና ደስታ የሚሰጥ አንድ ጌታ ኢየሱስ አለ። እርሱም " ደስታዬም በእናንተ እንዲሆን ደስታችሁም እንዲፈጸም ይህን ነግሬአችኋለሁ።"
(የዮሐንስ ወንጌል 15:11) በማለት ደስታውን ሰጥቶናል። በሌላ ስፍራም ". . . ደስታችሁንም የሚወስድባችሁ የለም።"
(የዮሐንስ ወንጌል 16:22) በማለት የደስታችን ምንጩ እንዲሁም ዘላለማዊ ደስታንም ሰጪ እርሱ እንደሆነ ይነግረናል። ከደስታው ባለቤት ደስታን ተቀበሉ። ሃዘንን ፍጹምና ዘላቂ በሆነ ደስታ የሚቀይር እርሱ ብቻ ነውና። የማያልቅና ማንም የማይቀማችሁን ደስታ ለዘላለም ትሰንቃላችሁና።

ሀብታሙ መረሳ
05/02/2011ዓ.ም

Friday, October 5, 2018

በእግዚአብሔር እውቀት በሳል ሰው እግዚአብሔርን ያውቃል። እግዚአብሔር ደግሞ መለኮታዊ አምላክ ነው። ከእግዚአብሔር የምንማረው ደግሞ መለኮታዊ እውቀት ነው።